>

ከራስ አበበ አረጋይ ማሕደር የተገኘው የኢትዮጵያ አርበኞች የአምስት አመታት መዝሙር ...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ከራስ አበበ አረጋይ ማሕደር የተገኘው የኢትዮጵያ አርበኞች የአምስት አመታት መዝሙር …!!!

አቻምየለህ ታምሩ
አምስት አመታት ሙሉ በትክሻ ወይም ባሕያ እንዲሁም በበቅሎ የተያዘ በሶ፣ ቆሎና ጥሬ እየበሉ፤ በወጣ ገባውና አስቸጋሪው የአገራች መልክዓ ምድር እየተንገላቱ ባካሄዱት ጸረ ፋሽስት ኢጣሊያ ተጋድሎ በደምና በመከራ ነጻ አገር ያቆዩን አርበኞች በአስምቱ የተጋድሎ አመታት ውስጥ በጋራ የሚዘምሩት የትግል መዝሙር ነበራቸው።
ስለዚህ የአርበኞች የአምስት አመታት የትግል መዝሙር ለመጀመሪያ ጊዜ ተጽፎ ያነበብኹት ታላቋ የኢትዮጵያ ባለውለታና እንግሊዛዊት ፀረ ፋሽስት ንቅናቄ የሴቶች መሪ  የነበሩት ክብርት ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስት ያሳትሙት በነበረው “New times & Ethiopia news” ጋዜጣ ውስጥ ነበር።
ክብርት ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስት እ.ኤ.አ. በአፕሪል 2 ቀን 1938 ዓ.ም. ባሳተሙት “New times & Ethiopia news” ጋዜጣ ገጽ 5 ላይ ስለ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የጋራ መዝሙር የጻፉ ሲሆን የተወሰኑ ስንኞችንም በእንግሊዝኛ ተርጉመው በጋዜጣው ላይ አውጥተዋል። ከዚህ በስቀር ስለ አርበኞቹ የአስምት አመታት የጋራ መዝሙር የጻፈ አጥኚና ታሪክ ነጋሪ እስካሁን አላገኘሁም ነበር።
በቅርቡ በእጄ የገባውን የራስ አበበ አረጋይን ሙሉ ማሕደር ሳገላብጥ ግን እስካሁን ድረስ ስፈልገው የነበረውን የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች በትግሉ ወቅት በጋራ ይዘምሩት የነበረውን መዝሙራቸውን ላገኝ ችያለሁ።
ይህ የአርበኞች የጋራ መዝሙር ልብን የሚነካና የኢትዮጵያ አርበኞች በሙሉ በሃይማኖትና በጎሳ ሳይወነሱ በጋራ የሚዘምሩት የተጋድሎ ስንቃቸው ነበር። እያንዳንዱ የአርበኛ መሪ የሚከተሉትን አርበኞች ወደ ፍልሚያ ከማሰማራቱ በፊት ጧት፣ ጧት ይህንን መዝሙር ያስዘምርና የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ያሰቅል ነበር።
እነዚያ የማይከጅሉ እጆች የነበሯቸው ጀግኖች ያንን ሁሉ የመከራ ቀንበር ተሸክመውና የደምና አጥንት ዋጋ ከፍለው ወደ ፊት እያዩ በክብር ያቆዩዋትን አገር ያ የተረገመ ትውልድ ወደ ኋላ እያየ በማፍረስ አገራችንን መንግሥትነትን የአውሬ ፍላጎታቸው ማስፈጻሚያ ባደረጉ አረመኔዎች እጅ ላይ ጥለዋታል።
የራስ አበበ አረጋይን ማሕደር ጠብቆ በማቆየት፣ ራስ አበበ ከንጉሠ ነገሥቱና ከሌሎች አርበኞች ጋር የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎች፣ በትግሉ ወቅት የተነሷቸውን ታሪካዊ ፎቶግራፎችና ማስታወሻዎቻቸውን በሙሉ ከነልዩ ማስታወሻቸው ጋር ታሪካቸው ይጽፉ ዘንድ ወዳጄ ለሆኑ አዛውንት ምሁር  የሰጡት ልጃቸው ልጅ አየለ ወርቅ አበበ አረጋይ ናቸው። አፈሩን ይቅልላቸውና ልጅ አየለ ወርቅ አበበ በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
ከልጅ አየለ ወርቅ አበበ የራስ አበበ አረጋይን ታሪክ ለመጻፍ አደራ የተቀበሉት አዛውንቱ ወዳጄም “እድሜዬ እየገፋ በመሆኑ የልጅ አየለ ወርቅን አደራ የምወጣ ስላልመሰለኝ የራስ አበበ አረጋይን ማሕደር ላንተ ስልጥህና ታሪካቸው እንዲጻፍ አድርግ” ብለው የራስ አበበን ሙሉ ማሕደር ከነ ልጅ አየለ ወርቅ የአደራ ደብዳቤ ጭምር በአደራ ስለሰጡኝ የራስ አበበ ማሕደር በእጄ ሊገባ ችሏል።
በእጄ ከገባው ከዚህ የራስ አበበ ባሕደር ውስጥ ሳገላብጥ ያገኘሁትን የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የትግል ወቅት የጋራ መዝሙር ታነቡ ዘንድ ከታች አትመነዋል።
Filed in: Amharic