>

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመዝጊያ መግለጫ አወጣ...!!! (ኢ.ኦ.ተ.ቤ)

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመዝጊያ መግለጫ አወጣ…!!!

ኢ.ኦ.ተ.ቤ

*…. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሰሞኑን ባካሄደው ጉባዔ በአገሪቱ ጦርነት ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን  ቤተ ክርስቲያን የአስታራቂነት ሚናዋን ለመወጣት ፍላጎት እንዳላት ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ለዚህ ጉዳይ መደላድል ለመፍጠር የተወከሉ ብጹአን  አባቶች ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ እና ብጹዕ አቡነ አብርሃም አገልግሎታቸው የሰመረ ያማረ እንዲሆን በምልዓተ ጉባኤው የተደረገላቸውን ጸሎት  በሲኖዶስ ጉባኤያተኛው ፊት በመስገድ ከአባቶች ቡራኬ ተቀብለዋል!!!

በቅዱስ ሲኖዶስ ፅ/ቤት ዛሬ በመግለጫው፥ ውይይቱን ተከትሎ በቀጣይ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ተወግዶ አጠቃላይ ሰላም በሚሰፍንበት መልኩ ተነጋግሮ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት እንዲቻል፣ ቤተ ክርስቲያኗ የአስታራቂነት ሚናዋን መጫወት እንድትችል ለማድረግ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ እንዲቀርብ ተደርጓል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሰሞኑን ባካሄደው ጉባዔ በአገሪቱ ጦርነት ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን እና የጦርነት ምንጭ የሆኑ ችግሮች እንዲፈቱ ቤተ ክርስቲያን የአስታራቂነት ሚናዋን ለመወጣት ፍላጎት እንዳላት ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባዔ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቤተ ክርስቲያኗ፣ በካህናቶቿ እና በምዕመናን ላይ በደረሱት ጥቃቶች፣ በቤተክርስቲያናት መቃጠል እና በሐይማኖታዊ በዓላት ቦታዎች መነጠቅ ዙሪያ በአጽንዖት ተወያይቶ፣ በቤተክርስቲያኗ ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን ለፌደራል እና ክልል መንግሥታት እንዳቀረበ እና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ እንደጠየቀ ተገልጧል። በትግራይ የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያኗን አስመልክተው ያወጡትን መግለጫ ያስታወሰው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ፣ በትግራይ የሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት ለአገር አንድነት በማዕከል ከሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶሱስ ጋር በጋራ እንዲሰሩ ጉባዔው ጥሪ አድርጓል።

ምልዓተ ጉባዔው ጨምሮም፣ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ሆስፒታል እንድትገነባ እና በጦርነት እና ግጭት ለተጎዱ ወገኖች፣ ለተጎዱ ቤተ ክርስቲያናት እና ለተዳከሙ የአብነት ትምህርት ቤቶች ማቋቋሚያ እና መደጎሚያ የገንዘብ ድጋፍ እንድታደርግ መወሰኑን መግለጫው አመልክቷል።

Filed in: Amharic