>
5:26 pm - Friday September 15, 1150

የአብይ አሕመድ ምኞትና ቅዠት...!!! (ጌጥዬ ያለው)

የአብይ አሕመድ ምኞትና ቅዠት…!!!

ጌጥዬ ያለው

*….ጃዋርና እስክንድር የሚያደርጉት ጉዞ በ24 ሰዓታት ልዩነት ሲሆን ተነጋግረውና ለተመሳሳይ አላማ ይሁን  አይሁን የታወቀ ነገር የለም። ከዲያስፖራው ገንዘብ ከመሰብሰብ ባሻገር ሁለቱም ተጓዦች ከህወሃት፣ከሸኔ እንዲሁም ሌሎች ፅንፈኛና አክራሪ ቡድኖች የዲያስፖራ ክንፍ ጋር የመገናኘትና የማሴር ስራ ይሰራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከውጭ ሃገራት ሃይሎች ግብፅን ጨምሮ ሊመክሩ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም።። 
ይለናል የጠቅላይ ምኒስትሩ ጽ/ቤት በቃል አቀባዩ ናትናኤል አማካይነት
በጋዜጠኝነት ‘ዜና የታሪክ ረቂቅ ነው’ (News is a raft draft of history) ይባላል። በኦሕዴድ/ብልፅግና ደግሞ የአንድ ተከፋይ አክቲቪስት ሽራፊ ጦማር የገዥው ፓርቲ የነገ አቋም/መግለጫ ቢጋር ነው ቢባል ስህተት አይደለም። ከታች የተቀመጠው ጦማርም የነገው የ4 ኪሎ መግለጫ ፍላጎት ለመሆኑ ጥርጥር የለም። መጠራጠር የምንችለው እውን መግለጫ ሆኖ ይወጣል ወይስ በፍላጎት ብቻ ይቀራል የሚሉ ጥያቄዎች ላይ ነው። ይህንን የሚወስነው ከሕዝብ የሚገኘው ግብረ መልስ ነው። በጦማሩ ሕዝብ ባይደሰትም እንኳን የማይቆጣ ከሆነ መግለጫ ነው፤ ካልሆነ ደግሞ ፍላጎት ሆኖ ይቀራል።
ቆላም ወረደ ደጋ የፕሬዚደንት እስክንድር ነጋ እንቅስቃሴ ለአብይ አሕመድ እንቅልፍ የሚነሳ  ቅዠት መሆኑን ለማረጋገጥ ምሊልክ ቤተ መንግሥት ታዛ ስር መተኛት አይጠበቅብኝም። እንኳንስ ከሀገር ወጥቶ እስክንድር እስክብሪቶ ለመግዛት ሱቅ ቢሄድ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይሸበራል፤ ልቡ ይንቦጀቦጃል።
በናትናኤል መኮንን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ተከፋይ አክቲቪስቶች እየተሰራጨ ባለው ጦማር ቅዠትና ሽብሩ በግላጭ ይታያሉ፦
፩. ‘እስክንድር በዚያው ቢቀርልኝ’ የሚል ከሕልምና ቅዠት ሁሉ የራቀ ምኞት አለ።
፪. የራስን የባንዳነት ባህሪ በመዋስ ‘እስክንድር ከውጭ ሃይሎች ጋር ይገናኝ ይሆን’ የሚል ስጋት ተፈጠሯል።
#እዚህ ላይ እስክንድር ነጋ ከእነ ማን ጋር ተገናኝቶ በምን ጉዳይ እንደሚነጋገር፤ ይህም የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ጥቅምና ፍላጎት ያከበረ እንደሆነ ፈሪዎቹ ጠንቅቀው ያውቁታል። ‘ግብፅ’ የምትለዋለን ማጀቢያ ለጭንቀታቸው አመጡ እንጂ ከእውነቱ 1ዐዐ ሜትር የራቀ መሆኑን እነርሱም አያጡትም።
እስክንድር ግብፅን ከእነ ማህበርተኞቿ የአረብ ሊግን ያወገዘ መሆኑን ልብ ይሏል። ሊጉ በአባይ ግድብ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ሲፈልግ “በእኛ ጉዳይ አይመለከትህም። ከዚህ በፊት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ገብተህ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል አስተዋፅኦ ነበረህ። አሁንም የአረብ ሊግ ተሳትፎ አያስፈልገንም” ያለው እስክንድር እንጂ አብይ አልነበረም። ጠቅላይ ሚንስትሩማ እንዳውም ለሳውዲው ንጉሥ ‘ኢትዮጵያ ሁለተኛ አገርህ ነች’ ሲል ነበር። ዛሬም እያለ ነው።
#ከወያኔና ከኦነግ-ሸኔ ጋር መገናኘት የሚል ሃሳብም ተጠቅሷል። ከእነኝህ ሽብርተኛ ቡድኖች ጋር ለመጨባበጥ እኮ የሚያስፈልገው ባሕር አቋርጦ ከሀገር መውጣት ሳይሆን እምዬ ምኒልክ ቤተ መንግሥት በር ላይ መቆም ነው።
፫. እስክንድርና ጃዋር ባልንጀራ ተደርገው የተገለፁበት ጉዳይ ገራሚ ነው። እዚህ ውስጥ ሁለት ኃሳቦች አሉ። አንደኛ እስክንድርን እንደ ጃዋር ወንጀለኛ የማድረግ ሙከራዎች አሉ። ይህ እየሱስ ክርስቶስን በርባን የማድረግ ሙከራ ሊባል ይችላል። ሁለተኛው ‘እውነትስ እነኝህ ሰዎች አንድነት ቢፈጥሩ ምን ይውጠኛል’ የሚል መብሰክሰክ ነው።
#በተረፈ እስክንድር ገንዘብ እንደሚያሰባስብ ጠቅላይ ሚንስትር ፅህፈት ቤት በነፃ ለሠራው ማስታወቂያ ምስጋና ይገባዋል¡
Filed in: Amharic