>

ዓለማችን ወዴት እያመራች ነው...???  (አሳፍ ሀይሉ)

ዓለማችን ወዴት እያመራች ነው…??? 

አሳፍ ሀይሉ

 

(ጥቂት እውነቶች፣ መዓት ስሌቶች፣ መዓት ስጋቶች፣ እና አንድ ተስፋ)
የሚዲያዎች ዘመን ያስቆጠረ የአድማጭ-ተመልካች የስነልቦና ጨዋታ አለ። በድግግሞሽ ብዛት ሰሚን የማሳመን ጥበብ።
አንድን ነገር ሺህ ጊዜ ደጋግመህ ስታሳየው፣ የተለመደ የሁሉም ሰው ዕውቀት ይሆናል። ሊከራከርህ የሚፈልገው ልፊያው አድክሞት ይተውሀል። እና እስከመጨረሻዋ እስትንፋስህ በጀመርከው ውሸት ድርቅ ብለህ – ወደፊት! ለዚህ ነው የምናየውን መምረጥ፣ የምናምነውን መጠንቀቅ የግድ ያለን።
ብዙ ጊዜ ዜናዎች ጫፏን ቆንፅለው ስለሚያሳዩን፣ ትክክኛውን የራሺያ እና የዩክሬንን የመጠን (የትልቀት) ልዩነት በተገቢው መጠን እንዳንገነዘበው ያደርጉናል። አረንጓዴዋ ራሺያ ነች፣ ብርትኳናማዋ ደሞ ዩክሬን። ጦርነቱ እንግዲህ በዝሆንና በጥንቸል መሐል ነው እየተካሄደ ያለው ማለት ነው።
ሌላው በሚዲያዎች የሚነገረን ስህተት ደግሞ የራሺያ ወረራ መጠንና ዓይነት ነው። የዓለም ሚዲያ ሁሉ የሚያወራው ራሺያ ዩክሬንን መውረሯንና ማሸነፍ እንዳቃታት ነው።
የዓለም ሚዲያ ይህን የሁሉአቀፍ ወረራ ለማስረዳት በሚያሳየን ካርታዎች ሁሉ ላይ ግን፣ ራሺያኖቹን የምናገኛቸው ዶምባስ ተብሎ በሚታወቀው ምስራቃዊ አቅጣጫ ብቻ ተወስነው ነው።
ራሺያኖቹ ዋና ከተማዋን ኪዬቭን ከበው እያስጨነቁ፣ ምሥራቃዊዎቹን የዶምባስ ግዛቶች ከዩክሬን መዳፍ ፈልቅቀው እያላቀቁ ነው። ዓላማቸው ግቡን የመታ ሲመስላቸው ከኪዬቭ ዙሪያ ውልቅ ብለው ወደ ምሥራቃቸው ፊታቸውን አዙረዋል።
ይህም የሚያሳየን ራሺያኖቹ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ለመውረርና ለመያዝም ሆነ፣ የዩክሬንን የዜሌንስኪ መንግሥት መገርሰስ ዕቅዳቸው እንዳልነበረ ነው።
ቢሆን ኖሮ በሙሉ የሠራዊት ኃይላቸው ትንሿን ጎረቤታቸውን ዩክሬንን አመድ አድርገው ለመቆጣጠር ከጥቂት ቀናት በላይ አይወስድባቸውም። የጥፋቱና የጥቃቱ መጠን መላዋን ዩክሬንን ያጠቃልል ነበር።
እና ዓላማቸው ሁሉንአቀፍ (ሙሉ) ወረራ ቢሆን ኖሮ፣ አሜሪካ በእነ ኢራቅና ሊቢያ ላይ እንዳደረገችው፣ ራሺያም የዩክሬንን ባለሥልጣናትና የቤተሰብ አባሎቻቸውን ዝርዝር በተፈላጊ ወንጀለኝነት አውጥታ በተገኙበት እያሳደደች ስትገድላቸው፣ በእነ ዜሌኒስኪ ቤተመንግሥት ላይ ሚሳይል ስታስወነጭፍባቸው፣ የሞቱና በስቅላት የተቀጡ ሚኒስትሮችን በየሚዲያው ስትለቅልን፣ እና ሌሎችንም ዘግናኝ ኢራቃዊ ድራማዎች በዩክሬን እናይ ነበር።
የራሺያኖቹ ዓላማ ግን ይህ እንዳልሆነ በግልፅ መገንዘብ ይቻላል። ከሚዲያው ጋጋታ ራሱን ጋብ አድርጎ እንቅስቃሴያቸውን ልብ ያለ ሁሉ በቀላሉ እንደሚረዳው፣ ዓላማቸው ሶስት ነው።
አንድ፦ ኖቮሮሺያ እየተባለ የሚጠራውንና ራሺያኖች በታሪክ የኛ ነው ይገባናል የሚሉትን (ዶምባስንና ውስጡ ያሉትን ሉጋንስክና ዶኔትስክን የሚያጠቃልለውን) መጠቅለል ነው፣
ሁለት፦ የዩክሬንን ወታደራዊ አቅም ማንኮታኮትና ከጥቅም ውጭ ማድረግ፣ እና ዩክሬንን በጉልበት አስገድዶ ለራሺያም ሆነ አሊያም በአዲስ ሀገርነት ስም ራሺያን ደግፈው ለቆሙት የዶምባስ ግዛቶቿን ቆርሳ እንድትሰጥ ለማድረግ ነው፣
ሶስተኛው፦ እና የመጨረሻው ግብ ደግሞ በአሜሪካኖች የሚመራውን የኔቶ ኃይል የመጨረሻ ቀይመስመሩ ከፖላንድ እንደማያልፍ በማያወላዳ ቋንቋ ማስረዳት ነው።
አውሮፓውያን ከአሜሪካና ኔቶ ጋር ተማምለው ወደራሺያ ከዚህ በላይ ከገፉ አውሮፓ ዳግመኛ የመጨረሻውን ዘግናኝ የሰውልጆች እልቂት የምታስተናግድ ምድረበዳ እንደምትሆንና ለዚያም ራሺያኖች ሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን በማይታበል ዐግናኝ የአረር ቋንቋ ማስረዳት ነው የመጨረሻው ዓላማ።
የዚህ ሁሉ ፋይዳው ምንድነው? የራሺያ ተከታታይ ወታደራዊ እርምጃዎች ዋና ማጠቃለያ ግብ፣ የቀዝቃዛው ጦርነትን ማክተም ተከትሎ በዓለም የሰፈነው በአሜሪካ የበላይ አዛዥነት የሚዘወረው የዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተዳደር የማብቃቱን እውነት ለዓለም (በተለይም ለራሳቸው ለአሜሪካኖችና የምዕራቡ ዓለም አጋሮቻቸው በሚገባ የተግባር ቋንቋ) ማረጋገጥ ነው።
ይህስ ራሱ ምን ፋይዳ አለው? ትልቅ ፋይዳ አለው። በዓለማችን ላይ አዲስ የኃይል አሰላለፍና፣ አዲስ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ምዕራፍ ያስከትላል።
ለምሳሌ አሜሪካ ከራሺያኖችና ቻይኖች ጋር የዓለምን ንፍቀክበብ በመከባበርና በሠላም ተከፋፍላ ለመጓዝ እስካልቻለች ድረስ፣ እየመጣባት ያለው አደጋ ወለል ብሎ እየተገለፀላት ይመጣል።
ነገሮች ገፍተው ገፍተው ወደጦርነት እሳት ለመግባት የሚገፉ ከሆነ፣ አሜሪካ ወይ ጨክና ለመዋጋት ወይ ለማፈግፈግ ትገደዳለች። በሰው አህጉር ውቅያኖስ ተሻግሮ መዋጋትና አሸንፋለሁ፣ አተርፋለሁ ብሎ መጠበቅ፣ በሕልምም የማይታሰብ ቅብጠት ይሆንባታል።
ስለዚህ ከአውሮፓና ከእስያ ያሏትን ግዙፍ ወታደራዊ ኃይሎች ለመሰብሰብ መገደዷ አይቀርም። አሜሪካ የረባ ጥቅም ለማታስገኝላት ታይዋን ስትል፣ ውቅያኖስ ተሻግራ ጦሯን እያጓጓዘች ከቻይና ጋር አትዋጋም።
የፖላንድና ሮማንያ ስደተኞች አማረሩኝ ብላ ራሷን ከአውሮፓ ህብረት ነፃ የዝውውር ቀጣና ያገለለችው እንግሊዝ፣ ለሮማንያና ፖላንድ፣ ወይ ለዩክሬንና ፊንላንድ፣ ወይ ለታይዋንና ደቡብ ኮርያ ብላ፣ ከራሺያና ቻይኖች ወይ ከኢራኖችና ሰሜን ኮርያዎች ጋር ሕዝቧን ወደጦርነት መማገድ አትፈልግም።
የሌላውም የዓለም ሀገር ቀመር ተመሣሣይ ነው። በማይመለከተው የሰው ሀገርና ምድር ጉዳይ ተንደርድሮ ጥልቅ ብሎ፣ እንደ ቻይናና ራሺያ ከመሠሉ ግዙፍ ባለኒውክሊየር ሀገራት ጋር ጦር መማዘዝና፣ ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቆ ራሱን ማግኘት ማንም አይፈልግም።
ስለዚህ ለእነ አሜሪካ የሚቀሯቸው ሶስት አማራጮች ብቻ ይሆናሉ፦
አንድም) ጦራቸውን የበለጠ ማፈርጠም፣ ወደ አውሮፓና ኢንዶቻይና ማጓጓዝና ዳግም የቀዝቃዛውን ጦርነት ዘመኑን የመሠለ የማያበቃ የዓመታት ወታደራዊ ፍጥጫ መጀመር፣ እና ዓለምንና ኢኮኖሚዋን ሁለት ቦታ የመክፈል አማራጭ አላቸው፣
ሁለትም) ከቻይና፣ ራሺያ፣ ሰሜን ኮርያና ኢራንን ከመሣሠሉት የተነጠሉ ግዙፍ ኃይሎች ጋር፣ እነ ህንድን፣ ቱርክንና ፓኪስታኖችን ሁሉ ጨምረው፣ የምሥራቃዊውን ንፍቀክበብ እንዳሻቸው እንዲያስተዳድሩ ነፃ ለመልቀቅ የሆነ የጋራ ስምምነት አድርገው፣ የጦር እንቅስቃሴያቸውን የማቆምና የመቀነስ፣ የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን ግን ያለገደብ የመቀጠል የተሻለና በረዥም ርቀት ለሁሉም የሚበጅ አማራጭ አላቸው፣ አሊያ
ሶስትም) የመጣው ይምጣብን ብለው፣ ካልደፈረሰ አይጠራም ብለው፣ ያለ የሌለ ወታደራዊና ቴክኖሎጂያዊ ኃይላቸውን አስተባብረው፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለሚደረግ የዓለምን ኢኮኖሚና አንፃራዊ ሠላም እንክትክቱን ወደሚያወጣ የጦር ቃልኪዳንን በመገባባትና በማክበር የተነሳ ወደሚከተል ዘግናኝ የዓለም ጦርነት ውስጥ ሰተት ብሎ መግባት፣ እና የማሸነፍ እድላቸውን መሞከር ነው።
ቀንቷቸው ይሄን ሶስተኛውን ቁማር ቢጠቀልሉት እንኳ፣ የዓለምን አንድ ሶስተኛውን ሕዝብና መሠረተልማት ሳያወድሙ የሚቻል አይሆንም። የወደመ ዓለምን ታቅፎ ማሸነፍ ምን ያደርጋል?
ምንም እንደማያደርግ ሁሉም ሲገባው፣ ሁሉም ወደ ድርድርና ወደሚያግባባ የስምምነት ጠረጴዛ ይመጣል። ብለን ተስፋ እናሳድር።
አሊያ ረብሻውን ማንም አይቋቋመውም። አሜሪካ ለጃፓኖች፣ ለደቡብ ኮርያዎች፣ ለታይዋኖች፣ ለአረቦች፣ ለታይዋኖች ኒውክሊየር ያስታጥቃሉ። ቻይናዎች በዙሪያቸው በቅርብም በሩቅም ላሉ ሸሪኮቻቸው ኒውክሊየር ያስታጥቃሉ።
ራሺያኖች ከኢራን እስከ ሶርያ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ቬንዙዌላ ዓለሙን በኒውክሊየር ያንበሸብሹታል።
ለታሊባኖችና ለተለያዩ አሜሪካን ከሠይጣን ከራሱ አስበልጠው ለሚጠሉ አሸባሪዎችም ቀላላል የኒውክሊየር፣ የባዮሎጂካልና ኬሚካል መሣሪያዎችን በችርቻሮ ወደመቸብቸብ ሊገቡም ይችላሉ።
አሜሪካ አሁን የምታስታጥቀው ለራሺያ ጠላቶች አይደለ? ታዲያ በራሺያ ቦታ ሆነን ካየነው፣ እሷስ ለአሜሪካ ጠላቶች ያላትን ብታሽራቸው ምን ችግር አለው?
ይሄ የእኔ እሳት ካንተ እሳት ይበልጣል የጥፋት እሽቅድምድምና የአውዳሚነት ፉክክር፣ በመጨረሻ ዓለማችንን በጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎችና በኒውክሊየር አረሮች በማጥለቅለቅ መጠናቀቁ አይቀርም።
የመሬቱ አልቆብን የሳይበርና የስፔስ ንፍቀክበባት ጦርነቶችንም ልናይ እንችል ይሆናል። ከተረፍን። እና ዕድሜ ከሰጠን ነው እሱም።
ሁሉም ባለአረሮች፣ ሁሉም ባላንጦች፣ ሁሉም የደምና የፖለቲካ ነጋዴዎች፣ መሣሪያ መማዘዙንና መፋጠጡን ለማስቀረት ወደአንድ የጋራ የሠላም ስምምነት ካልመጡ፣ የዓለም መጨረሻ፣ ዋይታና ጥርስ ማፋጨት ብቻ ነው። ሌላ መንገድም፣ ሌላ መጨረሻም የለም።
ስጋቶቻችን ሺህ ናቸው። ስሌቶቻችን ሚሊዮን ናቸው። ከፊታችን የተደቀኑት ጥፋቶች እንደ ባህር አሸዋ የበዙ ናቸው።
ምድር የምታርርበት፣ ጨረቃችን የምትወድቅበት፣ ከዋክብት የሚረግፉበት፣ ጥቂት በሀብት የመነጠቁ ሀብታሞች ብቻ (ኤለን መስኮችና ቢል ጌትሶች) ወደ ማርስ የሚያመልጡበት፣ እና እኛ የዓለም ጭቁኖች ባልለኮስነው እሳት የምንንገበገብበት አስፈሪ “የኒውክሊየር ነፋሪት” ዘመን፣ በያቅጣጫው ከፊታችን ወለል ብሎ ተዘርግቶብናል።
ተስፋችን አንድና አንድ ብቻ ነው። ሠላም። ብቻ።
የሰው ልጅ ሊያተርፍ የሚችለው ከሠላምና ከስምምነት ብቻ ነው።
ፈጣሪ ከክፉ ይሰውረን።
አለበለዚያ ግን ግልግል ነው።
መዓቴን አበቃሁ።
Filed in: Amharic