>

በግፍ የታሰሩት የአዲስ አበባ እና የባልደራስ ወጣቶች በዋስትና ተለቀዋል፣ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል!!! (ባልደራስ)

በግፍ የታሰሩት የአዲስ አበባ እና የባልደራስ ወጣቶች በዋስትና ተለቀዋል፣ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል!!!

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ወቅታዊ መግለጫ…!!!

ከ41 ቀናት እስር በኋላ በጅምላ የታፈሱት የአዲስ አበባ እና የባልደራስ ወጣቶች ትላንት እና ዛሬ ከእስር በዋስትና ተለቀዋል፡፡ ወጣቶቹ በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜ፣ ፖሊስ ለፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ባቀረበው ክስ #ወጣቶቹ በአድዋ እና በካራማራ ክብረ በዓላት ላይ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲያምጽ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በአደባባይ በመሳደብ ተግባር ላይ አግኝቻቸዋለሁ ብሏል፡፡
ፖሊስ በዚህ መንገድ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ከተቀበለ በኋላ፣ የህዝብ ትራንስፖርት የሌለበት  በመሆኑ ወጣቶቹ በወዳጅ ዘመዶቻቸው በቀላሉ ሊጠየቁ ወደማይችሉበት የአባ ሳሙኤል እስር ቤት በመውሰድ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለ41 ቀናት በእስር አንገላቷቸዋል፡፡ የአባ ሳሙኤል እስር ቤት ግንባታው ገና ያላለቀ በመሆኑ፣ በቂ ውሃ፣በቂ መጸዳጃ፣ በቂ ምግብ ወዘተ የለውም፡፡ በዚህም ሳቢያ፣ ወጣቶቹ በረሃብ፣ በውሃ ጥም፣ በንጽህና ጉድለት ፍዳቸውን አይተዋል፡፡ ይባስ ብሎም የአጼ ምኒልክ፣አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እና የአድዋ ድል ምስል ያለባቸው ልብሶች ለብሰው ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ ክልከላ ተደርጎባቸዋል፡፡
የዚህ ሁሉ ዓላማ፣ ወጣቶቹ ፖለቲካን እርግፍ አድርገው እንዲተው የነበረ ቢሆንም፣ በተቃራኒው ይበልጥ ፀንተው በመቆም ለመላው አገር አርአያ ሆነዋል፡፡ እንዲሰበሩ ተሞክሮ አልተሰበሩም፣ እንዲሸነፉ ተሞክሮ አልተሸነፉም፡፡ በእስራቸው ወጣቶቹ አሸናፊ፣ በህገወጥ መንገድ ያሰሯቸው ተሸናፊ ሆነው ሂደቱ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በእነዚህ የአዲስ አበባ እና የባልደራስ ወጣቶች በእጅጉ ይኮራል፡፡ የአነገቡትን መንፈስ ይዞም ለህዝብ ለገባው ቃልኪዳን በታማኝነት ይፀናል፡፡
ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል!
 ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
Filed in: Amharic