>
5:21 pm - Thursday July 21, 8050

የአማራ ብልፅግና አመራሮች ከፊልሰን አብዱላሂ ምን ተማራችሁ? (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ)

የአማራ ብልፅግና አመራሮች ከፊልሰን አብዱላሂ ምን ተማራችሁ?

/ር በቃሉ አጥናፉ

 

ፊልሰን አብዱላሂ የቀድሞዋ የኢፌዴሪ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ከሲንን ጋዜጠኛ ከላሪይ ማዶዎ ጋር ጥር 28/2022ዓ.ም ቃለ መጠየቅ አድርጋ ነበር፡፡  ፊልሰን አብዱላሂ ከአብይ አስተዳደር በፈቃድዋ የለቀቀችበትን ምክንያት በህሌናዋ ላይ ጫና በሚያሳድሩ ጉዳዬች ምክንያት እንደሆነ ገልፃለች፡፡ በመቀጠልም በአብይ አስተዳደር ምክንያት የሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ እንደሚያሳስባት ገልፃ ‘’የአብይ አስተዳደር ሁኔታውን ማስተካከል/ማከም እንደማይችሉ እና ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ አሳስባለች፡፡’’ 

ፊልሰን አብዱላሂ በወጣትነት እድሜዋ ምቾት እና ድሎት ህሌናዋን ያላናወዘው፣ ለህሌናዋ ያደረች ድንቅ ኢትዮጵያዊት ነች፡፡ ለሰላሳ ዓመታት (በኢህአዲግ እና በብልፅግናው መንግስት) ተረኞችን የምታገለግሉ አመራሮች ከዚች ወጣት ኢትዮጵያዊት ወሳኔ ምን ተማራችሁ? 

አማራ በግሪደር ሲቀበር፣ እህቶች ሲታፈኑ፣ አፈር ጭሮ የሚያድር ገበሬ በማንነቱ ሲፈናቀል፣ ሲገደል፣ ህፃናት ሲታረዱ፣ ማህፀን ውስጥ ያለ ፅንስ በማንነቱ ተፈርጆ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደል፣ ሰው በህይወት ሲቃጠል፣ ንብረቱ ሲወድም የወገኖቻችሁ ደም አይከረፋችሁም፤ የዜጎች ሰቆቃ አይሰማችሁም፤

የኦሮሞ የለውጡ አጋፋሪዎች ቀሪውን አማራ(በህወኃት መራሹ የኢህአዲግ ስርዓት ካፈናቀሉትና ከገደሉት በተጨማሪ) ከኦሮሚያ ምድር ለማፅዳት የኦነግ ሰራዊት ትጥቁን ሳይፈታ ከኤርትራ ምድር እንዲገባ የተደረገበት ምክንያት አማራውን ከኦሮሚያ ምድር ለማስወገድ እና በድርጊቱ የፖለቲካ ባለስልጣናቱ ተጠያቂ እንዳይሆኑ ነው፡፡ የኦሮሞ ብልፅግና እና የኦነግ ሰራዊት/ኦነግ ሸኔ ተናበው በጋራ እንዲሚሰሩ የአደባባይ ሚስጥር ሁኖ እያለ የአማራውን ህዝብ እንወክላለን ብላችሁ ስልጣን ወስዳችሁ ህዝባችሁን የምታስጨርሱ የብልፅግና አመራሮች በተለይ የአማራ ብልፅግና ዝምታችሁ ከተጠያቂነት እንደማያድናችሁ አውቃችሁ እንደ ፊልሰን አብዱላሂ ሚናችሁን ብትለዩ መልካም ነው፡፡

በወገናችሁ ሞት ሹመት ለተቸራችሁ፣ በሰዎች ልጆች ደም ለገዥዎች አሽከር በመሆን ከርሳችሁን ለሞላችሁ፣ ከግፍ ፈፃሚዎች ጋር የምትለዩት በስም እንጅ በግብር አይደለም፡፡ በንፁኃን ላይ የሚፈፀመውን ሰቆቃ አይታችሁ እንዳላያችሁ፣ሰምታችሁ እንዳልሰማችሁ እየሆናችሁ በጠቅላዩ ዙሪያ የተኮለኮላችሁ የብልፅጋና ባለስልጣናት በህግና በታሪክ ተጠያቂ የምትሆኑበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

Filed in: Amharic