ወልቃይት ጠገዴ እና ወ/ሮ አብረኸት ዳኘው (የቀድሞ የፈንቅል አመራር)
ከዶ/ር በቃሉ አጥናፉ
በሰሜን አሜሪካው የጥቁሮች እንቅስቃሴ እንደ እነ አብርሀም ሊንከን አይነት ነጭ መሪዎች የጥቁሮችን የነፃነት ትግል አበክረው ደግፈዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ነጭ የደቡብ አፍሪካ ተወላጆች (እንደ እነ ሄለን ሱዝማን እንደ ሄሌሴ ሩት አይነት) የጥቁር አፍሪካውያንን የነፃነት እንቅስቃሴ ይደግፉ ነበር፡፡
ከቡድን እሳቤ ወይም ማንነት ወጥቶ ለሰው ልጅ እኩልነት በምክንያታዊነት እና በሚዛናዊነት ማሰብ መቻል ታላቅነት ነው፡፡ የብሄር ፖለቲካ በሀገረ ኢትዮጵያ መቀንቀን ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል የዜጎችን ህመም፣ ሞት እና ሰቆቃ የሚመለከትበት
እይታ ከራሱ ብሄር ጥቅም አንፃር ብቻ በመሆኑ አሁን ላለንበት ምስቅልቅል ህይወት ዳርጎናል፡፡
ወልቃይት፣ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ በድሮው በበጌምድር ክፍለ ሀገር ስር ሲተዳደሩ እንደነበር በርካታ የታሪክ ድርሳናት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ታሪካዊ መዛግብቱ እንዳለ ሁኖ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዘመን የትግራይ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም የትግራይ ወሰን ተከዜ ነው ብለው በቪኦኤ (VOA) ላይ መስክረዋል፡፡ የትህነግ መስራች እና ሊቀ መንበር የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄም ወልቃይት፣ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ በጎንደር ክፍለ ሀገር ስር እንደነበር ከሲሳይ አጌና ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረው ነበር (ኢሳት)፡፡
እውነታው ይህ እንደሆነ እየታወቀ የትህነግ/የወያኔ አጥፊ ቡድን ወረርሽኝ የተዛመደባቸው የፖለቲካ ልሂቃን በጫጫታ ብዛት እውነትን በሀሰት ለመቀየር ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ አብዛኛው ትህነጋውያን እና ኦነጋውያን እሳቤን ያነገቡ ግለሰቦች የጎሳ ፖለቲካን ተግተው የተበዳይ ሙሾ አውራጆች ሲሆኑ ከነዚህ ቡድኖች መካከል ጥቂት ግለሰቦች ለእውነት የቆሙ መኖራቸው ሲታሰብ ለነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ነው፡፡
በጥቁሮች የነፃነት ትግል ጥቂት ነጮች የጥቁሮችን ትግል ደጋፊ እንደነበሩ ሁሉ ዛሬም የትግራይ ተወላጅ ወ/ሮ አብረኸት ዳኘው የአማራውን የወልቃይትን ጥያቄ ተገቢነት ተረድታ ወልቃይት የትግራይ አካል እንዳልነበረች ከትግራይ ተወላጅዋ እውነታውን በመስማቴ አብረኸትን ሳላደንቃት ማለፍ አልፈልግም፡፡ ወ/ሮ አብረኸት ዳኘው(የቀድሞ የፈንቅል አመራር) ከጋዜጠኛ ጌትነት አሻግሬ ጋር በእኛ ቲዩብ ላይ ባደረጉት ውይይት የአማራ ህዝብ የደረሰበትን በድል ይቅር ብሎ የትግራይን ተፈናቃዬች ተቀብሎ በፍቅር ማስተናገዱ አድንቃ ወልቃይት የጎንደር ክፍለ ሀገር እንደነበረ እና በእርስዋ እድሜ ወደ ትግራይ ተወስዶ አሁን ወደ አማራ እንደተመለሰ መግለፅዋን አደመጥን፡፡ የሰው ልጅ በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት ራሱን ሳያቧድን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ ኢ-ፍተሀዊነትን፣ አድሎዓዊነትን፣ ዘረኝነትን እያወገዘ ለእውነት መቆም ይገባዋል፡፡ የትህነጋውያን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ያልሆኑ እንዲህ አይነት ለእውነት የቆሙ ትግራዋይ ወደ ሚዲያ መቅረባቸው በሁለቱ ክልል መካከል ያለውን መካረር ያለዝበዋል፤ ሰላምንም ያመጣል፤ የሁለቱን ህዝብ መለያየት ለሚፈልጉ የፖለተካ ቁማርተኞችም መልስ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡