>

"የአማራ ክልል የሽግግር መንግሥት" ይቋቋም! (ኤርምያስ ለገሰ)

“የአማራ ክልል የሽግግር መንግሥት” ይቋቋም!

ኤርምያስ ለገሰ


የአማራ ማህበረሰብ የተጋረጠበትን የህልውና አደጋ እንዴት መታደግ ይችላል በሚለው ጥያቄ ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ምክረ ሃሳብ ሳቀርብ ቆይቻለሁ። ያቀረብኳቸውን ምክረ ሃሳቦች የተለያዩ ሚዲያዎች በተበጣጠሰ መንገድ ለራሳቸው በሚያመቻቸው መንገድ ቆራርጠው በማውጣት ለተከታታይ ሳምንታት ሲወያዩበት ተመልክቻለሁ። ዋና አጀንዳ አድርገው በመወያየታቸው አስቀድሜ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። የሃሳብ ድግስ ደግሶ አእላፍ ተቋዳሾችን እንደ ማግኘት የሚያስደስት ነገር የለም። በድጋሚ በጣም አመሰግናለሁ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከላይ እንደጠቀስኩት አንዳንዶች ለራሳቸው የፓለቲካ ፍላጎት ይጠቅሙኛል በሚሉት መንገድ እየቆራረጡ ሕዝቡን ግራ ሲያጋቡ ተመልክቻለሁ። በመሆኑም የቀረበውን ወደ ተግባር መለወጥ የሚችል ምክረ ሃሳብ በተጠቃለለ መንገድ በዚህ መልኩ አቅርቤዋለሁ። አሁንም በጥብቅ ማሳሰብ የምፈልገው አንዱን ምዕራፍ ከቀጣዩ ጋር አስተሳስሮና ሲነርጃይዝ አድርጎ ማየት ያስፈልጋል።

#የመጀመሪያው ምዕራፍ፣

ሕዝባዊ ቅቡልነቱን ያጣው የአማራ ክልል ምክር ቤት እና ስራ አስፈጻሚ በህጋዊ መንገድ ማፍረስ። ምክርቤቱ እውነታውን አምኖ ተቀብሎ ራሱን በራሱ በህጋዊ መንገድ ካፈረሰ የቅድሚያ ተመራጭ ይሆናል። ካልሆነ ግን በሰላማዊ ትግል ሕዝቡ የመተማመኛ ድምጽ የሚነፍግ ፒቲሽን በመፈረም በህጋዊ መንገድ ማፍረስ ሁለተኛው ምርጫ ይሆናል።

ሁለተኛው ምዕራፍ፣

ሕዝባዊ ቅቡልነቱን ያጣው የአማራ ክልል ምክርቤት እና ስራ አስፈጻሚው በህጋዊ መንገድ ከተሰናበተ በኃላ በምትኩ “የአማራ ክልል የሽግግር ምክርቤት” እንዲቋቋም ማድረግ። የሽግግር ምክር ቤቱ አባላት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ( የእያንዳንዱ ውክልና ከ10 በመቶ ያልበለጠ)፣ ሲቪክ አደረጃጀቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የሙያ አደረጃጀቶች፣ የባሮክራሲው ተወካዮች፣ የዲያስፓራ ተወካዬች…ወዘተ ያቀፈ ይሆናል።

ሶስተኛ ምዕራፍ፣

የአማራ ክልል ሽግግር ምክርቤት ዋና ዋና ተግባራት፣

3.1.  የክልሉን ሕገ መንግሥት የሚለውጥ ክንፍ ያደራጃል።

3.2.  የመንግስት የእለት ተዕለት ስራዎችን የሚሰራ የስራ አስፈፃሚ/ የፓለቲካ ክንፍ ያደራጃል።

3.3.  ለሽግግር ምክርቤቱ ተጠሪ የሆነ “የአማራ ሕዝባዊ የመከላከያ ኃይል” (ADF) ያደራጃል። የADF የመከላከያ አቅም ከሃይል ሚዛን አንጻር በአጭር ጊዜ ከትግራይ ኃይል (TDF) እና ‘የኦሮሞ ልዩ ሃይል” ጋር የተስተካከለ ማድረግን እንደ ግብ ይወስዳል። አልፋና ኦሜጋውም የሃይል ሚዛን በመጠበቅ የውስጥ ሰላምን ማስጠበቅ፣ ጦርነትን ማስቀረትና ለፓለቲካ ክንፉ የድርድር አቅም መፍጠር ይሆናል።

3.4.  ለሽግግር ምክርቤቱ ተጠሪ የሆነ ” የመንግስታት ግንኙነት እና ድርድር ክንፍ” ያደራጃል። የዚህ ክንፍ ተልዕኮ የሽግግር ጊዜው እስኪጠናቀቅ ድረስ በእኩል ቁመና ከፌዴራል መንግስት፤  ከክልል መንግስታትና  ከሌሎች ሃይሎች ጋር ሰላም መፍጠርንና ጦርነት ማስቀሩትን፤ ስጥቶ መቀበልንና የግዛት አንድነት ባስጠበቀ መንገድ መደራደር ይሆናል።

3.5. ለሽግግር ምክርቤቱ ተጠሪ የሆነ ” የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ክንፍ” ያደራጃል።

Filed in: Amharic