ወቅታዊ መግለጫ!
በወለጋ ሰሞኑን ለተፈፀመው የንጹሃን አማሮች የዘር ጭፍጨፋ ግድያ ዋነኛ ተጠያቂው የብልጽግና መንግሥት ነው!!
ባለፉት ሁለት ቀናት በወለጋ ፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ፣ ከ360 በላይ ንፁሃን የአማራ ሴቶች፣ ህፃናት እና አዛውንት ላይ የዘር ጭፍጨፋ በኦነግ ሸኔ ተፈጸመ መባሉ፣በአንጻሩ ኦነግ ሽኔ ደግሞ ጭፍጨፋዉ የተፈጸመዉ መንግስት ባስታጠቃቸዉ ታጣቂዎች ነው የሚል ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን እየታዘብን ነዉ። በርካታ ከጭፍጨፋው ያመለጡ የአማራ ተወላጆች በየጫካው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ተሸሽገው እንደሚገኙ፣ በየጫካዉ ተገለዉ አስክሬናቸዉ ተጥሎ የሚገኘዉ ሟቾች ቁጥር ወደ አንድ ሽህ ሊጠጋ እንደሚችል ስንሰማ በከፍተኛ ሀዘንና ቁጭት ውስጥ በመኾን ነው። ይህን በንጹሃን ዜጎች ላይ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ያለ ግድያና ጭፍጨፋ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ገዥዉ የብልጽግና መንግሥት እንዲያስቆም ሲያሳስብና ሲጠይቅ ቆይቷል።
ባልደራስ ለዓለም አቀፉም ማኽበረሰብ በተለይም ለመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጽህፈት ቤት በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ወንጀል የ Genocide ምልክቶች እየታዩ እንደኾነ የሚያሳዩ መረጃዎችን በማቅረብ ሲያሳውቅና፣ ሲያሳስብ ቆይቷል። የኢትዮጵያ ህዝብም ድርጊቱን እንዲቃወምና መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጫና እንዲያደርግ ጥሪ ሲያስተላልፍ መቆየቱ የሚታወስ ነው። እንደዛም ኾኖ ፣ የግፍ ግድያውም ኾነ የዘር ማጥፋት ወንጀሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋና እየተባባሰ ቀጥሏል።
መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማስከበር ተቀዳሚ ተግባሩ ቢሆንም፣ በኦሮምያ ክልል ላለፉት አራት ዓመታት በአማሮች ላይ የዘር ፍጅት ሲፈጸም፣ የክልሉ መንግሥትም ሆነ ሃገሪቷን እየመራ ያለው የኦህዴድ መራሹ መንግሥት ሊያስቆሙት አልፈለጉም። እንዲያውም ሀገሪቷን እየመራ ያሉትና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አንድም ቀን የዘር ጭፍጨፋውን በተመለከተ ለህዝብ ጉዳዩን ለማስረዳትም ሆነ፣ የደረሰውን ከፍተኛ ሃዘን ሃዘናቸዉ እንደሆነ ሲገልጹ የተስተዋለበት ቀን የለም። ይባስ ብለዉ ለአማሮች ሲኦል በሆነበት በወለጋ ምድር ደማቸው እንደውሃ ሲፈስ ፣የሃገሪቷ መሪ እና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የእነዚህን ንጽህ ዜጎች ጉዳይ ከመንም ባለመቁጠር፣ የጎመንና ቃሪያ አትክልት ቦታ ሲጎበኙ በቴሌቪዥን እየታየ ነበር።
በኦሮሞ ህዝብ ሥም በተቃዋሚነትም ሆነ በክልል መንግሥትነት ተደራጅተው በሽፍታነትና በሰላማዊ ትግል እንታገላለን የሚሉት አብዛኞቹ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅትቶች ጭምር፣ ይህን አሰቃቂ የዚጎች እልቂት ሲቃወሙ አይታዩም። ይኽ የሚያሳየው፣ በኦሮሚያ የሚኖሩ ንጹሃን አማሮችን መጨፍጨፍ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች የተስማሙበት የጋራ አጀንዳቸው እንደሆነ ነው።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፣ይኽ ወገኔ፣ሀገሬ ብሎ በመላው ኢትዮጵያ ተሰማርቶ በሚኖረው የአማራ ህዝብ ላይ በወለጋና በምዕራብ ሸዋ እየደረሰበት ላለው የዘር ጭፍጨፋ ዋነኛ ተጠያቂ የሚያደርገው፣ ለዓመታት ጭፍጨፋውን ለማስቆም ፍላጎትም ሆነ ሁነኛ ቁርጠኝነትን ማሳየት ያልቻለውን ኦህዴድ መር የብልጽግና መንግሥትን ነው። በመሆኑም ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የንጹሃንን ሕይወት መታደግ ያልፈለገውንና በተዘዋዋሪም ጭፍጨፋውን እየመራ ያለውን የብልጽግና መንግሥት በጽኑ እያወገዘ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፤
1. መላው ሀገር ወዳድ የኦሮሞ ህዝብ በስሙ የሚነግዱ የፖለቲካ ነጋዴዎችን እና ጨፍጫፊዎችን እንዲያወግዘ፣ የንጹሃን ወንድሞቹ የአማሮች ደም መፍሰስ እንዲቆም ተቃውሞውን እንዲያሰማ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
2. የኦሮሞ ምሁራንና፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው ወገኞች ሁሉ ፣ ይህንን በአማራ ወንድሞች ፣ሴቶች እና ህጻናት ወገኖቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ኢሰብኣዊ የዘር ማጥፋት ፍጅት፣ ሌላ የማያባራ የእርስ በርስ ጥላቻና ጦርነት መዘዝ ከመቀስቀሱ በፊት ፣ አውግዘው፣ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
3. መላው የአማራ ህዝብ ይህንን በህልውናው ላይ የመጣውን ጥፋት በተደራጀ እና በተቀናጀ ሁኔታ እንዲቃወመውና ብሎም እንዲታገለው ጥሪ እናቀርባለን፡፡
4. መሠረታዊ የሆነውን የንፁሃን ዜጎችን ሕይወት መታደግ ያቃተውን መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚችለው አቅሙና ጉልበቱ ሁሉ በሰላማዊ ህዝባዊ መንገድ ተቃዉሞዉን እንዲያሰማ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በመጨረሻም ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፣ በወገኖቹ እልቂት አንጀቱ አሮ እየተብሰለሰለ ላለው ስልጡኑ የአዲስ አበባ ነዋሪ ህዝብ በብልጽግና መንግስት ላይ ያለዉን ተቃውሞ ሰላማዊ በሆነ በማናቸዉም መንገድ እንዲያሰማ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ግፍን እንጂ ግፈኞችን አንፈራም!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፣
አዲስ አበባ
ሰኔ 13/2014