>

ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ታሰረች...!!! (ሮሃ ሚዲያ)

ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ታሰረች…!!!

ሮሃ ሚዲያ 


ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል ተጠርጥሮ ፍርድ ቤት ቀረበ

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድን ሁለት የፌዴራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ ፖሊሶችና 3 ሲቪል ለባሾች ሰሚት ከሚገኘው የጓደኛዋ መኖርያ ቤት በግምት ከጧቱ 3 ሰዓት አካባቢ “ለጥያቄ እንፈልጋታለን” ብለው ወስደዋታል። ወዴት እንደተወሰደች የታወቀ ነገር የለም።

ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል ተጠርጥሮ ፍርድ ቤት ቀረበ

ትላንት ከሰዓት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው፤ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” ተጠርጥሮ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረበ። የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ፖሊስ በጋዜጠኛው ላይ ለሚያደርገው ምርመራ 12 ቀናት ፈቅዷል።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ፤ “አልፋ ቴሌቪዥን” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና ባለቤት የሆነውን የጋዜጠኛ በቃሉ ጉዳይ ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 20፤ 2014 የተመለከተው በጽህፈት ቤት በኩል ነው። ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመጣው መርማሪ ፖሊስ፤ በቃሉ “በተለያዩ በመንግስት ሚዲያ ቀርቦ ቃለ መጠይቅ በማድረግ መንግስት እንዲጠላ እና ሀይማኖታዊ ግጭት እንዲፈጠር ተንቀሳቅሷል” ብሏል።

ፍርድ ቤት ያለ ጠበቃ የቀረበው ጋዜጠኛ በቃሉ በበኩሉ “ስራ እንዳልሰራ ተደርጌያለሁ በመንግስት ሚዲያም ቀርቤ አላውቅም” ብሏል። በቃሉ በችሎቱ ላይ “ጉዳዩ መታየት ያለበት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሰረት ነው” ሲል  የተከራከረ ሲሆን የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅለትም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የጋዜጠኛውን ጉዳይ መርማሪ ፖሊስ “ጋዜጠኛው በዋስትና ከወጣ ይጠፋል። ግብረ አበሮቹንም ያባብላል” በሚል የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱም መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ቀናት በሁለት ቀንሶ 12 ቀናትን ፈቅዷል።

በመጪው ሰኔ 2፤ 2014 በሚኖረው ቀጣይ ቀጠሮ ፖሊስ በተሰጡት የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት አንዲያቀርብ በማዘዝ ፍርድ ቤቱ የዛሬውን ውሎውን አጠናቅቋል። ትላንት አርብ አራት ኪሎ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በፖሊስ የተወሰደው ጋዜጠኛ በቃሉ፤ ከተያዘበት ሰዓት ጀምሮ ከቤተሰብ ጋር አለመገናኘቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Filed in: Amharic