>

መታፈንን ፈርተህ ለታፈንከው ወገኔ!! አሳዬ ደርቤ

መታፈንን ፈርተህ ለታፈንከው ወገኔ!!

አሳዬ ደርቤ


*….  ‹‹ፈሪ ልብ›› ጠላቱን ቀርቶ ጥላውን ያሳድዳል፡፡ ለስጋት የዳረገውን ሁሉ በማሰርና በመቅበር ከፍርሐት ስሜቱ ለመንጻት ይጋጋጣል፡፡ ጀግና ግን ከትርጉም የለሽ ሕይወት ይልቅ ምክንያታዊ ሞትን ይመርጣል፡፡ እንደ ቴዎድሮስ ‹‹እጄን አልሰጥም›› ብሎ እርሳስ ይጎርሳል፡፡ እንደ እሸቴ ሞገስ ‹‹ልጄን ጥየ አልሄድም›› ብሎ መላዕከ ሞትን ግብግብ ይገጥማል፡፡

ከሞት በላይ ባርነትን እና ትርጉም አልባ ሕይወትን ተጠየፍ፡፡

የምታስበውን መተግበር ቢሳንህ እንኳን ለመናገር አትስነፍ፡፡

ጥፋት መፈጸምን እና ግፍ መሥራትን ተጠየፍ እንጂ ፍትሐዊ ላልሆነ ቅጣት አትሸነፍ፡፡

ከፊታችን እኔና አንተን የሚፈትን ከባድ ቀን እየመጣ ነው፡፡ እናም ይህ ቀን መከራ አሸክሞህ እንዲሄድ ከፈለግክ ‹‹እንዴት ልችልው ነው›› እያልክ አካብደህ ተቀበለው፡፡ ጠንካራ አድርጎህ ያልፍ ዘንድ ከፈቀድክ ግን ‹‹አልፈዋለሁ›› በሚል መንፈስ ብርቱ ሆነህ ጠብቀው፡፡

‹‹ፈሪ ልብ›› ጠላቱን ቀርቶ ጥላውን ያሳድዳል፡፡ ለስጋት የዳረገውን ሁሉ በማሰርና በመቅበር ከፍርሐት ስሜቱ ለመንጻት ይጋጋጣል፡፡

ጀግና ግን ከትርጉም የለሽ ሕይወት ይልቅ ምክንያታዊ ሞትን ይመርጣል፡፡ እንደ ቴዎድሮስ ‹‹እጄን አልሰጥም›› ብሎ እርሳስ ይጎርሳል፡፡ እንደ እሸቴ ሞገስ ‹‹ልጄን ጥየ አልሄድም›› ብሎ መላዕከ ሞትን ግብግብ ይገጥማል፡፡

ኪሳራን የሚፈራ ነጋዴ ትርፋማ መሆን ይሳነዋል፡፡ እስራትንና እንግልትን የሚጠላ ዜጋ ነጻነቱን ሰውቶ ለባርነት ይንበረከካል፡፡ ጠላት በተነሳበት ወቅት ትግልን የሚፈራ ሕዝብ በቀላሉ ድል ሆኖ ከጦር ሜዳ የከፋ መራር ፍዳ ያስተናግዳል፡፡

በተረፈ…

‹‹በጋራ የሚፈትነን የአፈና ቀን መምጣቱን ስነግርህ ‹‹እራስህን ጠብቅ›› አትበለኝ፡፡ አንተ ጠብቀኝ እንጂ እኔማ ያንተ እረኛ ነኝ፡፡

ምክንያቱም… 

እንደ ግለሰብ በተናጠል እራሱን ወይም ደግሞ ቤተሰቡን የሚጠብቅ ፍጡር ድምጹን አጥፍቶ ጎረቤቱ ሲጠቃ እያዬ እንደ ሕዝብ ይወድማል፡፡ እርስ በእርስ የሚጠባበቅ ሕዝብ ግን በጋራ የመጣበትን አደጋ መክቶ በተናጠልም ሆነ በጋርዮሽ ከመጠቃት ይድናል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን ጸሐፊው ሁሉ ባደፈጠበትና በሚሳደድበት ጊዜ እዚህ እየመጣሁ የምቸከችክህ ልጆቼን አቅፌ በማደር ፈንታ ወህኒ ቤት ገብቼ ትኋን ማባረር አምሮኝ እንዳይመስልህ፡፡

ያላንዳች ጥፋት እንደ ሕዝብ የተላለፈብንን ቅጣት እንደ ግለሰብ በመፍራት ማለፍ እንደማይቻል ገብቶኝ እንጂ….!!

ወላጅን ቀርቶ ሕጻናትን ሳይቀር የሚያፍን መዳፍ እንዳያፍነኝ ፈርቼ እራሴን ማፈን ስለማልፈልግ እንጂ…!!

እናም እልኻለሁ…

አለመታፈን የምትፈልግ ከሆነ እራስህን በመለጎም ፈንታ ‹‹አፈናው ይቁም›› ብለህ ተቃወም!

Filed in: Amharic