>

አልወለድም...!!!  (አቤ  አቤ ጉበኛ)

አልወለድም…!!!

 አቤ ጉበኛ

እውነት በሌለበት በዚህ ውሸት አለም፣

እኔ አልወለድም ይቅርብኝ ግዴለም፣

ሠው በሰውነቱ እኩል ካልተዳኘ፣

ወፍራም በውፍረቱ ዳኝነት ካገኘ፣

ድህነት እርሀብን ችግርና ስቃይን ፣

ለማየት አልሻም ቅጡ ያጣ ፍርድን፣

አልወለድም፣

እቢ አልወለድም እኔ በዚህ ዓለም፣

ለህይወት የሚያጓጓ አንድ ነገር የለም፣

ለኗሪ አኗኗሪ ሆኘ ከምገፋው፣

ህይወት ተብሎ ስቃይን ከምጎናፀፈው፣

ሳልወለድ ልሙት እዚሁ ግደሉኝ፣

ከእናቴ ማህፀን ቀጥታ ቅበሩኝ፣

አልወለድም

ሳልፈልግ በወላጆች ስራ ፈጥራችሁኝ ሳለ፣

ብየ ስጠይቃችሁ በዓለም ምንድን አለ?

ለእኔ መኖሪያ ሚሆን ፣

ሀብት አለ?……….የለም፣

ነፃነት አለ?……….የለም፣

ፍትህ?……….የለም፣

ታዲያ ይሁ ነገር ከሌለ በምድር፣

ኧረ አልወለድም ውሀ ሁኘ ልቅር፣

አልወለድም፣

በዳይ እና ተበዳይ ገዢና ተገዢ፣

የሚል መደብ ካለ ስበብ ሳታበዢ፣

ዐለም አልሻሽም አትሽኝ እኔንም፣

ከአንቺጋ ለመኖር እኔ አልወለድም፣

አልወለድም፣

የዋሁ ደሀ ህዝብ ጉልበቱን በዝብዞ፣

ሀብታሙ ካለልክ ሁሉን አግበስብሶ

የሚወስድበት ዓለም፣

ባለስልጣን እንደጌታ እራሡን ኮፍሶ፣

ሁሉን የሚያሸክም የሚቀማም ነክሶ፣

በሆነበት ዓለም ለመኖር አልመጣም፣

እንዲህ ያለ ህይወት ልኖር እኔ አልወጣም፣

አልወለድም፣

ተወለድ ካላችሁ

ሠው በሠውነቱ እኩል ከተዳኘ፣

በሚሠራው ስራ ፍትህን ካገኘ፣

ጥቅምም ሆነ ጉዳት እንደሠራው ሁሉ

እኩል ክፍፍልን ካደረግን እዉን

የዛኔ ልወለድ ዐለም እኩል ስታይ

ሠውን ላይ ታች አድርጋ ከፍላ ሳትለያይ፡፡

Filed in: Amharic