>

የስርዓቱ አስጨናቂ የስንታየሁ ቸኮል መልዕክት ከባሕር ዳር ሰባታሚት ወህኒ ቤት

የስርዓቱ አስጨናቂ የስንታየሁ ቸኮል መልዕክት ከባሕር ዳር ሰባታሚት ወህኒ ቤት

ጌጥዬ ያለው

ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈፀመው እልቂት በእጅጉ አሳዝኖናል። መንግሥታዊ ድጋፍ ባለው የሽብር ቡድን በደረሰው የዘር ፍጅት ካለንበት የግፍ እስር ቤት ሆነን ሞታቸው ሞታችን ሆኖ ተሰምቶናል። ልባችን ሬሳቸው ወድቆ የጅብ መጫዎቻ በሆነበት ጫካ ይንከራተታል። ለመፍትሔው ምን ማድረግ እንዳለብን የጠቆመን እልቂትም ነው።
በኦሮሚያ ያለው ኦነግ፤ ኦሮምኛ ተናጋሪ ቦኩሀራም እንደሆነ ማናችንም ልንገነዘብ ይገባናል። በናይጀሪያ የሚታወቀው ገዳይ ቡድን በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በሽብርተኝነት የተፈረጀባቸው መስፈርቶች ቢፈተሹ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው አራጅ ቡድን ከሚያደርጋቸው ፈቀቅ ያሉ አይደሉም። ይህ የእልቂት ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ቦኩሀራም ነው። ከናይጀሪያ አቻው የሚለየው ስርዓታዊና ተቋማዊ በሆነ መልኩ በመንግሥት የሚደገፍ መሆኑ ነው። ስንቅና ትጥቅ የሚሰፈርለት ከመንግሥት በጀት መሆኑ ነው።
በአማራ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ጭፍጨፋ በዓለም ታሪክ አሸባሪዎች ሊፈፅሙ ከቻሉት ሁሉ በዘግናኝነቱ ቢልቅ እንጂ አያንስም። ይህንን ዘመቻ የሚመሩት ደምቢዶሎ ወይም ወለጋ የተቀመጡ የሽብር ቡድኑ አባላት አይደሉም። አራት ኪሎ እምዬ ምኒልክ ቤተመንግሥት ያሉ በሕግ አውጭው ፓርላማ እውቅና የተሰጣቸው ጠቅላይ ሚንስትር ናቸው። ለዚህ ማሳያው ከተጨፈጨፉት ከ1 ሺህ 5 መቶ በላይ አማሮች ይልቅ ደንታ የሰጣቸው ችግኝ ተከላ መሆኑ ነው። በፓርላማ ጥሪ ከማድረግ ጀምሮ የጭፍጨፋው ቀጥተኛ ተሳታፊ ናቸው።
የአብን አመራሮች ጉዳዩን ለውይይት ሲያቀርቡት አሻፈረኝ ያለው ፓርላማም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኑ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ያሳያል። የአማሮች እልቂት የመንግሥት እገዛ እንዳለው ሌላኛው ማረጋገጫ ነው። ችግሩ ከባድ ነው።
መፍትሔው አርበኛ መሆን ነው! ለትግል መነሳት ነው። እጅ ለእጅ መያያዝ ነው። መፍትሔው ለሕዝባዊ አመፅ መነሳት ነው። ከዚህ አንፃር ከሰሞኑ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና በሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም ዛሬ በባሕር ዳር ሕዝብ ዘንድ የታየው ትንቅንቅ እጅግ የሚበረታታ ነው።
 የተከፈተብንን የእልቂት ዘመቻ እናስቆመዋለን፤ እንቀለብሰዋለንም። ይህንን የምናሳካው በአባቶቻችን መንገድ በመሄድ ነው!
ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. 
ባሕር ዳር፤ ሰባታሚት ወህኒ ቤት
Filed in: Amharic