>
5:13 pm - Friday April 19, 2165

በአዲስ አበባ ት/ቤቶች ኦሮምኛን በግዳጅ የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ግጭት እየፈጠረ ነው...!!! (ባልደራስ)

በአዲስ አበባ ት/ቤቶች ኦሮምኛን በግዳጅ የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ግጭት እየፈጠረ ነው…!!!
ባልደራስ

በአዲስ አበባ  ከተማ የተለያዩ መንግሥታዊ ትምህርት ቤቶች ከመምህራን፣ ከተማሪዎች እና ከወላጆች ፈቃድ ውጭ በግዳጅ የኦሮምኛ ቋንቋን የማስተማሪያና የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ግጭቶች እየፈጠሩ ናቸው።
 ግጭቱ በተለይም በአዲስ አበባ ዳርቻ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ቀደም ብሎ የተጀመረና እየተባባሰ የመጣ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ ወደ መሀል አዲስ አበባ ትምህርት ቤቶችም ተስፋፍቷል።
እንደ ምንጮች ገለፃ፣ የግጭቱ ምንጭ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማን በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰቅለው በማውለበለባቸው እና  በሌሎች ትምህርት ቤቶች ደግም ለመስቀል ሙከራ በማድረጋቸው ነው።  ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙር ውጭ የአዲስ አበባ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን የማያውቁትን መዝሙር በኦሮምኛ የሚዘመረው እና ለመዘመር የሚደረገው ሙከራም ተቃውሞ እየገጠመው ነው። እንደሚታወቀው፣ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማም ሆነ የክልሉ መዝሙር በብዙሃኑ የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም።ከኢትዮጰያ ውጭ ባለው የኦሮሞ ዳያስፖራ ዘንድ የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ እንደ ክህደት አርማ ስለሚታይ ፈፅሞ አይለወለብም፣ የክልሉ መዝሙርም ጨርሶ አይታወቅም።
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ፣ በእነ ወ/ሮ አዳነች እና ሽመልስ አብዲሳ ቅንጅት የተጀመረውንና ብዙሃኑን ኦሮሞ የማይወክለውን እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ያመች ዘንድ፣ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ከሚገኙ የኦሮሞ መስተዳድር ከተሞች ተማሪዎችን በግዳጅ እና በጥቅማ ጥቅም በመደለል ወደ አዲስ አበባ ማምጣት ተጀምሯል።
Filed in: Amharic