የፓርላማው አስቂኙና፣ አሰልቺ ውሎ…!!!
ግርማ ካሳ
የዶር አብይ አህመድ የፓርላማ ውሎ የፈጀውው ከ4 ሰዓት በላይ ነው፡፡ ቢያንስ ኢቢሲ ዩቱብ ገጽ ላይ ባስቀመጠው መሰረት፡፡ ባይገርማችሁ አትታዘቡኝና ትንሽ መስማት የምችልበትና ሁኔታ ስለነበረ፣ ሁሉንም ነው የሰማሁት፡፡ የነ ክርስቲያን ጥያቄ ስላስደሰተኝ፣ እስቲ እንደው ምን ብሎ ይመልስ ይሆን በሚል፡፡ የሚያሳዝነው ሰውዬ ምለስ ከመስጠት የባጥ የቅጡት ሲተረተር ነው የዋለው፡፡ በተለይም ክርስቲያን ታደለንና ዶር ደሳለኝ ጫኔ እየደጋገመ በመጥራት ሊያሸማቅቃቸው ሞክሯል፡፡
ያው እኛን ነው፣ ፌስቡከሮችና ዩ ተበሮችን አስር ጊዜ ነው ሲጠራ የነበረው፡፡ ሶያወግዘን፣ ሲከሰን ነበር፡፡ “ወሬኞች ናቸው፣ ሳንቱም የሚሰበሰቡ፣ ውሸት እያወሩ ሕዝብ የሚያሸብሩ …፣ ሲሰድቡኝ ነው የሚውሉት፣ እናቴንም ይሳደባሉ ወዘተ ” እያለ፡፡ ለ3፣ 4 ሰዓት ብቻ እየተኛሁ ፣ ሰባት ቀ በሳምንት ነው የምሰራው ያለው ጠቅላይ ሚኒስተር፣ የማይተኛው አብዛኛውን ጊዜ የሕዝብ ስራ እየሰራ ሳይሆን፣ ወይም ሶሻል ሜዲያ ላይ ቁጭ ብሎ እየተጣደ አሊያም ስልጠና ፣ የፓርላማ ንግግር በሚል ከሰዓታት ብቻውን እያወራ ስለሚወል መሆኑን መገመት አያስቸግርም፡፡
ወደ ውሎውም ስመለስ፣ በአንድ ጊዜ በርካታ የፓርላማ አባላት ጥያቈዎችና አስተያየቶ ሰጥተዋል፡፡ ለዚያ ወደ አንድ ሰዓት ገደማ ወስዷል፡፡ ከዶር ደሳለኝ ጫኔና ከአቶ ክርስቲያን ታደለ ወጭ ያሉት ያው የሙገሳና የዉዳሴ ናዳ ዶር አብይ ላይ ሲጭኑ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ኝ በዉዳሴያቸውው ውስጥ እየፈሩም ቢሆን መልካም ጥያቄዎች የጠየቁ አሉ፡፡ ያለፈው ጊዜ ለዶር አብይ ሲያስጨበጭብ የነበረው አቶ አሰማኽኝ አስረስ ፣ እድል በድጋሚ አግኝቶ ነበር፡፡ ጥርይ ጥያቄዎች ነው ያቀረበው፡፡ ፋኖ አገር ያዳነ ሆኖ እንዴት ፋኖ ላይ እርምጃ ይወሰዳል የሚል ነገር፡፡ ስለ ኑሮ ውድነት፣ የብር የመግዛት አቅም ወዘተ ተጠይቀዋል፡፡
አብይ አህመድ ምን አለፋችሁ ሳያቋርጥ ለሶስት ሰዓት ነበር የተናገረው፡፡ ንግግሩን በሶስት መክፈል ይችላል፡፡ የመጀመሪያው አንብቦ ይሁን ከዶር ምህረት ደበበ፣ ሳይካትሪስቱ የሰማውን (ያው ጓደኛሞች ስለሆኑ) ስለ ሃሳብ፣ ስለ ጊዜ አጠቃቀም፣ ስለ ቦታ (space) ፣ ስለ ስራ ወዘተ እየተናገረ የሳይኮሎጂ፣ ስነ ምግባር ስብከት ሲሰብክ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ሁለተኛው የርሱ አገዛዝ ዘመነ ተሰሩ ያላቸውን ቁጥር እየጠቀሰ የዘረዘረበት ነው፡፡ በግብርና፣ በትራንስፖርት፣ በቴሌኮሚኒኬሽን ወዘተ በጣም ትልቅ መሻሻሎች እንደተመዘገቡ ነው የገለጸው፡፡ የኑሮ ውድነቱን፣ ኢንፍሌሽኑን በተመለከተ፣ ከሌሎች አገሮች እንሻላለን በሚል እነ አርጀንቲናን፣ ቪኑዜላን፣ ሊባኖስን ….እንደ ምሳሌ አቅርቧል፡፡ ከቡና አንድ ቢሊዮን ዶላር፣ ከጓሮ አትልክት 83 ሚሊዮን ዶላር ውዘተ ተገኘ የሚል ሪፖርት ነው ያቀረበው፡፡ ጠቅላይ ሚኒጽሩ ያቀረባቸው ሪፖርቶች ምን ያህል እውነት ናቸው የሚለው በራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለው አንድ አራተኛ እንኳን እውነት ከሆነ በርግጥም ጥሩ ነገር ተሰርቷል ማለት ይችላል፡፡ ሆኖም በዉሸት የሚታወቅ መሪ እንደመሆኑ የሚያቀርበውን ሪፖርት ሰዎች ባያምኑት ብዙ አያስደንቅም፡፡ የተሰሩ መንገዶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ብትጠይቁ መረጃዎች ይታገኛላችሁ ብሏል፡፡ በዚያ መሰረት የዚህ መስሪያ ቤት ድህረ ገጽ ገብቼ ሳይ ጠቅላዩ የተናገራቸው መንገዶች ተጠቅሰው አላየሁም፡፡
ሶስተኛውና የመጨረሻ በዋናነት ስለ ሰለምና መረጋጋት፣ ከሕወሃት ጋር ስላለው ጦርነት፣ ዜጎችን ስለማቋቋም፣ እየተፈጸመ ስላለው አፈና፣ ስለ አሻጋሪነት፣ ስለ ፋኖ፣ ስልከ ተረኝነት፣ ስለ “አካም ፣ አካም” .።የተናገራቸው ብዙው ውሸት የሆኑ አስቂኝ አስተያየቶቹ ናቸው፡፡
በአማራ ክልል እየተወሰደ ያለው የአፈና መንግስታዊ የዉንብድና ተግባራትን በተመለከተ አብይ አህመድ መቶ በመቶ የአማራ ክልል አመራሮች ላይ አላኳል፡፡ እኔ የለሁበት ብሎ፡፡ ድርድሩን በተመለከተ ደግሞ ሽምጥጥ አድርጎ በመዋሸት፣ የተደረገ ድርድር የለም ብሏል፡፡ ድርድር ለማድረግ ዝግጅት እያደረኝ ነው፣ ለዚያም ኮሚቴ አቋቁመናል። ኮሚቴን የሚመራው ደግሞ ደመቀ መኮንን ነው” ብሎ በወልቃይትና በድርድሩ ዙሪያ አብይ አህመድ ራሱ እየሰራው የነበረው ሸፍጥ በደመቀ መኮንን ላይ አላኳል፡፡ እንግዲህ ይህ የሚያሳየው የአማራ ፖለቲከኞች ምን ያህል አብይ አህመድ እየተጫወተባቸው እንዳሉ ነው፡፡ አብይ አህመድ የተናገረው ውሸት መሆኑ ቢታወቅም፣ እነርሱ ውሸት ነው እስካላሉ ድረስ የአብይ አሀምድ ሐጢያትና ወንጀል የኛ ነው ብለው ለመቀበል ፍቃደኛ ሆነዋል ማለት ነው፡፡