የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ መግለጫ…!!!
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር
ከሰሞኑ እርሳቸው በሚመሩት ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ስለተፈጸሙ ግድያዎች እና ጥቃቶች እንዲሁም ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 20፤ 2014 ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ለተፈጸሙ ጥቃቶች በፓርላማ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን “ሸኔ” ተብሎ የሚጠራውን ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል።
ይህ ኃይል ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ አካባቢ ጥቃት የፈጸመው፤ ደምቢ ዶሎ፣ ጊምቢ፣ ጋምቤላ እና ሌሎች ከተሞችን ለማጥቃት ያቀደው ዕቅድ “ስለከሸፈበት” እና የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት “ትልቅ እርምጃ” “ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት ነው” ብለዋል። “[ሸኔ] ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች ስለተያዙበት፤ ፍላጎቶቹን ማሳካት ወደማይችልበት ደረጃ እያወረድነው ስለመጣን፤ ህዝባችንን ልቡን ለመስበር፣ ኢትዮጵያን ለማድማት፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማፍረስ አቅዶ ንጹሃን ላይ እርምጃ ወስዷል” ሲሉም አማጺውን ቡድን ወንጅለዋል።
የምዕራብ ወለጋው ጥቃት ያነጣጠረው በክልሉ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በጉሙዝ ተወላጆች እና ኦሮሞዎች ላይ ጭምር የተፈጸመ እንደሆነ ርዕሰ መስተዳድሩ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል። “ይሄ ኃይል በጣም አሳፋሪ ተግባር፣ መቼም የኢትዮጵያ ታሪክ የማይረሳው፣ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ የጥቁር ጥቁር ጠባሳ ሆኖ የሚቆይ ተግባር ፈጽሟል። እየፈጸመም ይገኛል” ሲሉ አቶ ሽመልስ የሰሞኑን ግድያ በጠንካራ ቃላት አውግዘዋል።
“ይህ ኃይል ባለፉት ወራት ሲደረግ በነበረው ኦፕሬሽን ጸጥታ ኃይሉን መቋቋም አልቻለም። ጸጥታ ኃይሉን መቋቋም ስላልቻለ formless [ቅርጽ የለሽ] ሆኖ እየተሽሎከለከ፣ እየተደበቀ ነው ጥቃት እየፈጸመ ያለው። በንጹሃን ላይ፣ በእኛ አመራሮች ላይ፣ በጣም አሳዛኝ እርምጃዎችን እየወሰደ፤ የሽብር ተግባር እየፈጸመ ነው ያለው” ሲሉም አቶ ሽመልስ ከስሰዋል።
“የሽብር ጥቃት የተወሰነ መሳሪያ፤ የጸጥታ አካል የሌለበት ቦታ ብቻ ነው የሚፈልገው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ጥቃት ፈጻሚው ቡድን በጸጥታ ኃይሎች እና በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን በመጠቀም “የሽብር ተግባራት” እንደሚፈጽም ገልጸዋል። “ሀገራችን ሰፊ ነው። የተቋማት ግንባታችን ገና ነው። ያለን የጸጥታ ኃይል ውሱንነቶች አሉበት። የመንግስት መዋቅሩ በደንብ ተጠናክሮ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ አልደረሰም። ይህ ኃይል እነዚህን ዕድሎች ነው እየተጠቀመ ያለው። ይህንን ለመቀልበስ ተግተን ልንሰራ ይገባል” ብለዋል። (