>

ፖሊስ ቢንያም ታደሰን ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ከሰሰ...!!! (ጌጥዬ ያለው)

ፖሊስ ቢንያም ታደሰን ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ከሰሰ…!!!

ጌጥዬ ያለው


ፍርድ ቤቱ ለግንቦት ዘጠኝ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል!

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አባል የሆነው ወጣት ቢንያም  ታደሰ ካለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ ይገኛል።

ወጣቱ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዚያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርቧል። መርማሪ ፖሊስ “የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለማሰባሰብ” በሚል ሰበብ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ሙሉ በሙሉ ተቀብሎት ለፊታችን ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ለረፋድ 3፡30 ቀጥሮል።

የቢንያም ታደሰ ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 13 መሰረት የዋስትና መብቱ ተጠብቆለት ቢንያም ከእስር እንዲፈታ ቢጠይቁም፣ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።

ፖሊስ በአቀረበው ክስ፣በ22/08/2014 በአዲስ አበባ ፒያሳ ሲንማ አምፒር አካባቢ ቢንያም ‘ኦርቶዶክስ ተነስ’ እያለ በጎንደር የተፈጠረውን ግጭት መሰረት አድርጎ ሕዝብ ሲቀሰቅስ እንደነበር ቢገልፅም፣ ተፈጠረ ያለውን ሁከትና ብጥብጥ ማስረዳት አልቻለም። የደረሰ ጉዳት እንዳለ በጠበቃው ሲጠየቅም፣ ቢንያም በእስር ቤት ሆኖ ትናንት በኢድ አልፈጥር በዓል ላይ የደረሰውን የንብረት ጉዳት ጠቅሷል። ጠበቃ ሔኖክ በበኩላቸው፣ በዚህ ዕለት ቢንያም እስር ቤት ውስጥ በመሆኑ ማስረጃ ሊሰበሰብበት እንደማይገባ ገልፀው ተከራክረዋል።

ቢንያም ታደሰ በበኩሉ፣ በዕለቱ በአዲስ አበባ እንኳንስ ብጥብጥ ሊፈጥር ቀርቶ፣ ወደ ናዝሬት ከተማ ለመሄድ መኪና ውስጥ ሲገባ ፖሊስ እንደያዘው አስረድቷል። በቅስቡ ከእስር ቤት በመውጣቱ ገና ውጭውን በመለማመድ ላይ እንደነበር እንጂ፣ ለቅስቀሳ የሚያስችለው ሁኔታ ላይ እንዳልነበርም ተናግሯል።

Filed in: Amharic