ይድረስ – ሕዝብን በገንዘብ ተክተው- በአገር ላይ ለሚቆምሩ ጠ/ሚ/ር…!!!
አሳዬ ደርቤ
የትኛውም ሤራ በተደጋገመ ቁጥር ድብቅ ቁማር መሆኑ ቀርቶ የተለመደ ተግባር ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ጠላትን ማክሰም›› በሚል አቋም ተጀምሮ ‹‹ደጀንን ማዳከም›› ወደሚል ሤራ የተቀየረውን እና በየሩብ ዓመቱ የሚደረገውን ጦርነት ብንመለከት ቁማር መሆኑ የታወቀው መቀሌ ያስገቡትን ሠራዊት ወደ ቆላ ተንቤን ከሸኙት ጠላት ጋር ድብን አድርገው የረሱት ቀን ነበር፡፡
ግን እርስዎ ያሰቡት ሐሳብ የቱንም ያህል አገርን እና ሕዝብን ዋጋ ቢያስከፍልም ከመሆን አይዘልምና ‹‹የተበተነ ዱቄት›› ብለው የጠሩት አሸባሪ ዱቄትና ሊጥ ሳይቀር የሚዘርፍና ንጹሐንን የሚጨፈጭፍ ወራሪ ሆኖ መጥቶ መደረግ የሌለበትን ሁሉ አደረገ፡፡
የእርስዎን ዝምታ እና ይሁንታ መስበር የሚችል ሕዝባዊ ጫጫታም ሆነ ቅሬታ ባለመኖሩ አሸባሪው ኃይል እስከፈቀደሉት ጊዜና ቦታ ድረስ ተጉዞ ንብረት ሲያወድምና፣ ሕይወት ሲያከስም ከረመ፡፡ ‹‹በቃህ›› ያሉ ቀን ደግሞ ክንድዎን የሚመክት ጋሻ አጥቶ ለወራት ሲያወድም የቆየው ወሪራ በቀናት ውስጥ ወደመ፡፡
ጦሩን ከፊት ከፊት እየመሩ እስከ ራያ ከተጓዙ በኋላም ያለ ህውሓት መንግሥትዎ መጽናት እንደማይችል አስታወሱ፡፡ የተለመደውን ሤራም ጠነሰሱ፡፡ እናም አገር የመታደግ ዘመቻውን አሸባሪን ወደ መታደግ ቀይረውትና ሁለተኛውን አገራዊ ድል ወደ ሦስተኛ ሕዝባዊ ትግል አራዝመውት ተመለሱ፡፡
ከመላው ኢትዮጵያዊ ጋር ተባብሮ ከባድ ዱላውን ሲሰነዝር የታየው የአማራ ሕዝብም ጠላቱን ሳይሆን እርስዎን ማሸነፍ ተሳነው፡፡ የአማራ ገበሬም በመንግሥት እጅ ሊያካፋ የሚችለውን የክረምት ዝናብ ትቶ በመንግሥት ይሁንታ ሊያጠፋ የሚመጣውን ጠላት ልክ እንደ አምናው ሁሉ መጠበቅ ግድ አለው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡- እርስዎ እኮ መንግሥት ብቻ ሳይሆኑ ሕገ-መንግሥት ነዎት! ለዚያም ነው በኃይል የተወሰደውና በኃይል የተመለሰው የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ መጽደቅ ሲገባው የእርስዎን ይሁንታ አጥቶ ወደ ነበረበት የተመለሰው፡፡ ሕገ-መንግሥቱን የማሻሻልና የማስቀጠል ጉዳይም በእርስዎ ዙፋን ላይ የተቀመጠ በመሆኑ አንዳንዱ አንቀጽ ለአንዳንዱ ክልል ተብሎ በቃልዎ ይሻራል፡፡ አንዳንዱ አንቀጽ ደግሞ ‹‹ላንድ ሕዝብ ተብሎ አይቀየርም›› በሚል ውሳኔ ባለበት ይቀጥላል፡፡
ሌላው ደግሞ በርካታ ምሑራን ‹‹አገር የሚባለው ምድሩ ወይሰ ፍጡሩ?›› እያሉ ሲነታረኩ እሰማለሁ፡፡ እኔ ግን አገር ማለት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወሰን ነው” እላለሁ፡፡
እናም እርስዎ አገር ይሆን ዘንድ ይሁንታዎን የቸሩት ክልል እንደ ፋሽሽት ጣሊያን ወራሪ ሆኖ የቀድሞ አገሩን ይወጋል፡፡ የእርስዎን ፍቃድ ያላገኘ ክልል ደግሞ ባዕድ ሆኖ እንዲሁም በዞን ቀላድ ተሸንሽኖ ሲወረር ይኖራል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡- ሕገ መንግሥቱ ማንኛውም አካል ከሕግ በታች መሆኑን ይደነግጋል፡፡ የእርስዎ መንግሥት ግን ከሕግ በላይ በመሆኑ በ48 ሠዓት ውስጥ ለሕግ መቅረብ ያለበት ተጠርጣሪ እንደ ጎበዜ ሲሳይ ለ9 ቀን ሊደበቅ ወይም ደግሞ ለሕግ ቀርቦ ቅጣት ሊወሰንበት የሚገባው አሸባሪ እንደ አቦይ ስብሐት በነጻ ሊለቀቅ ይችላል፡፡
‹‹የአጼዎቹ ሥርዓት አይመለስም›› የሚለው ዛቻም እርስዎ ላይ የማይሠራ በመሆኑ ንጉሥ ሆነው ጦር ሲያዘምቱ ብቻ ሳይሆን ቄስ ሆነው ሲገዝቱ ዐየዎታለሁ፡፡ እናም እርስዎ የገዘቱት አካል አገራዊ ሥሙ ጁንታ ብቻ ሳይሆን የቀን ጅብ ይሆናል፡፡ ግዝቱን ያነሱለት ቀን ደግሞ ከጅብነት ወደ ሰውነት ተቀይሮ ለድርድር ይቀመጣል፡፡
እርስዎ የባረኩት አሸባሪ ወራሪ ሆኖ ለሦስተኛ ዙር ወረራ ይዘጋጃል፡፡ ግዝትዎን የጣሉበት ፍጡር ደግሞ ለመወረር የተፈጠረ መሆኑን አምኖ በተመሳሳይ ስልት የሚወድምበትን ሦስተኛ ዙር ጦርነት ይጠባበቃል፡፡
መንግሥታዊ ወንበር የተቆናጠጡ ብቻ ሳይሆኑ መለኮታዊ ተዓምር የጨበጡ በመሆንዎ ‹‹ተከተለኝ›› ብለው የተጣሩ ቀን አገር ምድሩ ከኋላዎና ከጎንዎ ቁሞ አዲስ ታሪክ ይጽፋል፡፡ ‹‹በቃኝ›› ያሉ እለት ደግሞ የአምናው የጦርነት ታሪክ ሲደገምና ከኋላዎ ቁሞ የነበረው ሕዝብ ሲወድም ይታያል፡፡
እናም እልዎታለሁ…
የቀጣዩ ጦርነት ውጤትም በጠላት ክንድ ሳይሆን በእርስዎ እቅድ መሠረት የሚመራ ነውና ሕዝባዊ ትግሉና መገዳደሉ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል? ከቀጣዩ ትግል እጅዎን አስገብተው ድል የሚጨብጡበት ቀን’ስ መቼ ይሆን?