በዐማራ ክልል መንግሥታዊ አፈና በአፋጣኝ ይቁም…!!!
የእናት፣መኢአድ እና ኢሕአፓ የጋራ መግለጫ
[መንግሥት] “ማርከህ ታጠቅ” የተባለውን ሕዝብ በትግሉ ወቅት እንደአለኝታ የቆጠረውን ፋኖን ለማሳደድ፣ አለፍ ሲልም የማኅበረሰቡን ሥነ-ልቡና ለመስለብ በሕግ ማስከበር ሰበብ አንገት ማስገቢያ ቀዳዳ ፍለጋ ሊገባ ይችል ይኾን ወይ? የሚሉ ጭንቀቶች በኹሉም ዘንድ እንደየመጠኑ ይንጸባረቅ ነበር፡፡
የፈሩት ይደርሳል… እንዲሉ በመጀመሪያ በክፉ ጊዜ “ድረስልኝ” ብሎ የጠሩትን “ፋኖ” ተረታ ተረቶችን እየሰደሩ በጓዳ ውይይቶችና በዐደባባይ ሲያወግዙና ሲያስወግዙ ከርመው በይፋ ማሳደዱንና አፈናውን ቀጥለው ምንም የማይመለከታቸው ሕፃናትና ሴቶች ጭምር የጥቃት ሰለባ እየኾኑ ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ እነበላይ ዘለቀ በፋኖነትና በአርበኝነት ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጥተው ተፋልመው ሀገራቸውን ነፃ አውጥተው ሳለ በነገር ሠሪዎች ትብታብና አጉል የሥልጣን ፍርሀትና ሽኩቻ ውለታቸው የተከፈላቸው በስቅላት ነበር፡፡ በደርግም በሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግም ለሀገራቸው ውለታ የዋሉ ምርጥ የጦር መሪዎች ገና ለገና ለዐራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ስጋት ሊኾኑ ይችላሉ በሚል ተቀጥፈዋል፡፡
አኹን በዐማራ ክልል እየተደረገ ያለው መንግሥታዊ አፈና ታሪክ ራሱን እየደገመ ለመኾኑ ጥሩ ማሳያ ኾኖ የሚቀርብ ነው፡፡ የማኅበረሰብን ቅስም መስበር፣ የኃይል ሚዛንን ማስጠበቅ፣ አጉል የሥልጣን ስጋት፣ መሪ ማሳጣት እና በዚሁ አጋጣሚ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችን ከመከላከያና ልዩ ኃይል ተመላሾችን ለማሳደድ እየተጠቀመበት ነው፡፡ በሸዋ፣ ወሎ፣ ጎንደር፣ ጎጃም በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ታፍነዋል፣ በወልዲያ፣ ሞጣ፣ መርዓዊ፣… ብዙዎች የቡድን መሣሪያ በታጠቁ አጋኣዚያዊ እርሾ ባልለቀቃቸው ኃይሎች ተገድለዋል፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ስማችን የተጠቀሰው ፓርቲዎች እንዲህ ያለውን በሕጋዊነት ሽፋን የሚደረግን መንግስታዊ አፈና በጽኑ እያወገዝን ለሞቱና አካላቸው ለጎደለ ወገኖቻችን ልባዊ ኀዘናችንን ለመግለጽ እንወድዳለን፡፡