>

በአማራ ደም ላይ የሚሰነዘሩ ቧልቶች (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

በአማራ ደም ላይ የሚሰነዘሩ ቧልቶች

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ


በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ አማሮች ላይ የሚካሄደው የዘር ማፅዳት እና ማጥፋት ዘመቻ በኦህዴድ ከፍተኛ የመንግስት አመራር አካላት አቅጣጫ ሰጪነት በእቅድ የሚፈጻም ለመሆኑ ብዙ ጠቋሚ ምልክቶች አሉ። 

እነዚህ የዘር ማፅዳት እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ለሰላሳ አንድ ዓመታት የተካሄዱ ሲሆን በተለይ ላለፉት አራት ዓመታት በተወሰነ የጊዜ ርቀት ሲፈፀሙ ቀይተዋል፡፡ ድርጊቶች ከተፈፀሙ በኃላ  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለተጠቂዎች ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት ከሚሰነዘሩ የፖለቲካዊ ቧልቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

  • የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የፀጥታ ኃይል በኦነግ ሸኔ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን አስለቀቀ፣
  • የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኦነግ ሸኔን ደመሰሰ፣
  • በኦነግ ሸኔ ላይ የፀጥታ ኃይሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፣
  • የሸኔ የታችኛው አመራር ተመታ፤ተገደለ፣
  • የኦነግ ሸኔ የተሸነፈ ኃይል ተስፋ ቆርጦ እየሸሸ እያለ በንፁኃን ላይ ጥቃት አደረሰ፣
  • የአማራ እና የኦሮሚያ የክልል ፕረዘዳነቶች አብረው መግለጫ ይሰጣሉ(የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት አብሮ የኖረ ወንድማማች ህዝብ ነው እያሉ ዲስኩራቸውን ይነዛሉ)፡፡ ፖለቲከኞች ለያዩት እንጅ ህዝቡ ወንድማማች እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ከግድያው በኃላ የሚወጡ መግለጫዎች ከእውነተኛ ፍላጎት ላይ የተመሰረት እንዳልሆነ ጥሬ ሃቅ ነው። ከወንጀሉ በኃላ የሚወጡ መግለጫዎች የዜጎችን የቁጣ ስሜት ለማብረድ ድውያን ፖለቲከኞች የሚጠቀሙበት ቁማር ነው፡፡ ስለዚህ የአማራ ህዝብ እና የአማራን ህዝብ ህመም የሚጋሩት ኢትዮጵያውያን ዛሬም እንደ ትናንቱ ቁጣን አሰምቶ መመለስ ሳይሆን መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ መታገል ነው፡፡ የስርዓት ለውጥ ተደርጎ ህገ መንግስቱ እስከሚቀየር ድረስ እነዚህ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፡

1ኛ. የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ያልቻለ መንግስት ስልጣኑን እንዲያስረክብ፤

2ኛ. በአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን እንዳለው ሁሉ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል  ክልሎች የአማራ ልዩ ዞኖች እንዲፈጠሩ እና ከክልሉ ውጭ የሚገኙ አማራዎች እራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት እድል እንዲፈጠር ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በደራ፣ በአሶሳ፣ በወለጋ፣ በድሬዳዋ፣ በአዳማ፣ በጉራ ፈርዳ፣ እና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ አማራዎች እራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ንቅናቄ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ትግሉ መቀጠል አለበት፡፡ ያለበለዚያ እነርሱም በሞታችን እየቀለዱ እኛም እያለቀስን እንኖራለን፡፡

Filed in: Amharic