የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም ሁሉም ሰው ስለሰላም ያወራል ነገር ግን በጀርባ በሴራ ሲንቀሳቀስ እየታየ ነው ብለዋል።
ጎንደር ላይ የተፈጠረው ጉዳይ ሄደን ባንመለከተውም ባጣም አዝነናል፤ ተበሳጭተናልም ነው ያሉት፡፡
የችግሩ ምንጭ ማን ነው ማንስ ጀመረው የሚለውን አጣሪ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ አካባቢው በመላክ እናጣራለን ሲሉም ተናግረዋል።
በጎንደር በተፈጠረው ችግር የሰው ህይወት እስከሚጠፋ፣ የእምነት ቦታ እስኪወድም አንዲሁም ንብረት እስኪቃጠል ድረስ የአካባቢው አስተዳደርና የክልል መንግሥት የፀጥታ አካላት ተግባራቸውን አልተወጡም ብለዋል፡፡
መጀመሪያ ችግር ሲፈጠር ማሥቆም ባለመቻላቸው ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ አሁንም ለመፍትሄው ሊሰሩ እንደሚገባና አጥፊዎች ላይ የማያዳግም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡
እንዲህ አይነት ችግር ለክርስትናም ሆነ ለእስልምና ሃይማኖት የማይጠቅም በመሆኑ ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለአብሮነት በጋራ መቆም አለብን ብለዋል፡፡