>

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ እንደገቡ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር ትክክለኛ [Original] ቅጂ   (አቻምየለህ ታምሩ) 

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ እንደገቡ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር ትክክለኛ [Original] ቅጂ  
አቻምየለህ ታምሩ 

በኢትዮጵያ አርበኞች ብርታትና ተጋድሎ በዋና ከተማችን ተሰቅሎ  የነበረው የጣሊያን ባንዲራ  ወርዶ ለአምስት ዓመታት ወድቆ  የነበረው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ-መንግሥት በግርማዊ ቀዳማዊ  ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ  ተሰቅሎ ከፍ ብሎ  የተውለበለበው  ከ80 ዓመታት በፊት በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ አስራ አንድ ሰዓት ላይ ነበር።
ሚያዝያ 27 የንጉሥ ነገሥቱ አዲስ አበባ ገብቶ ሰንደቅ ዓለማ መስቀል ታሪካዊ እንደምታና ግጥምጥሞሽ ነበረው። ሚያዚያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. ፋሽስት ጥሊያን የኢትዮጵያን ዋና ከተማ ተቆጣጥሮ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ተሰቅሎ ይውለበለብ የነበረውን አድዋ ላይ ከፍ ብሎ የተውለበለበ የኢትዮጵያ ጀግና አርበኞች ሰንደቅ አላማ በማውረድ የጥሊያንን ሰንደቅ አላማ ሰቅሎ የኢትዮጵያ የኢጣሊያ ኢስት አፍሪካ ግዛት አካል መሆኗን በኦፊሴል ያበሰረበት እለት ነበር።
የጥሊያንን ባንዲራ ባዲስ አበባው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የሰቀለው ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ ነበር። ይህ በሆነ ልክ በአምስት አመቱ ነበር ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወድቆ የነበረውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በቤተ መንግሥታቸው በመስቀል የኢትዮጵያን መንግሥት መልሶ መቋቋም ለአለም ያበሰሩት።
ለመላው አለም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባደረጉት  ታሪካዊ ንግግርም
“…Even in the 20th Century with faith, courage, and a just cause David will still beat Goliath” ነበር ያሉት!
ሙሉ ንግግራቸው በድምጽና በተንቀሳቃሽ ምስል ከታች ቀርቧል።
ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያደረጉት ይህንን ታሪካዊ ንግግር ከማድረጋቸው በፊት  ለሕዝባቸው  የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በቤተ መንግሥታቸው እንደሰቀሉ ከታች የታተመውን ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል። ንግግሩ ንጉሡ በእጃቸው ይዘው ያነበቡትና ከጨረሱ ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ፈርመው ወደ መዝገብ ቤት ተመላሽ  ያደረጉት ታሪካዊ ሰነድ ነው።  አንብቡት!
ሚያዚያ 27 ቀን የከሀዲ ጥርቅምና የኢትዮጵያ ጠላቶች አገር በቀል ወኪል ሁሉ  «ነፍጠኛ»  እያለ ሲሰድባቸው የሚውላቸውን  ሁሉንም ጀግኖች አያቶቻችን የምናስታውስበት ቀን ነው። የከሀዲ ጥርቅምና የኢትዮጵያ ጠላቶች አገር በቀል ወኪል  ሁሉ ወደር የለሽ አርበኞቻችንን ሲያንኳስስ አርባ አምስት ዓመታት ቢሞላውም ታሪክና ትውልድ  ግን ሁሌም ሚያዚያ 27ን እየጠበቀ ውለታቸውን ሲዘክር ዝንታለም ይኖራል። ዘላለማዊ ክብር  አውስተን ያልጠገብነው ታሪካቸው አገራዊ ቅርስ ለሆነን ጀግናና አርበኛ አያቶቻችን ይሁን!
Filed in: Amharic