>

የምርጫ ቦርድ የአገዛዙን ሴራ እያሳለጠ ነው!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የምርጫ ቦርድ የአገዛዙን ሴራ እያሳለጠ ነው!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ትናንትና አመሻሽ ላይ የብዙኃን መገናኛዎች ይሄንን ዜና ይዘው ወጥተው ነበር፦ 
“ምርጫ ቦርድ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ባካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ በሕጉ መሠረት የተካሔደ መሆኑን ለመወሰን የሚያስችሉ ሰነዶችን አሟልቶ እንዳላቀረበ ለፓርቲው በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል። ፓርቲው ከሚያዝያ 24 በፊት 8 ተጨማሪ ሰነዶችን እንዲያቀርብ ቦርዱ አዟል። ፓርቲው እንዲያቀርብ ከታዘዘው ሰነዶች መካከል፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የተጠቆሙበት መንገድ፣ እነማን እንደተጠቆሙ እና ተጠቋሚ ዕጩዎች በስንት ድምፅ እንደተመረጡ የሚገልጽ ሰነድ እንዲሁም ጠቅላላ ጉባኤው የተካሔደበትን የሥነ ሥርዓት ደንብ ማን እንዳጸደቀው የሚገልጽ ማብራሪያ እንዲያቀርብ የሚሉት ይገኝበታል” የሚል ነበር ዜናው!!!
ምርጫ ቦርድ ተብየው ብልጽግናን ሕጋዊ ሒደቶችን ሳይፈጽም ማለትም በጠቅላላ ጉባኤ ምሥረታውን ሳያከናውን፣ መተዳደሪያ ደንብ ሳያጸድቅ፣ የፓርቲውን ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ሳያስመርጥ ወዘተረፈ. ለምርጫ እንዲቀርብ ወይም እንዲወዳደርና ተወዳድሮም እጅግ አስቂኝ በሆነ ብቻውን እሮጦ የማሸነፍ አፈና እና የማጭበርበር መንገድ “አሸነፍኩ!” ብሎ እንዲያውጅ ያደረገ የአገዛዙ ቅጥረኛ መሆኑን የረሱ ባለ አጭር ትውስታ ወይም short memory የዋሃን ወገኖች ይሄንን ዜና ሲሰሙ የምርጫ ቦርድ ይሄንን ደብዳቤ ለአገዛዙ የላከው ኃላፊነቱን ለመወጣት ቆርጦ መስሏቸው “እንዴ ምርጫ ቦርድን ምን አጀገነው?” ሲሉ ተደምጠዋል!!!
የልቅስ “ለመሆኑ ከላይ የገለጽኩላቹህን አሳፋሪ ውንብድናዎችን በግልጽ በመፈጸም ብልጽግና ተብየውን ሕገወጥ ፓርቲ ያወዳደረ ወንጀለኛው የምርጫ ቦርድ አሁን በድንገት ኃላፊነት የሚሰማውና ሥራውን በትክክል የሚሠራ ተቋም መስሎ በመቅረብ ሆን ተብሎ እንዲጨመላለቅና መጨመላለቁንም ሕዝብ እንዲያውቅ ሆን ተብሎ በአገዛዙ ሚዲያዎች ጉባኤውን የቀጥታ ስርጭት በማስመሰል ያስተላለፉትን የብልጽግና ተብየውን የተጨመላለቀ ጠቅላላ ጉባኤ ውድቅ ሊያደርግ ወይም ሊያሰርዝ የሚያስችሉ ጠንካራና አፋጣጭ ጥያቄዎችን አስይዞ እንዴት ደብዳቤ ሊጽፍለት ቻለ? የዚህ ሁሉ የተወናበደ ተግባር ዓላማው ምንድን ነው?” በሉና ጠይቁ!!!
የዚህ ሁሉ ሴራ ዓላማው ምን መሰላቹህ በየሁነቶቹ ደጋግሜ እንደነገርኳቹህ የወያኔ ቅጥረኞች እነ አቶ አቢይ አሕመድ ሆን ብለው ሕዝብ እንዲያውቅ እያደረጉ ብልጽግናን ሕገወጥ ሆኖ ምርጫ እንዲወዳደር ያደረጉት፣ ምርጫው የመጨረሻውን የምርጫ መስፈርት እንኳ ጨርሶ ባላሟላ መልኩ በጣም አስቂኝ በሆነ ሁኔታ መጭበርበርና ለነጻ ፉክክር ዕድል ያልሰጠ እንዲሆን ተደርጎ “ብልጽግና አሸነፈ!” እንዲባል ያደረጉት፣ አሁንም እንደገና የብልጽግና ጠቅላላ ጉባኤ በጣም አስቂኝ በሆነ ሁኔታ የምርጫ ቦርድን የፓርቲዎች ማቋቋሚያና ማደራጃ ሕግና ደንብ በእጅጉ በጣሰ መልኩ መፈጸሙ ወዘተረፈ. የሚያሳያቹህ ነገር የሆነ ወቅት ላይ በእነዚህ ዓይን ያወጡ ሕገወጥ ክንውኖች ላይ ጥያቄ እንዲነሣና ውድቅ እንዲደረጉ ወይም እንዲሰረዙ ለማድረግ እየሠሩ ወይም እያመቻቹ መሆኑን ነው!!!
ጥያቄው ለመቸ እና ለምን የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ከዚህ ቀደም ደጋግሜ ለመግለጥ እንደሞከርኩት የወያኔ ቅጥረኞች እነ አቶ አቢይ አሕመድ እነኝህን ሁነቶች ሆን ብለው ሕዝብ እንዲያውቅ እያደረጉ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሚያስኬዷቸው ለአራት ዓመታት ወያኔ/ኢሕአዴግ ለሁለት የተከፈለና የተጣላ መስሎ ሲተውንብን የቆየውን ድራማ በድርድርና እርቅ ስም ሲያጠናቅቅ በአራት ዓመቱ ውስጥ የተፈጸሙ ሁነቶችን በሙሉ ውድቅ በማድረግ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ እንዲያመች ለማድረግ ነው!!!
“አይደለም!” የሚል ሰው ካለ ብልጽግና ተብየውን “በራሱ ጊዜ ተቀባይነት ለማጣትና ወንጀለኛ ለመባል በራሱ ላይ እያሴረ ነው!” የሚል የሞኝ ሐሳብ እያሰበ መሆኑን ይወቅ!!!
Filed in: Amharic