የባለስልጣናት ምንጣፎች….!!!
እስክንድር መርሀ ጽድቅ
ነገረ- መጽሐፍ ወ ኢትዮጵያ
በሰለሞን ለማ ገመቹ
* ቀረብ ባለው ጊዜ (በ2014 ዓ.ም አጋማሽ ማግስት ከነበሩት በአንደኛው ወር) ‹‹የባለሥልጣናት ምንጣፎች›› የተሰኘው መጽሐፍ በሃገር ፍቅር ቴአትር ትንሺቱ አዳራሽ ተመርቋል፡፡ የተመረቀው መጽሐፍ የጸሐፊ እስክንድር መርሐጽድቅ ነው፡፡
* የመጽሐፉ የሽፋን ገጽ እጅግ በጣም ማርኮኛል፡፡
* ይህ የተመረቀው መጽሐፍ ለጸሐፊው ስንተኛው መጽሐፉ ነበር?
ምን አገባኝ ግን?… እኔ የመጽሐፍ ጸሐፊያን የጻፉት መጽሐፍ ክብረ-ወሰን ምዝገባ ክፍል ኃላፊ ወይም ተጠሪ አይደለሁም፡፡
* ሆ!… ግን መጽሐፍ ‹‹ተመርቋል›› ወይም ‹‹ተመረቀ›› ሲባል… ምን ማለት ነው?
እ… እንደው በደፈናው ‹‹ተመርቋል›› ማለት ምን ማለት ነው? ወይስ ምንስ ማለት ነበር?
* ያው አልተረገመም ማለት ሊሆን ይችላል፡፡
በሌላ ልማድ ወይም ዘ ልማድ…. የታተመን መጽሐፍ ወዳጅ ዘመድ፣ ቤተሰብ፣ መጽሐፍ ወዳጅና ጸሐፊ አክባሪ የሆኑ ሰዎች… ተሰባስበው ‹‹ይሁን ይሁን ይበል ይበል… አሉ›› ማለት ነው አሉ፡፡
ተጽፎ ለአሳታሚዎች ቅድሚያ ክፍያ ተከፍሎበት፣ ጸሐፊው የሌለ ድካም ሁሉ ደክሞበት፣ መጽሐፍ አከፋፋዮች የየድርሻቸውን ለመውሰድ በየራሳቸው መንገድ ሽቅብ ቁልቁል ለማለት ተዘጋጅተውበት ወይም ብለውበት ወይም ለግመውበት… ሲያበቁ፤ ከዚህም በፊት በስተኋላ ሰዎች ስለታተመውና ወደ አንባቢያን ደርሷል፣ ሊደርስ ነው… ስለተባለው መጽሐፍ በአንድ አዳራሽ ጉባዔ ተሳተፉበት… ስለ ጸሐፊው፣ ስለ መጽሐፉ አንድ አፍታ፣ ለተወሰነ ወይም ለተቆረጠ ሰዓት ተነጋገሩበት… ማለት ነው ‹‹መጽሐፍ ተመረቀ›› ማለት?
* ከፍ ሲል ያነበባችሁት ወይም ዓይታችሁ በሾርኒ ሽርደዳ… ያለፋችሁት ቀዳሚ ቃል እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በቅርቡ የተመረቀውን የእስክንድር መርሐጽድቅን ምጥን ገጽ ያላትን መጥሐፍ አንድ አፍታ ተወጣኋት፡፡ ጊዜ አልፈጀችብኝም፣ አላነቀፈችኝም፣ ለማንበብ አልገረገረችም… ለማለት ነው፡፡
፩ኛ፡- የመጽሐፉ ቀዳሚ ጥሑፍ ማለትም የ‹‹መንፈሳዊያን ድምፆች›› መልዕክት ጥልቅ ሐሣብ ግሩም ነው፡፡ በጥሑፉ የተነሱት ነጥቦች አግባብነት ያላቸው ናቸው፡፡ በሑፉ ያቋቱት አስተያየቶችም ገንቢና አሳማኝነት ያላቸው ሆኖ አግኝቼአቸዋለሁ፡፡ ‹‹የኃይማኖች ተቋማት ስብከታቸውን /አስተምህሯቸውን/ በተመጠነና ጨዋነት በተመላበት ሁኔታ ለየዕምነቱ ተከታዮች ማሰማት ይኖርባቸዋል…›› በሚለው በጥሑፉ ወደረኛ ሐሣብ ወይም አስተያየት በበኩሌ ተስማምቼአለሁ፡፡ ይልቁንም በመጮህ ወይም በመጯጯህ ማንኛውንም ዓይነት ትምህርት ማስረጽ፣ ወደሚያስፈልገው ቦታ… ማድረስ አይቻልም የሚል ግለ-አቋም ስላለኝም…. ከዚህ አንፃር ‹‹መንፈሳዊያን ድምፆች›› በሚለው ጽሑፍ ውስጥ ያቋተውን ጥቅል መልዕክት ወድጄዋለሁ፡፡
፪ኛ፡- ገራሚው ‹‹ያሸነፋችሁትና ‹ያሸነፋችሁት›…›› በሚለው ርዕስ ሥር በአምስት የዕይታ ረድፍ ተሸንሽኖ ነው ተቀምሮ… የቀረበው ጥሑፍ በርግጥም ገራሚ ነው፡፡ ምንም ዕንኳ ይህ ጥሑፍ ጢኖ (ሚጢጢ) ምክር ቢሆንም፡፡ ለነገሩ ምክርን በማስረዘም ሳይሆን በማሳጠር ነው ተመካሪው አስተዋይ ሆኖ እስከተፈጠረ … ድረስ ማስረጽ የሚቻለው፡፡ በይበልጥም ተመካሪው የሚመከር ህሊና፣ ምክርን የሚያደምጥ የአሰላሳይ ሰው ጆሮ እስካለው ድረስ፡፡ የሆኖ ሆኖ ጥሑፉን ‹‹ሕዝቡ ብልጽግናን/ኢሕአዴግ ዘ ተሃድሶን እንዴት መረጠ? ለምን መረጠ?…›› ለሚለው ጥያቄ ደርባባ ምላሽ የመስጠት ፍላጎት ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
፫ኛ፡- ‹‹የባለሥልጣናት ምንጣፎች›› የሚለው ሌላው ጥሑፍ፡፡ ተይህ… ጥሑፍ ለጥቅስ የማበቃው፡- ‹‹በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባልለፉበት ዲግሪ፣ በሌላቸው ችሎታ፣ ባልሠሩበት (ባላካበቱት) ልምድ፣ በባዶ ዕውቀት፣ ያለደረጃቸው እና ያለ ልምዳቸው ተመድበው የሚሠሩ ሰዎች ካጋጠሟችሁ ምንም አትጠራጠሩ፤ እዚያ ተቋም ውስጥ ወይ የዝምድና፣ ወይ የዝሙት፣ ወይ የምላስ፣ ወይ የፖለቲካና የኃይማኖች፣ ወይ የጉቦ፣ ወይ የዘር ምንጣፍ አላቸው›› የሚለውን የጠሐፊውን ትዝብታዊ… ኃይለ-ቃል ነው፡፡
ተያ… ባሻገርስ? ምን ልበል ይሆን? … ‹‹የባለሥልጣናት ምጣፎች›› ለባለሥልጣኖች የሚያጎበድዱትን፣ የመላላክ ጭራ የሚቆሉትን… ብቻ ነጥሎ የሚተች… ወይም በእነሱ እና በእነሱው ላይ ብቻ ልዩ ትኩረት አድርጎ የጠሐፊውን ሐሣብ አስተያየት ወይም የመኖር ትዝብት … የሚያስቃኝ ጥሑፍ ብቻ አይደለም፡፡
ጠለቅ፣ ሰፋ…. ያለ ዕይታ ያለው ነው፡፡ ‹‹ምንጣፎች›› ሲባልም ከሃገረ ኢትዮጵያ እስከ ፐርሺያ … ድረስ የሚታወቁት ስጋጃዎች ወይም የታላላቅ ሳሉኖች ወለል ማስዋቢያዎች … አይደሉም፡፡ የሰው ተረጋጮች፣ የሰው መረማመጃዎች፣ የሰው የየቢሮው፣ የየባለልጣኑና ተራ ሹመኛው ሳሉን መረጋገጫ … ዕቃዎች ናቸው፡፡ የሰው ቁሳቁሶች፡፡ ራሳቸውን እንደ ቁሳቁስ በማድረጋቸው የሚጠቀሙ፣ ከፍ ሲልም የሚከበሩ… የሚመስላቸው የሰው ተዋራጆች… ወይም ውራጆች … መለያዎች ወይም ምሣሌዎች ናቸው ምንጣፎቹ፡፡
‹‹የባለሥልጣናት ምንጣፎች›› የተሰኘውና የጸሐፊው እስክንድር መርሐጽድቅ ተመራቂ መጽሐፍ ዋንኛ ርዕስ ለመሆን የበቃው ጥሑፍ እንደሚነግረን ‹‹ምንጣፎች››፡- የኢትዮጵያውያንን ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሕዝባዊ፣ ኃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ-ሀብታዊ ሂደቶችን ውል-አልባ ልቃቂት ያደረጉት የማኅበረሰባችን አስተሳሰበ አረሞች ናቸው፡፡ ኢና… ይህ ጥሑፍ የጠሐፊው ረቂቅና የሚያስመሰግነውም ዕይታ ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ጸሐፊው የመገናኛ ብዙኃን ሰው ወይም ባልደረባ ሆኖ ሳለ… እሱ ‹‹ምንጣፎች›› ከሚላቸው ወገኖች የሚመደቡ የየመገናኛ ብዙኃኑ ትንሽ ትልቅ የሥራ መደብ ኃላፊዎች ያልፈቀዱ ወይም ያኮረፉ… ከመሆናቸው የተነሳ በመጽሐፉ ምረቃ ዕለት ‹‹ዘጋቢ ጋዜጠኞች›› በተለይም ከመንግሥት ሚዲያ በኩል በትንሽቱ የሃገር ፍቅር አዳራሽ ዝር…ያላሉት፡፡
፬፡- ከ‹‹ብርቄ ሬዲዮ እስከ ፌስ ቡክ…›› የሚለው ጥሑፍ፡፡ ይህ ጥሑፍ በእኔ አመለካከት ሐተታ የጸሐፊው ሥራ ወ ሕይወት ወይም የኑሮ ጥረትና ውጣ-ውረድ… የተንቆረቆረበት ዓይነት ነው፡፡ በመሆኑም ጸሐፊው የሄደባቸውን መንገድ… እየተከተለ የሚያትተውን ነገር አለው፡፡ የመኖር፣ የፍላጎት፣ ጋዜጠኛ የመሆን ሐሣብና ስኬት ጎዳናዎቹን የሚያስቃኝ ጥሑፍ ነው፡፡ ርግጥ ነው ጥሑፉ እንደሚለው የጠሐፊው ጉዞ ጥሩ ነበረ፡፡ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱንም ይሁን ዕልህና ትጋቱን አንፀባራዊ ጥሑፍም ነው፡፡
በዚህ ጥሑፍ ውስጥ በሰንጠረዥ አባሪ አድርጎ ካስቀመጠው፡- ‹‹… ‹አዛውንቱ ማትሪክ ወሳጅ› ፣ ‹ቀይ ሥሮች› እና ‹አይደል?› ›› የተሰኙትን ጥሑፎቹን ከሦስት ወይም ከአንድ ጊዜ በላይ የጣፋቸው ወይም ደግሞ ያሳተማቸው መሆኑን ጠሐፊው ጠቁሞናል፡፡ ዛዲያ እነሱኑ ጨምሮ 257 ጡሁፎችን ወደ አንባቢያን ማድረስ መቻል ቀላል ተግባር ሆኖ አልተሰማኝም፡፡ ተይህ አንጣር… አንጣር በአንጣር ቲታይ ጠሐፊው እስክንድር መርሐጽድቅ በእውነት ብርቱ መሆኑን ማስተባበል አይቻልም፡፡
፭፡- በመጨረሻ… ቁጥር አምስት፡፡ ‹‹የኃይማኖት ገበሬው›› የተሰኘው ጥሑፍ ነው፡፡ ይህ ጥሑፍ በጠሐፊው ወላጅ አባት በካህኑ መርሐጽድቅ ያለፈ… ሕይወት ታሪክ አጭር እና ምጥን ትርክት ዙሪያ ለማጠንጠን የሚሞክር ነው፡፡ ደስ ያሰኛል፣ ያጓጓል እንጂ… ዝርዝር ጉዳይ ስለሚቀረው፣ ሁሉ-አቀፍ ስላልሆነ፣ አጭርና ዕምቅ ስለሆነ… በእውነቱ ጥም ቆራጭ አይደለም፡፡ ወይም ስሜትን ቆስቋሽ ብቻ ነው፡፡ የታሪኩን ቁመትና ግዝፈት… የጸሐፊውን አባት ታላቅነት ያህል ሞገስና ግርማ ያለው አይደለም፡፡
አዎ የጠሐፊው አባት የ‹‹መርሐጽድቅ›› የሕይወት ታሪክ እጅግ አጓጊ ነው፡፡ ግን በጣም ምጥን ነው፡፡ የጠሐፊውን ስስት ጠቋሚ ነው፡፡ ምናልባትም የመተንተን፣ አስፍቶና አብራርቶ፣ አጉልቶና አድምቆ… የማሳየት አቅሙ ውሱን ሆኖ ይሆናል፡፡ ሌላም ምክንያትና ድካም… ሊኖርበት ይችላል፡፡ እሱን ልተወውና … በቀረበው ‹‹የኃይማኖት ገበሬው›› ገጸ-ባሕሪይ አባት ዐመል… ከግፈኞች ወይም መማር ከማይሹ አላዋቂ ሰዎች መደብ የሚያስፈርጃቸው መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
‹‹ጽድቅን ዓይተው ለመመለስ›› የበቁት … የጸሐፊው አባት ‹‹ግንዘት›› የተፈታላቸውና ከሙታን ዓለም ደጃፍ ወደ ሕያዋን ምድር የተመለሱ መሆናቸው የሚደንቅ ብቻ አይደለም፡፡ ተዓምራዊም ነገር ነው፡፡ ገና በማለዳው … በጠዋቱ መገፋት፤ ለባሰ የከፋ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የዕውቀትና የአስተዋይነት ሥለት ለማውጣት የሚበጅም መሆኑን ከማስገንዘቡ አንጻር አስክንድር የአባቱን ታሪክ በጥንጥዬም ደረጃ ቢሆን ማቅረቡ አያስመሰግነውም የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ይኸው ነው! ያሰንብትልኝ!!!