>
5:26 pm - Monday September 15, 1327

«ለሩሲያ መዋጋት እንፈልጋለን!» ስላሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሩስያ ኤምባሲ ምላሽ (DW)

«ለሩሲያ መዋጋት እንፈልጋለን!» ስላሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሩስያ ኤምባሲ ምላሽ
DW

አዲስ አበባ የሚገኘው የሩስያ ኤምባሲ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ኤምባሲው «የሩስያ ጦር ሠራዊት ውስጥ ለመቀጠር ማንኛውንም ማመልከቻ አይቀበልም» ሲል ጽፏል። 
በርካታ ኢትዮጵያውያን ለሩስያ ተሰልፈው ለመዋጋት ማመልከቻቸውን ይዘው እስከ ትናንት ድረስ አዲስ አበባ የሚገኘው የሩስያ ኤምባሲ መታየታቸውን ዶይቸ ቬለ (DW) በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል። ዩክሬን ውስጥ ጦርነት ለገጠመችው ሩሲያ «መዋጋት እንፈልጋለን» ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለምዝገባ አዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ፊት ለፊት እንደተሰለፉ የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ ትናንት ተመልክቶ በቦታው የተሰለፉትን ኢትዮጵያውያን አነጋግሯቸውም ነበር። ዶይቸ ቬለ ካነጋገራቸው ወጣቶች መካከል አንዱ፦ «ከመከላከያ የተሰናበተበትን» መረጃ ይዞ በሥፍራው በመገኘት መመዝገቡን ገልጧል።  ለመመዝገብ ወደ ኤምባሲው አቅንቶ ሳይሳካለት እንደቀረ ለዶይቸ ቬለ የተናገረ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሦስተኛ ዓመት የአካውንቲንግ ተማሪ ወጣት ከዚህ ቀደም በውትድርና ሞያ የሰለጠነበት ማስረጃ ስለሌለው ምዝገባው ሳይሳካለት በመቅረቱ እንደሚቆጨው ገልጧል። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአዲስ አበባ የሩሲያ ኤምባሲ ባለስልጣናት ለሩሲያ የሚዋጉ ወታደሮችን ከኢትዮጵያ እየመለመሉ አለመሆኑን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። ሩስያ ለሚጓዙ ግን እንደ ሁልጊዜው የቪዛ አገልግሎት እንደሚሰጡ አክለዋል።
የሩስያ ኤምባሲ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፦ «ለ1961 የቪዬና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ድንጋጌ» እንደሚገዛ በመጥቀስ «የውጭ ሃገራት ዜግነት ያላቸውን ሰዎች በሩስያ ፌዴሬሽን ጦር ሠራዊት መቅጠር» የኤምባሲው የዲፕሎማሲ ተልእኮ አካል አለመሆኑን ገልጧል።  ኤምባሲው ማመልከቻ እንደማይቀበል በመጥቀስ፦ «በኢሜል እና በአካል በመገኘት ድጋፋቸውን» የገለጡ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ግን ምስጋናውን አቅርቧል። «የኢትዮጵያ መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዩክሬን ጋር በተያያዘ ጉዳይ ለሩስያ ፌዴሬሽን ላደረገው ድጋፍ ልባዊ ምሥጋናችንን እናቀርባለን» ሲልም አክሏል። በመግለጫው ስር አስተያየት የሰጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሩስያ በታሪክ ከዚህ ቀደምም ኾነ በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ በመግለጥ በማንኛውም ጊዜ ቢጠሩ ለሩስያ «ተሰልፈው እንደሚዋጉ» ያላቸውን ፍላጎት አንጸባርቀዋል። ኢትዮጵያውያኑ ለሩስያ መዋጋት የፈለጉት ሀገሪቱ ውስጥ ያለው «የኑሮ ውድነት ከብዷቸው ነው» የሚሉ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል።
በእናንተ አስተያየት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች «ለሩስያ መዋጋት እንፈልጋለን» በማለት ለቀናት በሩስያ ኤምባሲ ደጃፍ ማመልከቻቸውን ይዘው የተሰለፉበት ምክንያቱ ምንድን ነው ትላላችሁ? እንደተለመደው የሰከነ አስተያየት ለምትሰጡን ምሥጋናችን ከወዲሁ እንገልጣለን።
Filed in: Amharic