>

የኢትዮጵያን ደጃፍ እያንኳኳ ያለው የራሺያ ጦርነትና፣ ይዞብን እየመጣው ያለው መዘዝ! (አሳፍ ሀይሉ)

የኢትዮጵያን ደጃፍ እያንኳኳ ያለው የራሺያ ጦርነትና፣ ይዞብን እየመጣው ያለው መዘዝ!
አሳፍ ሀይሉ

 

*…. በቀይ የተመለከቱት ሀገሮች ራሺያን እየደገፉ ያሉ ሀገሮች ናቸው – በሚል በእነ አሜሪካ የተፈረጁ (የተጠቆሩ) ሀገሮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የቀይ ምድብተኞች መሐል ኢትዮጵያም አለችበት፡፡ ለምን? 
ባለፈው (ከሣምንት በፊት) ከከተመድ የዓለም ሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ራሺያ ‹‹ትባረር›› ወይስ ‹‹አትባረር›› የሚል ድምጽ ሲሰጥ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ራሺያ ልትባረር አይገባትም›› በማለት ድምፁን ለራሺያ ስለሰጠ ነው፡፡
በድምፅ አሰጣጡ 93 ሀገሮች የራሺያን መባረር ሲደግፉ፣ እነ ህንድን፣ ፓኪስታንን፣ ደቡብ አፍሪካን፣ ግብጽን፣ እነ ኤምሬትስ፣ ካታር፣ ኢራቅ፣ ኩዌት፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሲንጋፖር፣ ታይላንድ፣ ወዘተ የመሳሰሉ (በቢጫ የማስጠንቀቂያ ቀለም የተመለከቱት) 58 ሀገሮች ደግሞ ድምጸ ተዓቅቦ አድርገው ነበር፡፡
ኢትዮጵያ፣ ቻይና፣ ሰሜን ኮርያ፣ ቬትናም፣ ኢራን፣ ሶሪያ፣ የሚገኙበት 24 ሀገሮች ግን ‹‹ራሺያ ከሰብዓዊ መብት ካውንስሉ መባረር የለባትም›› በማለት በሙሉ ድምጽ ከራሺያ ጎን ቆመዋል፡፡
በመጨረሻ በአብላጫ ድምጽ የተሰጠባት ራሺያ፣ ካውንስሉ የማሰናበት ርምጃ ከመውሰዱ ቀድማ፣ በራሷ ፈቃድ ከካውንስሉ መውጣቷን አስታውቃለች፡፡
ኢትዮጵያ ለራሺያ ወግና ድምጿን በሰጠች 24 ሰዓት እንኳ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአሜሪካ በሪሞት ኮንትሮል እንደሚዘወሩ የሚነገርላቸው ሁለቱ የዓለም የሰብዓዊ መብት አስጠባቂ (ተሟጋች) ተቋማት – ‹‹ሂዩማን ራይትስ ዎች›› እና ‹‹አምንስቲ ኢንተርናሽነል›› የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸሙን የሚያሳይ ዝርዝር ዘገባዎችን አውጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ለራሺያ ድምጽ መስጠት ተከትሎ መግለጫቸውን ያወጡት ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ በዘገባቸው የአሜሪካ መንግሥት ጀምሮት የተወውንና ዳር ዳር ሲልበት የቆየውን፣ ‹‹ምዕራብ ትግራይ›› በመባል ይታወቅ በነበረው በወልቃይትና ፀገዴ የአማራ ልዩ ኃይሎች ዘርን መሠረት ያደረገ ዓለማቀፍ የሰው ልጆች ወንጀልን (ክራይምስ ኧጌይንስት ሂዩማኒቲ) ፈጽመዋል በማለትም፣ የአማራን ልዩ ኃይል ነጥለው በስም በመጥቀስ፣ መግለጫቸውን አውጥተዋል፡፡
ከእነዚህ ሁለት ድርጅቶች መግለጫዎች ጥቂት ቀደም ብሎ የወጣው የአሜሪካ መንግሥት ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት በበኩሉ፣ በአብይ አህመድ የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ከብሔር የጸዳ ፓርቲ መሆኑን፣ አብይ አህመድ የፌዴራል ፖሊስ ሃይልን ብቻ የሚመራ መሆኑን፣ መከላከያን የሚያዘውና የሚመራው ተጠሪነቱም ለመከላከያ ሚኒስትሩ መሆኑን፣ እና የክልል ልዩ ኃይሎች በአብይ አህመድ ለሚመራው የፌዴራል መንግሥት ተጠሪ እንዳልሆኑም፣ በአብይ አህመድ እንደማይታዘዙም የሚገልጽ ሪፖርት ማውጣቱ ይታወቃል፡፡
እነዚህን መግለጫዎች ደማምሮ ለሚያያቸው ሰው፣ በአሜሪካ ፊት አውራሪነት በሚመሩት ምዕራባውያን እየተሄደበት ያለውን ሎጂክ ማንኛውም ሰው ይበልጥ በቀላሉ መረዳት ይችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ፣ በኃያላኑ በኩል እየተከናወነ ያለው ነገር ይህን የመሰለ ነው፡፡
በሌላ በኩል ግን የኢትዮጵያ ለራሺያ ወግና ድምጽ መስጠትና፣ በሰፊ ልዩነት አብዛኛው የአፍሪካና የእስያ (እንዲሁም የላቲን አሜሪካ) ሀገሮች በርካታ እርዳታ ሲያዘንቡላቸው ከኖሩት ከአሜሪካኖች ይልቅ፣ ለራሺያ አዘንብለው መገኘት አስደንጋጭ መራር ዜና ሆኖባቸዋል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው? እና ምን ብናደርግስ ወደኛ እናመጣቸዋለን? በሚል እየመከሩም ይገኛሉ፡፡
በዚህ መሐል አሜሪካ ልዩ ፕሬዚደንታዊ መልዕክተኛዋን ወደ አብይ አህመድ ልካ መምከሯ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአዲሳባ ወጣቶችም ራሺያ ኤምባሲ በራፍ ላይ ተኮልኩለው መታየታቸውና፣ በፈቃደኝነት ሊዘምቱ ነው መባሉን እየተመለከትን እንገኛለን፡፡
Filed in: Amharic