እያስደመሙኝም፣ እያሳዘኑኝም ካሉ ነገሮች በጥቂቱ…?!?
ያሬድ ሀይለማርያም
1ኛ/ እንዴት እንዲህ ያለ ከባድ ችግር በአገር ደረጃ ሲደርስ የመንግስት ሃላፊዎች ሕዝቡን ለማረጋጋት፣ የተጎዱትን ለማጽናናት፣ አሁን ባአደጋ ውስጥ ያሉትን ለመታደግ፣ የታወቀውን ያህል ስለ ጉዳቱ መጠን፣ ስፋትና ሁኔታ እና በቀጣይ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥ ይጠፋል?
2ኛ/ የሟቾችን ቁጥር ከ400 እስከ 1600 የሚጠቅሱ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ዘገባዎች ወጥተዋል። በጭፍጨፋው ስንት ሰው ነው በትክክል የሞተው፣ ስም፣ እዴሜና ጽኦታቸውን፣ ከቀበሌው ሕዝብ ስንት ተረፉ የሚለውንስ መንግስት ለምንድን ነው ይፋ የማያደርገው? ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ካሉ ለምን ይሄንኑ ለሕዝብ አያሳውቅም?
3ኛ/ ሶማሌ ፑንት ላንድ ገበያ ተቃጠለ ብለው ሊያጽናኑ ማቅ ለብሰው፣ አውሮኘላን ተሳፍረው እና የእዝን ይዘው ጎረቤት አገር የነጎዱ ሚንስትሮች እግራቸው ስር ይሄ ሁሉ ሰው ሲረግፍ የት ገቡ?
4ኛ/ በጠአት ከሚቆጠሩና ድምጻቸውን ካሰሙት በቀር በሰብአዊ መብት እና በበጎ አድራጎት ሥራ ስም ፈቃድ አውጥተውና ቢሮ ከፍተው የሚንቀሳቀሱ በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችስ ምነው እንደሚኒስትሮቹ አፋቸው ተለጎመ? በየሆቴሉ ድንኳን ጥሎና አጀንዳ እያሽሞነሞኑ የወርክሾኘ ድግስ ከማሳደድ ባለፈ አገር እንዲህ ጭንቅ ውስጥ ስትወድቅ እንዴት ዝምታን ትመርጣላችሁ? መላ መፍጠሩ ቢከብድ ነፍስ ይማር ማለትና ለሞቱት ሻማ ማብራት እንዴት ያቅታል?
5ኛ/ የሕዝብ መገናኛ ብዙሀን ባለሥልጣን እገሌ አስነጠሳቸው የሚመስል ዜና ስትሰሩ እያዋላችሁ ይህ የውጭ ሚዲያዎች ጭምር ደጋግመው የዘገቡትን ሰቅጣጭ ግድያ ባላየ ማለፋችሁ ምነዋ? ነውርም፣ ማፈርም ቀረሳ? አንዳንዱ ጉዳዩ የማያልፈው ሲሆንበት የሚያቀርበው ትንታኔ ጋዜጠኝነት ከካድሬነት ጋር ሲጋባ ምን እንደሚመስል ዘግናኝ ገጽታውን ማሳያ ነው። አንድ የቀድሞ የኢሳት ጋዜጠኛ የመንግስት ‘ዝምታ ገዳዬቹ እንዳይደሰቱ ከማሰብ ነው’ የሚል የቀነጨረ ጋዜጠኛ ትንታኔ ሲሰጥ ከመስማት በላይ ምን ይሰቀጥጣል። መንግስት የአማራ ክልል ሹሞች ሲገደሉ፣ ወንድማችን አጫሉ በግፍ ሲገደል ሀዘኑን ሳይውል ሳያድር ምርር ባለ መንገድ የገለጸው እንደዚህ ጋዜጠኛ ትንታኔ ከሆነ ገዳዮቹን ለማስደሰት ነው?
‘ማፈር ድሮ ቀረ’ አሉ የኔታ