>

ባልደራስ የታሰሩ አባላቱና ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እንዲፈቱ ጠየቀ!

ባልደራስ የታሰሩ አባላቱና ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እንዲፈቱ ጠየቀ!

በዋሽንግተን የኢትዮጰያ ኤምባሲ በር ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል!

ዜና ጌጥዬ ያለው

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ትላንት ሐሙስ ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰሜን አሜሪካ፤ ዋሽንግተን ዲሲ፤ የኢትዮጵያ ኢምባሲ በር ላይ በወቅታዊና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት ፕሬዚደንት እስክንድር ነጋ፣ በሰሜን አሜሪካ የባልደራስ  ድጋፍ ማሕበር ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አያሌው እና አቶ ኤርሚያስ ሺበሺ ናቸው።
በአካባቢው የሚኖሩ ጋዜጠኞች በአካል የታደሙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ያሉት ደግሞ በ’ዙም’ መገናኛ በቀጥታ  በቪዲዮ ተሳትፈዋል።
በአዲስ አበባ በግፍ የታሰሩ አባላቱ እና ሌሎችም እንዲፈቱ ባልደራስ ጠይቋል። ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እንዲፈታም አሳስቧል።
በተጨማሪም፣” በጦር ግንባር ሀገር እየጠበቀ ያለውን ፋኖ ተውት። ህወሓት ጥቃት ከከፈተ ፋኖ ያስፈልጋል ” ብለዋል የአመራር አባላቱ። ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተነሳበት ጊዜ ፋኖ ሀገር ያዳነ፤ አሁንም ኢትዮጵያን እየጠበቀ ያለ አርበኛ መሆኑንም ዘርዝረዋል።
ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ይህንን እንዲረዳ እንደሚሠሩም የባልደራስ አመራሮች በመግለጫየቸው ተናግረዋል።
በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የባልደራስ ድጋፍ ሰጭ ማሕበር የኢትዮጵያን አንገብጋቢ ፖለቲካዊ ችግሮች ዘርዝሮ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ  ዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በደብዳቤ አስገብቷል። አዲሱን ዙር የግፍ እስር፣ ፖለቲካዊ ሽፋን የተሰጠውን የሃይማኖት ግጭት እና የሰሜኑን ጦርነት በዚሁ ደብዳቤ ዘርዝሯል።
ፓርቲው ሀገራዊ  ድርጅት ለመሆን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መቀጠሉም በመግለጫው ተነግሯል።
Filed in: Amharic