>

ሰሙነ ህማማት ዘአርብ ፡ ስቅለት

ሰሙነ ህማማት ዘአርብ ፡ ስቅለት

†        †         †        †         †

ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡
በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ። ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/
የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡
 በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና የስቅለት ዓርብ ይባላል።/ማቴ ፳፯፥፴፭/
 13ቱ  ሕማማተ  መስቀል!!!
1ኛ. ተአስሮ ድኅሪት (ወደኋላ መታሰር)
2ኛ. ተስሕቦ በሐብል (በገመድ መሳብ)
3ኛ. ወዲቅ ውስተ ምድር (በምድር ላይ መውደቅ)
4ኛ. ተከይዶ በእግረ አይሁድ (በእግረ አይሁድ መረገጥ)
5ኛ. ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ (ከምሶሶ ጋር መላተም)
6ኛ. ተጽፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)
7ኛ. ተቀስፎ ዘባን (ጀርባን በጅራፍ መገረፍ)
8ኛ. ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዱላ መመታት)
9ኛ. አክሊለ ሦክ (የሾህ አክሊል መድፋት)
10ኛ. ፀዊረ መስቀል (መስቀል መሸከም)
11ኛ. ተቀንዎ በቅንዎት (በችንካር መቸንከር)
12ኛ. ተሰቅሎ በዕፅ (በመስቀል ላይ መሰቀል)
13ኛ. ሰሪበ ሐሞት (መራራ ሐሞትን መጠጣት)
✝ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቸነከረባቸው አምስቱ ችንካሮች፦
1. ሳዶር ፦ በዚህ ችንካር ቀኝ እጁን ቸነከሩት
2. አላዶር ፦ በዚህ ችንካር ግራ እጁን ቸነከሩት
3. ዳናት ፦ በዚህ ችንካር ሁለት እግሩን ቸነከሩት
4. አዴራ ፦ በዚህ ችንካር ማሀል ልቡን ቸነከሩት
5. ሮዳስ ፦ በዚህ ችንካር ደረቱን ቸነከሩት
 ሰባቱ  የመስቀሉ ቃላት
★አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?
 ★አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።
★ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር እንድትኖር በእውነት እነግርሃለሁ።
★እነሆ ልጅሽ አነኋት እናትህ ።
★ተጠማሁ።
★አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ።
★የተጻፈው ሁሉ ደረሰ ተፈጸመ አለ።
 ሰባቱ  ተዐምራት – ጌታ እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ የተፈጸሙ ተዐምራት፦
★ፀሐይ ጨልሟል
★ጨረቃ ደም ሆነ
★ከዋክብት ረገፉ
★ዐለቶች ተሠነጠቁ
★መቃብራት ተከፈቱ
★ሙታን ተነሡ
★የቤተ መቅደስም መጋረጃ ለሁለት ተቀደደ
ለእኛ ለኀጥአን ሲል ይህንን ሁሉ መከራ የታገሰ አምላክ ስለ አሥራ ሦስቱ ኅማማቱ፣ አምስቱ ቅንዋቱ፣ ስለ ቅዱስ መስቀሉ፣ ስለ ድንግል እናቱ ለቅሶና ስለ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስ ብሎ ይማረን።
“እንበለ ደዌ ወሕማም፣
             እንበለ ጻማ ወድካም፣
             አመ ከመ ዮም
             ያብጽሐነ ፤ ያብጻሕክሙ፣
             እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም፡፡”
Filed in: Amharic