ጎንደር ፍትሕ ትፈልጋለች!
ጌታቸው ሽፈራው
“… ነውር በነውር አይፈታም!
*… የግጭት ነጋዴዎች ተው ሊባሉ ይገባል!
ትናንት የተጎዱት የአንድ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። ከምንም በላይ ለጎንደር ለአማራ ይቀርባሉ። ስለሆነም:_
የተፈጠረው ነገር ከፍተኛ ጥንቃቄና አስተውሎት ይጠይቃል! ከስር መሰረቱ የተጠና መፍትሔ፣ ፍትሕም ይፈልጋል።
1) ፖለቲካው እጅ በዝቶበታል። ሕዝብን ከብሔር አልፎ በእምነት ለማጋጨት ቀን ከሌት የሚሰሩ ሞልተዋል። የአማራውን የውስጥ አንድነት ለመናድ የሚጥሩ ተበራክተዋል። ይህ ሁሉ በሆነበት አንድ ጉዳይ ሲከሰት ሮጦ ከማጯጯህ ባለፈ ከበስተጀርባ ያሉትን፣ ሕዝብን ለመከፋፈል የመጡትን ማጤን ያስፈልጋል። ጥንቃቄና አስተውሎት ያስፈልጋል።
2) የጎንደር ክርስትያን የሙስሊሙን መስገጃ አፅድቆ፣ የጎንደር ሙስሊም የክርስትያኑን መስቀል በዓል መዋያ አሳምሮ አብሮ የሚኖር ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር የሚያደርጉ በሙሉ የጋራ ጠላቶች ናቸው። እምነት ያለው አካል እምነት ለይቶ አያጠቃም። ጥቃት የሚፈፅም የፖለቲካ አላማ ያለው ነው። እምነትን የፖለቲካ አላማ አድርጎ የሚመጣ ካለ የሁሉም እምነት ጠላት ነው። ጉዳዪ እስኪጣራ ማንም ይሁን ተንኳሹ፣ ምንም ይሁን ሴረኛው፣ ምንም ይሁን ከበስተጀርባ ያለው በስክነት መመልከት፣ በጋራ ማጥራት ግዴታ ነው። ለሰላም ፈላጊው ሁሉ።
3) ይህን ሰበብ አድርገው ግጭት ለመፍጠር፣ ጉዳዩን ለማባባስ የሚጥሩት አካላት ላይ መንግስት ብቻ ሳይሆን ከተማውን የሚወድ ነዋሪ በሙሉ፣ ክርስትያን ሙስሊሙ በአንድነት ማጋለጥ፣ ለሕግ ማቅረብ ይጠበቅበታል።
4) መንግስት አንድ ጉዳይ ሲፈጠር ከላይ ከላይ እያየ እሳት ለማጥፋት ከሚጥር ዋናዎቹን የችግሮቹን ምንጭ ይመርምር። ለምን ይህ ይፈጠራል? እነማን ፈጠሩት? ለምን? ይበል። እያንዳንዱን ነጠብጣብ ይመልከት። ለይስሙላህ ብቻ ከሚደረጉ መፍትሄዎች ወጥቶ ጉዳዮች ከስር መሰረታቸው ይታዩ።
በዚህ ጉዳይ ተሳታፊ የሆኑት በእምነት የሚወከሉ አይደሉም። የሁላችንም ጠላቶች ናቸው። በእምነት ስም ይነግዱ፣ ተገዝተውም ይሁን፣ ተዘጋጅተውም ይሁን እምነትን አያገለግሉም። አማኞችም አይደሉም።
የተጎዱት ፍትሕ የሚያገኙት፣ ከተማና ሕዝብ ሰላም የሚያገኙት ይህን ወንጀል ከስር ከመሰረቱ እነማን ሰሩት፣ ማን ከበስተጀርባው አለ ተብሎ ሲወጣ፣ ዋና ድርጊት አድራጊው ለሕግ ሲቀርብ ነው። የተጎዱት ንፁሃን ብቻ አይደሉም። ጎንደር ፍትሕ ትፈልጋለች። አማራው ፍትሕ ይፈልጋል። የእምነት ግጭት እየተጠነሰሰባት ያለችው ኢትዮጰያ ፍትሕ ትፈልጋለች።
የፌደራል መንግስቱ፣ የክልሉ መንግስት፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር መሰል ውስብስብ ችግሮችን ከኋላ ያቀፈ ወንጀልን ለማምከን፣ የወደፊት ችግርን ለማስቀረት የሚያችል ስራ መስራት አለባቸው። ለሕዝብ ከሰለቸ ድብታና መፋዘዝ ወጥተው ለሕዝባችን ፍትሕ መስጠት አለባቸው። ጎንደር የሆነው ለጠላት ማሳያ ነው። ይህን እሳት በቶሎ ማጥፋት ያስፈልጋል። የፌደራል መንግስቱ በመሰል ጉዳይ ላይ መረጃ አጥቶ አይደለም። ሆኖም ጉዳዮችን በቅርብ አዳሪነት ሲመለከት ሕዝብ እየተጎዳ ነው።የአማራ ክልል መንግስትና የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከልክ ባለፈ መፋዘዝ ሕዝብን ዋጋ እያስከፈለ ነው።
ነውር በነውር አይፈታም!
ትናንት የተጎዱት የአንድ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። ከምንም በላይ ለጎንደር ለአማራ ይቀርባሉ። ስለሆነም:_
የጎንደር ከተማ ሕዝብ ችግር ሲፈጥር ያየውን በእምነት ይምሰለው አይምሰለው፣ ይዘመደው አይዘመደው አሳልፎ ለሕግ መስጠት አለበት። ነገ ራሱን የሚያስጎዳው እንዲህ አይነት ነውረኛ ነው። በትናንቱ ችግር ሙስሊም ክርስትያኖች ተጎድተዋል። ጎንደር እንደ ከተማ ተጎድታለች። ስለሆነም የትኛውንም ነውረኛ ለሕግ አሳልፎ መስጠት ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ግን ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ፖለቲካ ለመስራት የተዘጋጀ ኃይል እጁን ቢሰበስብ ይሻለዋል! ትህነግ ደረሳዎችን ሲጨፈጭፍ አንድም ቃል፣ አንድም ቃል ትንፍሽ ያላለ በአማራ ክልል፣ በጎንደር ከተማ ሲሆን ለማባባስ የሚሰራ የፖለቲካ ነጋዴ ተው ማለት ያስፈልጋል። በትህነግ መስጊዶች ሲቃጠሉ፣ ቅዱስ ቁራን ሲቀደድና መፀዳጃ ሲያደርጉት፣ ሸኮችን በግዳጅ አልኮል ሲያስጠጡ፣ መስጊድ ውስጥ ሴቶችን ሲደፍሩ፣ መስጊድ ውስጥ መጠጥ ይዘው ሲጨፍሩ ሲያድሩ እያወቀ አንድም ነገር ትንፍሽ ያላለ አሁን ወንድማማቾች መካከል የተፈጠረንና ጎንደር የምትፈታውን ጉዳይ አጋጣሚ ተጠቅሞ ለማጦዝ የሚጥፈው እረፍ ሊባል ይገባዋል። ወንጀሉን የሚያባብስ፣ ከወንጀሉ በላይ ነውረኛ ነው።
አማራን የሚጠሉ፣ ወሎንና ሸዋን አውድመው፣ ጎንደርን አውድመን ወደ ጎጃም አልፈን እናወድማለን እያሉ እየተዘጋጁ ያሉት የትህነግ ካድሬዎች ጋር ሆኖ ማጯጯህ ተቀባይነት የለውም። ነውርን ማውገዝ አንድ ነገር ነው። ነውርን ግን በነውር መፍታት አይቻልም። በአንድ ቦታ 40 ሺህ ሙስሊም ያረደውን ዮሃንስን ፎቶ አንጠልጥለው ጎንደርን ለመውጋት ከቋመጡት ጋር አጀንዳ እየተጋሩ ሌላ ነውር ላይ መጠመድ ችግሩን አይፈታውም።
ነውርን ማውገዝ፣ ነውረኞችን ለሕግ ማቅረብ የጎንደር ከተማ፣ የአማራው ግዴታ ነው። ነገር ግን በሌሎች አካባቢዎች መሰል ችግሮች ሲፈፀሙ ዝም ብሎ የሚያሳልፍና የሚመራ ኃይል አማራ ክልል ሲሆን ጉዳዪን እያጦዘ አጀንዳ ማድረጉ የተለመደ ነው። አማራ ክልልንና አማራ ሙስሊሞችን ነዳጅ አድርጎ የቡድንና የግል ትግሉን ለማጧጧፍ በሚደረግ ነውረኝነት ችግሩ አይፈታም። እረፉ መባል አለበት። ጎንደር ወንጀለኞችን ለሕግ አቅርባ ችግሯን ትፈታለች። አማራው ወንጀለኛን አጋልጦ አብሮነቱን በሚገባ ያስቀጥላል። ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ በአማራው መሃል ችግር ፈጥሮ የራሱን አላማ አራምዳለሁ የሚለውን ደግሞ ይጋፈጠዋል።
የግጭት ነጋዴዎች ተው ሊባሉ ይገባል!
የግጭት ነጋዴዎች አማራ ላይ ሲሆን ሙስሊም ቢሞት ትርፋቸው ነው። አጀንዳ ካገኙ ደስታቸው ነው። አማራን፣ ጎንደርን ሰበብ ፈልገው ሲያወግዙ የከረሙ የግጭት ነጋዴዎች ሰበብ አገኘን ብለው ውግዘታቸውን ቀጥለዋል። በሀሰት ፎቶ ጭምር አጀንዳቸውን ቀጥለዋል።
ለአብነት ያህል ከስር የሚታየው የተቃጠለ ቅዱስ ቁርዓን ከሶስት አመት በፊት ፌስቡክ ላይ ሲዘዋወር የነበረ ነው። ጉዳዩን ለማጦዝ ብለው የሀሰት ምስል እያመጡ ሳይቀር ተጨማሪ ግጭት እንዲፈጠር እየሰሩ ነው። እነዚህ የሀሰት አጀንዳ ይዘው፣ ግጭት የሚነግዱ ክፉዎች አጋጣሚ ተጠቅመው፣ በሚጠሏቸው የአማራ ሙስሊሞች መረማመዳቸውን ማቆም አለባቸው።