አስደናቂው አዛውንት በወለጋ!!
22 ቤተሰብ የተገደለባቸው አዛውንት፣ 7 ወላጆቻቸው የተገደሉባቸውን ህፃናት እየተንከባከቡ ናቸው!!
ለአል ዐይን አማርኛ
በወለጋ የቶሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሐመድ የሱፍ፣ 22 ቤተሰብ በአንድ ቀን እንደተገደለባቸው ለአል ዐይን አማርኛ ተናገሩ፡፡
አቶ መሐመድ የሱፍ የአራት ቀን እመጫት ልጃቸው ከእነ ልጇ በጥይት መገደሏን ያነሱ ሲሆን፤ ገዳዮቹ ህጻኗን እንኳን አለመተዋቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ መሐመድ ልጆቻቸው ከእነልጅ ልጆቻቸው መገደላቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የመጀመሪያና ሶስተኛ ልጆቻቸው እስከ ልጅ ልጆቻቸው አምስት፤ አምስት ሆነው መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛዋ ልጃቸው ከሶስት ልጆቿ ጋር፤ እመጫቷ ልጃቸው ከሁለት ልጆቿ ጋር፤ ሌላኛዋ ልጃቸው ከአንድ ልጇ ጋር፣ በቅርቡ የተዳረችው ልጅ፣ እንዲሁም አንድ ወንድ ልጅም እንደተገደሉባቸው ነው የገለጹት፡፡
አቶ መሐመድ በአጠቃላይ ስድስት ልጆቻቸው እና 16 የልጅ ልጆቻቸው መገደላቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የቀበሯቸውም እራሳቸው እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ የራሳቸውን ቤተሰቦችን ጨምሮ በአጠቃላይ 60 ሰዎችን መቅበራቸውን ይናገራሉ።
ከሟቾች ባለፈም የቆሰሉ ስድስት ልጆች እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡ አንደኛዋ ልጃቸው አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንደሄደች ገልጸዋል፡፡ አዲስ አበባ የሄደችው ልጃቸው፣ “እግሯ ይቆረጥ ወይስ አይቆረጥ?” እየተባለ መሆኑን ተናግረዋል።
የአቶ መሐመድ የሱፍ ፣ 22 የቤተሰብ አባላትን ከአሳጣቸው ግድያ የተረፉት በቆሎ ማሳ ውስጥ ገብተው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው በቆሎ ማሳ ውስጥ ገብተው የተደበቁት፣ ገዳዮቹ ሴት እና ልጅ አይገድሉም በሚል ግምት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አሁን እናታቸውም አባታቸውም የተገደሉባቸውን ሰባት ልጆች ይዘው እዛው ቶሌ ቀበሌ መቀመጣቸውንና መሸሽ አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡