>
5:21 pm - Sunday July 20, 9969

ታፋኞቻችንን ስናስባቸው...!!! (አሳዬ ደርቤ)

ታፋኞቻችንን ስናስባቸው…!!!

አሳዬ ደርቤ


*….. በጥቅም ተገዝቼ ድምጽ ሳልሆናችሁ ብቀር ምላሴ ከትናጋዬ ትጣበቅ!!

*….. እስርን ፈርቼ በአረመኔ መዳፎች መታፈናችሁን ብክድ የአምላክ ጥበቃ ከእኔ ይራቅ!!

*….. ጥፋታችሁ አገር አጥፊን ማውገዛችሁ ብቻ ነው። ወንጀላችሁም ወንጀለኛን መክሰሳችሁና የፍትሕ ድምጽ መሆናችሁ ብቻ ነው።

ከቤታቸው እና ከሥራ ቦታቸው ታፍነው የተወሰዱ ጋዜጠኞችና የሕዝብ ድምጾች ለጋዜጣዊ መግለጫ የተጠሩ ይመስል ዘና ባለ መንፈስ ውስጥ ሆነው እንዲሁም መታሠራቸውን ዘንግተው ከእስር ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡  መስኪ ግን ለሰባት ቀናት ያህል መታሰሯን ሳይሆን የሰባት ወር ልጇን መርሳት ተስኗታል፡፡

ከእነዚህም ታፋኞች መሀከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ሰሎሞን ሹምዬ ‹‹ዛሬ ቀኑ ማን ነው›› በማለት ሲጠይቅ ‹‹ባግባቡ አልተከበረም እንጂ ግንቦት ሃያ ነው›› በማለት ያየሰው ሽመልስ መለሰለት፡፡

ይሄንንም መልስ መስኪ ስትሰማ ‹‹‹‹የግንቦት ሃያ ቀንን በደማቁ ለማክበር ጋዜጠኞችን እና የመብት ጥያቄ ያነሱ ዜጎችን አሰልፎ ወደ እስር ቤት ማስገባት እንጂ ሕዝብን አሰልፎ ወደ አደባባይ ማውጣት አይጠይቅም›› በሚል መልስ ከወትሮው በላቀ መልኩ ግንቦት ሃያ መከበሩን ታስረዳው ጀመር፡፡ አቦይን በምሕረት በፈታው መንግሥት የታሰሩት አቶ ታዲዮስ ታንቱም ‹‹እዚህ እስር ቤት የተገኘነው እኮ አጥፍተን ሳይሆን የግንቦት ሃያ በዓልን አክብሩ ተብለን ነው›› በማለት በመስኪ ሐሳብ መስማማታቸውን ገለጹ፡፡

በወሬው መሀከልም ከፊት ለፊታቸው ካለ ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ቴሌቪዥን ‹‹ከአፍታ በኋላ ልዩ ልዩ ዜናዎች ስለሚኖሩን ባሉበት ይጠብቁን›› የሚል መልዕክት አስተላለፈ።

ያን ጊዜም በወያኔ ዘመን ወደ እስር ቤት ከገባ በኋላ የታሰረበትን ጥፋት ከተመስገን በየነ አንደበት ሲያዳምጥ የኖረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ‹‹ከመኮነን መንትያ ልጆች አንዱ ወንጀሌን ቢነግረኝ…›› ከሚል ንግግር ጋር ሪሞቱን አንስቶ ቻናል ይቀያይር ጀመር፡፡

‹‹የመኮነን መንትያ ልጆች እነማን ናቸው›› ተብሎ ሲጠየቅም ‹‹መሳይ መኮነን እና ናትናኤል መኮነን ይባላሉ›› የሚል መልስ ሰጥቶ በየቻናሉ ሲፈልጋቸው ከቆየ በኋላ ከአቶ ደመቀ መኮነን ውጭ ማንንም ማግኘት ስላልቻለ ቻናሉን ፋና ላይ አድርጎ ሪሞቱን አስቀመጠው፡፡

በዚህም ቻናል ‹‹በሕግ ማስከበር ዘመቻው በዝርፊያ፣ በሕገ-ወጥ መሳሪያ ዝውውር፣ የሕብረተሰቡን ሰላም በማወክና በኮንትሮባንድ ንግድ… የተጠረጠሩ ከአምሥት ሺህ በላይ ዜጎች በቁጥጥር ስር ዋሉ›› የሚል ዜና ሲከታተል ከቆየ በኋላ የኮንትሮባንድ ዜናው እሱን የሚወክል ሆኖ ስላላገኘው ቻናሉን አሚኮ ላይ አድርጎ ‹‹ሕገ መንግሥቱን በመናድ የተጠረጠሩ…›› የሚል ዜና ይጠብቅ ያዘ፡፡

በዚህ መሀከልም ወደ ታፋኞቹ የመጣ አንድ የፖሊስ አዛዥ ‹‹በአንዳንድ ነገሮች ላይ ላነጋግራችሁ ስለምፈልግ ሰብሰብ ብላችሁ ተቀመጡ›› የሚል ትዕዛዝ ከሰጣቸው በኋላ ማስታወሻ ደብተሩን ገልጦ ከፊታቸው ተቀመጠ፡፡

ከደርዘን በላይ ከሚሆኑ ታዋቂ ጋዜጠኞች መሀከል እራሱን ያገኘው የፖሊስ አዛዥም ‹‹መቅረጸ ድምጽና ካሜራ ሳትይዙ የመጣችሁት ለምንድን ነው?›› ብሎ ሊቆጣቸው ካሰበ በኋላ ከፊቱ የተገኙት ታስረው እንጂ ለጋዜጣዊ መግለጫ ተጠርተው አለመሆኑ ትዝ ሲለው ‹‹የእስረኛ አያያዛችን እንዴት አገኛችሁት? ጤንነታችሁስ እንዴት ነው?›› በማለት ጠየቀ፡፡

ለዚህም ጥያቄ አቶ ታዲዮስ ታንቱ የሰጡት መልስ እንዲህ የሚል ነበረ፡፡

‹‹የታፈንበት መንገድ ከኮቪድ ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም ኤካ ሆስፒታል ሳንገባ አብዛኞቻችን አገግመናል››

Filed in: Amharic