>
5:29 pm - Friday October 10, 1451

ይችን መዝግባችሁ ያዙልኝ...!!!

ይችን መዝግባችሁ ያዙልኝ…!!!

አሳዬ ደርቤ


*…. የመጀመሪያ ምዕራፍ ‹‹የሕግ ማስከበር›› ዘመቻ በስኬት መጠናቀቅ ከቻለ ሁለተኛው ምዕራፍ ‹‹ሕግ አስከባሪ›› የሚል ይሆናል፡፡ እናም ‹‹በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች መልስ እስኪያገኙ ድረስ በፌደራል መንግሥትና በኮማንድ ፖስት ሊተዳደሩ ይገባል›› መባል ይጀመራል…!!!

የአራት ኪሎው መንግሥት ወደ ፈላጭ ቆራጭነት ለመሸጋገርና በወልቃይት መሬት ላይ ለመደራደር ሲያስብ አብን እና ብአዴን የእቅዱ ተገዢ ሆነው ደስ አሰኙት፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ በሶሻል ሚዲያው መድረክ ሕዝባቸውን የሚያነቁ ጦማሪዎችና በጦር ሜዳ ላይ የሚዋደቁ ወጣቶች እንቅፋት ሆነው ታዩት፡፡

እርሱም አለ…

‹‹በወልቃይት ማንነት ዙሪያ ለመደራደርም ሆነ አማራን ለማስገበር የጌታቸው ረዳን ሐሳብ መተግበር ግድ ይላል፡፡ ይሄውም የአማራን ልሳኖችን እና ክንዶች የመስበር ዘመቻ ‘ሕግ ማስከበር’ ይባል፤››

ከዚህም ውሳኔ በኋላ ከላይ የተዘረዘሩትን ኃይሎች ጠርቶ ወረቀትና ገንዘብ ካቀበላቸው በኋላ “ሕግ አስከብሩ›› አላቸው።

እነርሱም ቦርጫቸውን እንደ ጠረጴዛ በመጠቀም የተሰጣቸውን ወረቀት ካስደገፉበት በኋላ ‹‹ጽንፈኛ›› በሚል ርዕስ ‹‹እንቢተኛ እና ሐቀኛ›› የአማራ ልጆችን ሥም መጻፍ  ጀመሩ፡፡ እናም አሁን ላይ ፦

➔አንዳንድ የአብን አመራሮች በብአዴን የሚታፈኑ የአማራ ልጆችን እየጠቆሙ ነው፡፡

➔አንዳንድ ተከፋይ የአማራ ወመኔዎች ‹‹ወገኔ›› የሚሉትን ሕዝብ ለአፈና ዳርገው ‹‹ወያኔ›› የሚሉትን ጠላት እየጠበቁ ነው፡፡

➔አብዛኛው የአማራ ሙሕራን እና ፖለቲከኞች ‹‹ተደራጅ›› ብለው ሲቀሰቅሱት የኖሩት ፋኖ ሲሳደድ እያዩ ‹‹ሕግ እንዲከበር እንፈልጋለን፡፡ በወልቃይት ላይ ለመደራደር ያሰባችሁ ቀን ግን እንጣላለን›› እያሉ ነው፡፡

ይሄውም የመጀመሪያ ምዕራፍ ‹‹የሕግ ማስከበር›› ዘመቻ በስኬት መጠናቀቅ ከቻለ ሁለተኛው ምዕራፍ ‹‹ሕግ አስከባሪ›› የሚል ይሆናል፡፡ እናም ‹‹በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች መልስ እስኪያገኙ ድረስ በፌደራል መንግሥትና በኮማንድ ፖስት ሊተዳደሩ ይገባል›› መባል ይጀመራል፡፡

ያን ጊዜም ከላይ የተጠቀሱት ተላላኪ ኃይሎች ስምምነታቸውን ገልጸው ከወጡ በኋላ ለይምሰል ያህል ከሕዝብ ጎን ቆመው ቁጣቸውንና ተቃውሟቸውን እንዲገልጹ ይፈቀድላቸዋል፡፡

የሕዝብ ጠበቃና ጠባቂ የሆኑ ወጣቶች ወንጀለኛ እና ጽንፈኛ ተብለው እየተመረጡ ሲታፈኑ በዝምታው አማካኝነት ለዘብተኛ መሆኑን ሲገልጽ የከረመው የአማራ ሙሕርም በብልጽግና ውሳኔ የመናደድ መብቱ ይከበርለታል።

ከወልቃይት ምድርም ‹‹ማንነቴን የምትወስን አንተ ማን ነህ›› የሚል ትግል ይቀጣጠላል፡፡ ‹‹የወገን ያለህ›› የሚል ቃልም ይሰማል፡፡ ሆኖም ግን ያ ጊዜ እንደሚመጣ አውቀው በሸዋ፣ በወሎ፣ በጎጃምና በጎንደር ሲደራጁ የከረሙ ፋኖዎች ለአፋና እና ለብተና የተዳረጉ በመሆናቸው ፈጥኖ የሚደርስ ኃይል አይኖርም፡፡

ከዚያ በማስከተል በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የታፈኑ ሁሉ ያለምንም ፍርድ በነጻ ይለቀቃሉ፡፡ ከእነዚህ መሃከል አብዛኞቹ ትግላቸውን ሲቀጥሉ አንዳንዶቹም ዝምታን ተምረው ይወጣሉ፡፡

አሳሪዎቹ ደግሞ የሚታሠሩበት ቀን እስኪመጣ ድረስ የእነሱ ሕልውና በብልጽግና እድሜ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተረድተው የህውሓትና የመንግሥት ጋብቻ ሲፈጸም እልልታቸውን ያቀልጣሉ። ‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› በሚል አቋምም ዛሬ ላይ የንቁ ዜጎች ማሸማቀቂያ ካደረጉት ጠላት ጎን ተሰልፈው ሕዝባቸው ላይ ይዘምታሉ፡፡

ይህ ቀን እንዳይመጣ የሚሹ ወገኖች ግን አሁን ላይ እንቅልፍ በተጫጫነው ክልል ውስጥ ቆመው ቀን እና ሌሊት በመታገል ላይ ይገኛሉ። “አፈናው ይቁም” ይላሉ።

Filed in: Amharic