ላለመሞት መሞት
ከአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) የተሰጠ መግለጫ
በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የአማራ ተማሪዎች ባለፉት 4 ዓመታት በተለይም ደግሞ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በወለጋ አማራዎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ እያሰሙ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጅ አገዛዙ በሰላማዊ ተማሪዎች ተደጋጋሚ ድብደባ፣ ወከባ እና አፈና ሲደያርስ የቆየ ሲሆን ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የማህበሩ አመራሮችን ጨምሮ 5 ተማሪዎች ‹‹ዐመጽ ቀስቅሳችኋል›› በሚል ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በጎንደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ይገኛሉ፡፡ የታሰሩት ተማሪዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
1. ሠምረ አብ አየለ፤ የማህበሩ ሒሳብ ሹም
2. ኤርሚያስ ጥጋቤ፤ የማህበሩ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ
3. መኳንንት ሙላት፤ የጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ
4. ሌሎች 2 የአማራ ተማሪዎች ናቸው
በተያያዘ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ግቢ ተማሪዎች እና የህክምና ባለሙያዎች በሰላማዊ መንገድ ድምጻቸውን ለማሰማት ቢሞክሩም በጭስ ቦንብ መታፈን፣ ተኩስ እና ድብደባ ደርሶባቸዋል፡፡ በሌሎች ግቢዎችም ድብደባ ሲፈጸም ውሏል፡፡
በአጠቃላይ አገዛዙ ባደረጋቸው ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴውን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየወሰደው ይገኛል፡፡ በዚህም ለሚፈጠር ማንኛውም ክስተት ሃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን በድጋሜ እየገለጽን ትግሉ የኅልውና በመሆኑ ትግላችንን አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን እንገልጻለን፡፡
አተማ፤ የአማራ ትውልድ ተቋም!
ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም