>

ገበሬ እንደ በሬ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ገበሬ እንደ በሬ…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

* … ውርደቱ ለእኛ ሀፍረት ለማናውቀው፣ ባንተ ትከሻ ተረማምደን ምቾታችንን ላደላደልነው፣ ፊደል ቆጥረን ለደነቆርነው፣ ለካድንህ ጥራዝ ነጠቅ የቀነጨርን ልሂቃን ነው”
 
የአገሬ ገበሬ ከቅም ቅም አያቶቹ በወረሰው ዘዮ ጥንድ በሬ ጠምዶ በማረስ ዕህል እያመረተ እልፍ አእላፉን ሲቀልብ ኖሯል። ከአንተ ኋላ ግብርናን ትላንት ‘ሀ’ ብለው የጀመሩ አገራት ገበሬዎች ሞፈር ጥለው ዘመናዊነትን ተዋጅተውና ተከብረው መኖር ከጀመሩ ዘመናት ተቆጠረ። በልጆቹ ቀን ያልወጣለት ያአገሬ ገበሬ እሾህና ጋሬጣ ሳይበግረው ባዶ እግሩን እየሄደ፤ የለበሳትን እራፊ ጨርቅ ከአመት አመት እየለበሰ፣ ከአፈርና ድንጋይ ታግሎ እሱ ሳይማር ፊደል ያስቆጠራቸው፣ ቀለም ያጠገባቸው፣ ኮሌጅ በጣሽ ልጆቹ እንደ ይሁዳ ገና በጠዋቱ ክደውት ቀኑን አጨለሙበት። ከበሬና ከሞፈር አስጥለው ያዘምኑኛል ብሎ በልጆቹ የቋጠራት ተስፋ ዛሬ እዚህ ደርሳለች። ጭራሽ በበሬም ማረስ ብርቅ ሆኖ ይኸው በዚህ ፎቶ ላይ እንደሚታዩት ጥማድ በሬዎቹን ድርቅ የፈጀበት የቦረና ገበሬ እራሱን በሬ አደረገ። ሞፈሩን ከጀርባው አድርጎ የሺ አመታቱን የበሬዎቹን ቀንበር እሱ ራሱ ተሸከመ። ከዚህ በላይ ውርደት ምን አለ?
 እየተራበ፣ እየተራቆተ፣ ግብር ከፍሎ  ያስተማራቸው ልጆቹ ትራክተር ገዝተው እሱንም፣ በሬውንም ከዘመናት የግብርና እንፉቅቆሽ አውጥተው፣ ግብርናውን አዘምነው ይገላግሉኛል ብሎ ሲጠብቅ ልላ ክፉ ቀን ከፉቱ ተጋረጠ።
እኛ ጉዶች፤ የበላንበትን ወጪት ሰባሪዎቹ ቀለም ቀመሶች፤ የራሳችንን ደሴት ገንብተን፣ በአርቴፊሻል የድሎት ህይወት ታውረን፤ ያንን የመኖራችን ዋልታና ማገር የሆነውን በሬና አፈር ገፊ ደሀ ገበሬ እረሳነው። አንጀቱን ቋጥሮ  ያስተማራቸው ልሂቃን ልጆቹ  በትራክተር ፋንታ ታንክና መድፍ  ገዝተው ለሥልጣን ሲሻኮቱና እርስ በርስ ሲጫረሱ እሱን ዘነጉት። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በየመንገዱ ግራና ቀኝ ተቃጥለው እና ወድመው የቆሙትን ታንኮችን ሳስብ፤ የአንድ ታንክ ዋጋ ስንት ትራክተሮች ይገዛ ነበር? የሚል ጥያቄም አጫረብኝ።

…. የኛ ነገር እንዲህ ነው። ሰለጠኑ የምንላቸው አገሮች ከ150 አመት በፊት ይጠቀሙበት የነበረውን የባርነት ግብርናን እኛ እንደ ዐዲስ እየተጠቀምንበት ነው። ይህ ከ160,ወይም 90 አመት በፊት የፈረንሳይ ገበሬዎች ከማሊ የወሰዷችን ጥቁር ባሮቻቸውን ጠምደው የሚያርሱበት ቅፅበት እንዳይመስላችሁ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የሚኖሩ አርሶ አደሮች በድርቁ ምክኒያት ያሏቸው በሬዎች ስለሞቱባቸው እራሳቸውን እንደ በሬ ተክተው ሲያርሱ የተነሱት የትናትና ምስል ነው።

ውርደቱ ለእኛ ሀፍረት ለማናውቀው፣ ባንተ ትከሻ ተረማምደን ምቾታችንን ላደላደልነው፣ ፊደል ቆጥረን ለደነቆርነው፣ ለካድንህ ጥራዝ ነጠቅ የቀነጨርን ልሂቃን ነው!!!

Filed in: Amharic