ተሰደብኩኝ!” ካሉ በየእለቱ እንባው የሚፈሰው ደሙ የሚቀዳው ድሀ ምን ይበል
እርስዎ ስድብ ካመመዎ ለአራጆች ለአፈናቃዮች አሳልፈው የሰጡት ህዝብ ምን ይበል…???
ሳሙኤል ሀይሌ
*…. ተሰደብኩኝ በሚል የፊትዎ ገጽታዎ እስኪለዋወጥ ድረስ ካስቆጣዎ እና ፓርላማ ውስጥ ጭምር ንዴትዎን መደበቅ አላስችል ካለዎት መንግስትዎ በሕይወት የመኖር ዋስትናቸውን ማስጠበቅ ባለመፈለጉ የተነሳ ቤተሰቦቻቸው ፊት ለፊታቸው በኦነግ ሽኔ ታርደው የተገደሉባቸው እና በዚሁ የተነሳ ህሊናቸው ውስጥ በሚኖረው ጭንቀት ዘወትር የሚሰቃዩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ምን ይበሉ ?
ርስዎ ሃላፊነትዎን ባለመወጣትዎ የተነሳ ተወልደው ካደጉበት መንደር ብሔራቸው ተለይቶ ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸዉ ፣ የአካል ጉዳተኛ የሆኑ እና የተፈናቀሉ ፣ በሃገራቸው ውስጥ ሆነው ሀገር አልባ የሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰደብኩኝ በሚል በብስጭት ናላዎ ሲዞር ሲመለከቱ ምን ይበሉ ?
መንግሥትዎ በሚከተለው ድብቅ የሆነ የሴራ ፖለቲካ የተነሳ ከሕግ አግባብ ውጭ ያለ ፍርድ ቤት መጥሪያ ወረቀት በየመንገዱ በአፋኝ ቡድንዎ ታፍነው ተወስደው የሚታሰሩ ፣ የሚደበደቡ ፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር የሚሰቃዩ ዜጎች በመሰደብዎ መበሳጨትዎን ሲያዩ ምን ይበሉ?
እርስዎን ስድብ የሚያምዎት ከሆነ ስለምን ለሌሎች ማሰብ ተሳነዎ? አማራ በመሆንዋ ባለቤቷ ፣ ወንድሟ ፣ እህቶቿ እና ልጆቿ ሁሉም ኦሮሞኛ በሚናገሩት ኦነግ ሽኔዎች ወለጋ ላይ ተገድለውባት ፣ ቤት ንብረቷን አውድመውባት ሰማይ ምድሩ የጨለመባት እና ዘወትር የምታነባ እናት ርስዎ በመሰደብዎ ሲበሳጩ አይታ ምን ትበል ?
ርስዎን ማንም ሰው እንዲሰድብዎ እንደማይፈቅዱ ሁሉ ምነው ዜጎችን ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆኑ ኦነግ ሽኔ የሚባሉ አካላት በየቀኑ ሲያርዳቸው ሲያፈናቅላቸው እና ሀገር አልባ ሲያደርጋቸው ለአራት ዓመታት በዝምታ መመልከት መረጡ ?