>

በደብረ ብርሃንና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ተቋረጠ (ጌጥዬ ያለው)

በደብረ ብርሃንና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ተቋረጠ

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አማራ ተማሪዎች እየታደኑ እየታሰሩ ነው
ጌጥዬ ያለው

በምዕራብ ወለጋ የቀጠለውን የአማሮች የዘር ጭፍጨፋ ተከትሎ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የአማራ ተማሪዎች ቁጣቸውን እየገለፁ ይገኛሉ። ቁጣውን ለማፈን የአገዛዙ ታጣቂዎች በንፁሃን ተማሪዎች ላይ    ተኩስ እስከ መክፈት የደረሰ የሃይል እርምጃ እየወሰዱ ነው። በዚህም ምክንያት በተለያዩ ዩኒበርሲቲዎች የትምህርት ማቆም አድማዎች ተጀምረዋል።
ደብረ ብርሃን እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬ ሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ መደበኛ ትምህርት ማስተማራቸውን እንዳቋረጡ ከሥፍራው ምንጮች ያደረሱን መረጃ አረጋግጧል።
በተመሳሳይ በሰላሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በርካታ የአማራ ተማሪዎች እየታደኑ እየታሰሩ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ሦስት የአማራ ተማሪዎች ማሕበር (አተማ) አመራሮች በጎንደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረዋል።
የአተማ የገንዘብ አስተዳድር ዘርፍ ኃላፊው ተማሪ ሰምረአብ አየለ፣ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ አፈ ጉባኤ የሆነው ተማሪ መኳንንት ሙላት እና የአተማ አባላት ጉዳይ ኃላፊው ተማሪ ኤርሚያስ ጥጋቤ በጎንደር ከታሰሩት መካከል ናቸው። ሰምረአብ ዓይነ ስውርና የሕግ ተማሪ ሲሆን መኳንንት ደግሞ የማስተርስ ተማሪ መሆኑ ታውቋል።
ተቃውሞውና የትምህርት ማቆም አድማው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ ዩኒቨርሲቲዎች ይቀጥላል።
Filed in: Amharic