>

ስለሀገር ተነጋግሮ ለመግባባት ሀገር ላይ መቆምና ወደ መሀል መምጣት ያስፈልጋል...!!!"  (በድሉ ዋቅጅራ)

ስለሀገር ተነጋግሮ ለመግባባት ሀገር ላይ መቆምና ወደ መሀል መምጣት ያስፈልጋል…!!!”

 (በድሉ ዋቅጅራ)


.ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር እንድትወጣና ሰላሟ እንዲመለስ የመፍትሄ ሀሳብ የማያቀርብ የፖለቲካ ፓርቲ (ወይም የፓርቲዎች ጥምረት) እና አክቲቪስት/ግለሰብ የለም፤ መንግስትም እንዲሁ ከችግር እንወጣበታለን ያለውን መንገድ ተከትሎ እየሰራ ነው፡፡

እነዚህን ‹ለሀገር እንሰራለን› የሚሉ ግለሰቦች፣ ፓርቲዎችና መንግስትን እንዳይግባቡ የሚያደርጋቸው ዋናው ምክንያት የቆሙበት ቦታና የመሸጉበት ጽንፍ ነው፡፡

በዚያ በኩል፣.  . .

አንድ ግለሰብ ወይም ፓርቲ ስለሀገሩ ለመነጋገር/ለመስራት ሲነሳ ግቡ ሀገሩና ዜጋው ብቻ መሆን አለበት፡፡ ስልጣንና ገንዘብ ከሀገሩና ከወገኑ እንኳን ሊወዳደር ሚዛን ላይም መቅረብ የለበትም፡፡ ምእራባውያኑ የገቡባቸው ሀገራት (ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ሱማሌ) የገጠማቸውን የተመለከተ፣ ምእራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ እንዴት ያለ አሉታዊ ፍላጎት እየታወቀ ‹የውጭ ሀይል ኢትዮጵያ ይግባ› ብሎ የሚነሳ፣ አራት አመት ጠብቆ በመጪው ምርጫ ከመወዳደር ይልቅ ‹ዛሬ መንግስት ተለውጦ የሽግግር መንግስት ካልተመሰረተ ሀገር ይፈርሳል› ወዘተ. እያለ ጉባኤ እየጠራ መግለጫ የሚያወጣ የፓርቲ ድርጅትም ሆነ አክቲቪሰት/ግለሰብ ሀገሩ ላይ ቆሞ፣ ሀገሩን አስቀድሞ የተነሳ ነው ለማለት አይቻልም፡፡

በዚህ በኩል፣ . . .

ከላይ ከተጠቀስኳቸው በተለየ ሀገራቸውንና ወገናቸውን ብቻ ስቀድመው ለችግሮች መፍትሄ የሚያቀርቡ አክቲቪስቶች/ግለሰቦችና ፓርቲዎች (ወይም የፓርቲ ጥምረቶች) ባይበዙም አሉ፤ መንግስት የእነዚህን አካላት የመፍትሄ ሀሳብ ሊያዳምጥና ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል፡፡ መንግስትነት የሀገር አስተዳዳሪነትን እንጂ ለሀገር ተቆርቋሪነትን አያጎናጽፍም፡፡ ደርግ በሀገር ፍቅር የተለከፈ፣ ወያኔ/ኢህአዴግ የሀገር ፍቅርን የተጸየፈ መንግስታት ነበሩ፤ ስለሀገር ተቆርቋሪነታቸው ሰማይና ምድር ቢሆንም ሁለቱም ሀገር አስተዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ በመሆኑም ሀገር የሚያስተዳድር መንግስት ምንጊዜም ከእሱ እኩል ወይም በበለጠ ለሀገራቸው የሚያስቡ ግለሰቦችና ፓርቲዎች እንዳሉ በመገንዘብ በሩን መክፈት፣ ለሀገራቸው እንዲሰሩ እድል መስጠት አለበት፡፡

በዚህና በዚያ በኩል . . . .

እንኳን የሀገርን  የቤተሰብም ችግር ለመፍታት መነጋገር ያስፈልጋል፤ ተቀራርቦ መነጋገር፡፡ የየራስን ጥግ ይዞ በየተራ መናገር መነጋገር አይደለም፡፡ ስለኢትዮጵያ ያገባናል የሚሉ በየተራ መናገር አቁመው መነጋገር አለባቸው፤ በርግጥ ጉዳያቸው ሀገርና ህዝብ ከሆነ፡፡ ሁለቱም ወገኖች በየጽንፉ ከገነቡት የራስ ሀሳብ ጣኦትን ማምለኪያ ታዛ ወጥተው ወደ መሀል መምጣት አለባቸው፡፡ የገዛ ሀሳባቸውን ቋሚና ማገር አድርገው በየጽንፉ ከገነቡት ዋሻ ወጥተው መሀል ላይ መገናኘት/መነጋገር መጀመር አለባቸው፡፡ ተራርቀው ከቆሙበት ወደ መሀል መጥተው መነጋገርና ሀገርንና ህዝብን ከችግር እንዲላቀቅ መስራት አለባቸው፡፡  ለግማሽ ምእተአመት ኢሊቶቹ ያራመዱት ጽንፍ – ረገጥ ፖለቲካ ህዝብ ላይ ያደረሰው ሰቆቃ፣ ሀገርን የከተተበት አዘቅት ሊያማቸው ይገባል፡፡ ሀገርም ይበቃታል! ህዝቡም ይበቃዋል፡፡

Filed in: Amharic