>
5:18 pm - Wednesday June 15, 9205

ባሌ ውስጥ ሮቤ ከተማ በ22 ሚሊዮን ብር ወጪ የመታሰብያ ሐውልት የቆመለት “ጄኔራል” ዋቆ ጉቱ ማነው?  አቻምየለህ ታምሩ

ሌ ውስጥ ሮቤ ከተማ በ22 ሚሊዮን ብር ወጪ የመታሰብያ ሐውልት የቆመለት “ጄኔራል” ዋቆ ጉቱ ማነው? 

አቻምየለህ ታምሩ


ኢትዮጵያ ውስጥ የቆመው የኦሮሙማ አፓርታይዳዊ አገዛዝ ቁንጮ  የሆነው በላዔ ሰብዕ ዐቢይ አሕመድ ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ባሌ በማቅናት እነ ዋቆ ጉቱን የነጻነት ታጋዮችና አርበኞች አድርጎ በማቅረብ፣ በአማርኛ ስለኢትዮጵያ በሚያሰማው ለጆሮ የሚስቡ ዲስኩሮቹ የሚያጠልቀውን ጭንብሉን ሮቤ ላይ በማውለቅ፣ በኦሮምኛ ስለነዋቆ ጉቱ ‹ጀግንነት› የኦነጋውያንን ዲስኩር በመድገም ማንነቱን አሳውቆ ነበር። ይህን የሰሙ የአርሲና ባሌ ቄሮዎች ባለፉት ሳምንታት ኦሮሞ ባልሆነው ወይም ኦሮሞ መሆን የለበትም በሚሉት የኅብረተሰባችን ክፍል ላይ የተካሄደውን ፍጅትና የዘር ማጥፋት ያካሄዱት የዋቆ ጉቱ ልጆች (Ilmaan Waqqo Gutuu) ነን በማለት ዋቆን እንደ ኦሮሞ አርበኛ በመቁጠር ነበር። በሌላ አነጋገር ፍጅቱና የዘር ማጥፋቱ የተካሄደው ዐቢይ አሕመድ መንግሥታዊ ባደረገው ትርክት በተመሩ ቄሮዎች ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ኦሮምያ የሚባለው በኢትዮጵያ እምብርት ላይ የበቀለው እባጭ አበጋዝ የኾነው ሽመልስ አብዲሳ ወደ ባሌ አቅንቶ ባሌ ውስጥ በሮቤ ከተማ  በ22 ሚሊዮን ብር አስገነባነው ያለውን የዋቆ ጉቱ የመታሰብያ ሐውልት መርቋል። ሽመልስ አብዲሳ ሐውልቱን መረቅኹ ባለበት ወቅት ባደረገው ንግግር ዋቆን  “ለሕዝቦች ነፃነት እና እኩልነት መስዕዋትነት የከፈለ የኦሮሞ ጀግና” ሲል አሞካሽቶታል። ሽመልስ አብዲሳ መስዕዋትነት እንደከፈለ አድርጎ ያቀረበው  ዋቆ ጉቱ  ከ.ኦ.ነ.ግ ጋር ተጣልቶ ይኖርበት በነበረው ናይሮቢ ከተማ ለወራት ታምሞ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በ83 ዓመቱ ሰኞ ጥር 26 ቀን 1995 ዓ.ም. በተፈጥሮ ምክንያት በሚደርስ ሞት ምክንያት ሕይዎቱ ያለፈውን አዛውንት ነው።

ለመሆኑ ዐቢይ አሕመድና ሽመልስ አብዲሳ  እንደነገሩን ዋቆ ጉቱ የኦሮሞ የነጻነት ታጋይና አርበኛ ነበርን? እስቲ ዶሴው ይውጣና ዋቆ ጉቱ በኢትዮጵያ ላይ በተለይም በቦረና የኦሮሞ ጎሳዎች ላይ ምን እንዳደረገ ታሪኩ ይመርመር።

እንደሚታወቀው የኦ.ነ.ግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ባለፉት አርባ ሰባት ዓመታት ፖለቲካቸው፣ በፈጠራ ታሪክ ላይ ተመስርተው ኢትዮጵያን በቅኝ ገዢነት፣ ዳግማዊ ምኒልክን በወራሪነትና በጨፍጫፊነት፣ ሰፊውን የአማራ ሕዝብ ደግሞ በጨቋኝነት በመፈረጅ በነዚህ ጠላት ባደረጓቸው አካላት ላይ የዘር ማጥፋት እየፈጸሙ ከአማራ የፀዳ ሀገር የመመሥረት የሚያስችል ትግል ነው ያደረጉት። በርግጥ በፈጠሩት የውሸት ትርክት ላይ ተመሥርተው በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ሲያካሂዱ ብቻቸውን አልነበሩም። የኦ.ነ.ግ ፕሮግራም አቀንቃኞች እንደ ትግል አርአያነትና ታሪካዊ መነሻ ወደኋላ የሚያማትሩት የአርሲ ጎሳ ተወላጁ ዋቆ ጉቱ ባሌ ውስጥ የዚያድ ባሬ እንደራሴ ሆኖ ለኦሮሞ ሳይሆን የታላቋን ሶማሊያ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ መሳሪያ ሆኖ የተንቀሳቀሰበትን አመፅ ነው። ዋቆ ጉቱ በዚያድ ባሬ እየታገዘ የሃይማኖት ወንድሞቼ አይደሉም ባላቸው ክርስቲያንና ዋቄፈና እምነት የሚከተሉ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች ላይ ያካሄደውን ውጊያ እንደ ተራማጅ እንቅስቃሴ የሚቆጥሩት የኦ.ነ.ግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ብቻ አይደሉም።

የኢትዮጵያ የግራ ፖለቲከኞች ሁሉ «ገበሬው በፊውዳሉ ሥርዓት ላይ በተለያየ ጊዜና ቦታ እያመፀ በመነሣት መብቱን ለማስከበር፣ ሥርዓቱንም ለመደምሳስ ታግሏል፤ በተለይ በባሌ ያካሄደው የነጻነት ትግል በአርአያነት የሚጠቀስ ነው» ብለው ያልነበረ ‹የገበሬ አመፅ› ፈጥረው እስካሁን ድረስ ሳያፍሩ ይናገራሉ፤ ከሚጽፉት አልፎም መታሰቢያ እስከማቆም ሁሉ ደርሰዋል። የዚህ ዓይነቱ ትርክት ዋቆ ጉቱንም ሆነ የኢትዮጵያ ገበሬ ያልሆነውን ሆነ፣ ያልፈጸመውን ፈጸመ እያሉ ለማሞገስና እንዲሁም ለሚቀጥለው ትውልድ ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ ዛሬም እንደነዋቆ ለጠላት ዓላማ ተሰለፍ ብሎ ለመቀስቀስ ካልሆነ በስተቀር በባሌም ሆነ በሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ ገበሬው በዘመኑ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ላይ አምፆ ለውጥ ለማምጣት ታግሎ ነበር የሚያሰኝ አንዳች እንቅስቃሴ አልነበረም።

በ1950ዎቹ ዛሬ ሶማሊያ የሆነው ሀገር በኢትዮጵያውያ መሪዎች ተጋድሎ ከቅኝ ግዛት ተላቆ «የሶማሊያ ሕዝብ ሪፑብሊክ» ተብሎ ነጻነትን አግኝቶ ከተቋቋመ በኋላ «ታላቋን ሶማሊያ» እንመሰርታለን የሚል ዓላማ አዲሱ መንግሥት በመንደፍ «የሱማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሰዎች የሰፈሩበት አካባቢ ሁሉ የሶማሊያ መሬት ነው» የሚል የተሳሳተ አቋም ላይ በመመርኮዝ ኦጋዴንና የባሌን ምሥራቃዊና ደቡባዊ ክፍል ወደ ሶማሊያ ለማጠቃለል የቀየሰውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲረዳው የተወሰኑ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ባላባቶችንና ልጆቻቸውን በገንዘብና በጦር መሳሪያ በመርዳትና በማደራጀት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ብረት እንዲያነሱ አደረገ። ለዚህ እንቅስቃሴ ጥሩ መሳሪያና አገልጋይ ሆኖ የተገኘው ዋቆ ጉቱ የሚባል የአርሲ ጎሳ ተወላጅ የሆነ የባሌ ባላባት ነው፡፡ ዋቆን ሞቃዲሾ ድረስ ወስደው በገንዘብ በመደለል በእሱ መሪነት የተወሰኑ ጭሰኞቹን አሰልጥነውና አስታጥቀው በሽፍትነት የቦረናና ጉጂ ጎሳዎችን እንዲወጉና ሰላም እንዲደፈርሱ ወደ ባሌ ጫካ አሰማሯቸው።

ይህ «የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጥ ሽፍቶች ተወሮ ሲያዝ ኃይሉ ስለሚዳከም በቀላሉ በኦጋዴን ላይ ወረራ በማድረግ በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋለን፤ ታላቋን ሶማሊያም እንመሰርታለን» ብለው የሶማሊያ መሪዎች የቀየሱትን የባዕድ የወረራ እቅድ ለማስፈጸም የተደረገ እንቅስቃሴ ነበር እንጂ ሲነገረን እንደኖርነው የኢትዮጵያ ገበሬዎች በተለይም ደግሞ የኦሮሞ ገበሬዎች ለነጻነትና ለመብት መጠበቅ ያካሄዱት ትግል እንዳልነበር ታሪኩን የመረመረ ሁሉን ያውቀዋል። የሶማሊያ መንግሥት አራት የማሰልጠኛ ጣቢያዎችን አቋቁሞ ሲያበቃ በዋቆ ጉቱ እየተመለመሉ የሚቀርቡትን የዋቆ ጭሰኞች እያሰለጠነና እያስታጠቀ የሶማሊያን ፍላጎት ለማሟላት ኢትዮጵያን በተለይም በጠቅላይ ግዛቱ የሚገኙ የኦሮሞ ጎሳዎችንና ዋቆ የሃይማኖት ወንድሞቼ አይደሉም፣ ከብቶቼን ወስደዋል ያላቸውን ቦረናዎች ወጋ፣ የባሌን አካባቢ ፀጥታ አደፈረሰ፣ በነዋሪው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ፣ በተለይ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ከፍተኛ ፍዳና መከራ አስከተለ።

የባሌ ገበሬዎች አመፅ መሪ ተደርጎ የሚቆጠረው ዋቆ ጉቱ ምንም እንኳ ተወልዶ ያደገው ባሌ ቢሆንም በመሠረቱ ግን ትውልዱ የአርሲ ጎሳ ነው። ዋቆ ጉቱ የቃልቻ ዘር በመሆኑ የአርሲ ጎሳዎች ያመልኩበት ነበር። ተወልዶ ያደገው ባሌ ውስጥ ወለቦ ከምትባለው መንደር ሲሆን ከወላጅ አባቱ ከአቶ ጉቱ ኡሶ ጋር አብሮ ሲኖር ይተዳደሩ የነበረው በከብት ርቢ ስለነበር ግጦሽ ፍለጋ ከአባቱ ጋር ወደ ቦረና አውራጃ ይዘዋወር ነበር። አባቱ ሲሞቱ ከወንድሙ ከግራዝማች ጨምሪ ጉቱ ጋር አብሮ መኖር ጀመረ። ወንድሙ ‹‹አባ ቆሮ›› የሚባል የጎሳቸው ባላባትነት ስለነበረው አንድ ወቅት የባላባትነቱን ሥራ እንዲሰራ ውክልና ሰጥቶት ነበር። ዋቆ ጉቱ በውክልና የባላባትነት ሥራ ከያዘ በኋላ ውክልና የሰጠውን የወንድሙን ባላባትነት ይቀማና በስሙ አዛውሮ ለራሱ በማድረግ አሻፈረኝ በማለት እምቢተኛ ሆነ።

በዚህ ምክንያት ወንድሙ ከሶት ብዙ ጊዜ ከተሟገቱ በኋላ በገንዘብ ኃይል ዋቆ ጉቱ ስላሸነፈ የአባ ቆሮ ባላባትነቱን ይዞ መኖር ጀመረ። ነገር ግን ይዞታው በገንዘብ ኃይልና በተጭበረበረ ሁኔታ እንጂ በሐቅ ስላልሆነ ነገሩ በሽምግልና ታይቶ ሽማግሌዎቹም ባላባትነቱን ያላግባብ ለተነጠቀው ለወንድሙ እንዲመልስ ስለወሰኑበት በሽማግሌዎቹ ውሣኔ መሠረት ለወንድሙ ለማስረከብ ተገደደ። ይህ በሆነ ጊዜ ከወንድሙ ይለይና በከብት አርቢነት ዘመኑ ወደሚያውቀው ነገሌ አካባቢ ኩርኩር ወደሚባለው ቦታ ሄዶ መኖር ጀመረ። ዋቆ ከወንድሙ በውክልና የተሰጠውን ባላባትነት ለመንጠቅ ሲል ይሟገት በነበረበት ወቅት ከብቶቹን ሽጦ ገንዘቡን በጉቦ አባክኖ ጨርሶ በድህነት ላይ ወድቆ ስለነበር ለመሸፈት በዝግጅት ላይ ሳለ ለመሸፈት የሚገፋፋው አንድ ነገር በመሀሉ ላይ ተፈጠረ። ታሪኩ እንደሚከተለው ነው፡-

ዋቆ ጉቱ ከብቶቹን ሁሉ ሽጦ በድህነት ይኖርበት ከነበረው ከቦረና በታች በጠረፍ በኩል በከብት አርቢነት ኑሯቸውን የሚገፉ ሱማሌያዎች ይኖሩ ነበር። እነዚህ የሱማሌ ጎሳዎች የኢትዮጵያ ሱማሌያዎች ሲሆኑ ጎሳቸው መሪኻንና ዲጎድያን ነው። እነዚህ ሁለት ጎሳዎች እንደ ማንኛውም አርብቶ አዳሪ ማኅበረሰብ የጥንት ይዞታቸውን እያለፉ የቦረናዎች ይዞታ ወደሆነ መሬት እየገቡ ከብቶቻቸውን ሳር ያበሉ ውኃ ያጠጡ ነበር። ይህ እየተደጋገመ በመምጣቱና በመለመዱ እንዳሻቸው በፈለጉ ጊዜና ሰዓት እየወጡና እየገቡ ውኃ በሚያጠጡበትንና ሳር በሚያግጡበት መሬት የተነሣ ሁለቱ ጎሳዎች ከቦረናዎች ጋር መጋጨት ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ቦረናዎች ስብሰባ አድርው «በላይ በኩል ጉጂ የሚባሉት ጎሳዎች ወደታች እየወረዱ ያጣብቡናል፤ በታች በቆላው ያሉት ሱማሌያዎች ደግሞ ይዞታቸው ከፊልቱ በታች ሆኖ ሳለ አሁን ፊልቱን አልፈው የኛን ይዞታና ርስታችን ከሆነው ምድር ገብተው ከማስቸገር አልፎ ከርስታችን የሚፈልቀውን ውኃ እያጠጡና የበቀለውን ሳር ከብቶቻቸውን እያስጋጡ የኛ ከብቶች እንዲራቡና እንዲጠሙ አደረጉብን፤ ስለዚህ ሱማሌዎች ፊልቱን አልፈው ወደኛ መሬት እንዳይገቡ በጥንቱ ይዞታቸው ጸንተው እንዲኖሩ ይደረግልን» ሲሉ ለጠቅላይ ግዛት እንደራሴው ለራስ አንዳርጋቸው መሳይ አመለከቱ።

ጠቅላይ ግዛቱም ነገሩን በጉባዔ ዐይቶ ሱማሌዎቹ የጥንቱ ይዞታቸውን አልፈው ከቦረናዎች ርስትና ይዞታ ገብተው እንዳይሰፍሩ፣ የሰፈሩ ቢኖሩ እንዲለቁ ወደፊትም ፊልቱን አልፈው ወደ ቦረናዎች መሬት እንዳይገቡ ብሎ ወሰነላቸው። ይህ ውሳኔ በተሰጠበት ቦታ ሱማሌዎች ብቻ ሳይሆን የቦረና ጎሳዎች ያልሆኑት አርሲዎቹ እነ ዋቆ ጉቱም ይኖሩበት የነበረ ቦታ ነው። ሱማሌያዎቹ የጠቅላይ ግዛቱን ውሳኔ አክብረው የቦረና ጎሳዎችን መሬት ለቀው ወደቦታቸው ሲመለሱ የአርሲ ጎሳዎቹ እነ ዋቆ ጉቱ ግን «እኛ ሱማልያዎች አይደለንምና ልንለቅ አይገባም» በማለት ተከራከሩ። በዚህ ጊዜ የቦረና ጎሳዎች እነ ዋቆን ለጠቅላይ ግዛቱ ከሰሱ። ጉዳዩን የተመለከተው ጠቅላይ ግዛቱም በሰጠው መልስ «ቦረናዎች ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ተመስርቶ የተላለፈው ውሳኔ ጎሳ ሳይለው በሁሉም ላይ የተሰጠ ስለሆነ ባለርስቶቹ ሳይፈቅዱ በሰው ቦታ ላይ ማንም ሊቀመጥ አይገባም፤ ስለሆነ እናንተም ወደ ርስታችሁና ወደ ጥንት ይዞታችሁ ተመለሱ» ብሎ ወሰነባቸው።

ይህን ውሳኔ በመተላለፍ በዋቆ ጉቱ አደፋፋሪነትና ምክር ሰጭነት የተሰባሰቡ የተወሰኑ የአርሲ ጎሳ አባላትና ጭሰኞቻቸው ቦታውን አንለቅም በማለት ለቦረናዎች የተላለፈውን ውሳኔ በመጋፋት ተቀመጡ። በዚህ ጊዜ ቦረናዎችና ጀምጀሞች በአንድ ላይ ሆነው መንግሥት ለሰጠው ውሳኔ አንታዘዝም ብለው በተቀመጡ ሰዎች ላይ ጦርነት ከፍተው ከሀያ በላይ የሚሆኑ የአርሲ ጎሳ አባታትን ገደሉ። ዋቆ ጉቱ ፊትም የወንድሙን ባላባትነት ሊነጥቅ ባስነሳው ሙግት ሀብቱን ጨርሶ ከድህነት ላይ የወደቀ ስለሆነ ኋላም መንግሥት የሰጠውን ትእዛዝ አልቀበልም ብሎ በሱ ሐሳብ የሚመሩትን ባላገሮች አደፋፍሮ ከቦታው እንዳይነሱ አድርጎ በማቆየቱ ምክንያት ጦርነት ተከፍቶ ከሀያ በላይ ሰዎች እንዲሞቱ ስላደረገ፣ እንዲሁም በሙግቱ ጊዜም ከሽያጭ ተርፈው የነበሩትን ከብቶች ቦረናዎች ዘርፈው ስለወሰዱበት በ1957 ዓ.ም. በመስከረም ወር በግልጽ ወደ ሽፍትነት ገባ። ዋቆ ሲሸፍት አብሮ ይዟቸው ጫካ ካስገባቸው ሰዎች መካከል ድንበር እየተሻገሩ የቦረናዎችን መሬት በመያዛቸው በጠቅላይ ግዛቱ እንዲለቁ በመታዘዛቸው ቅሬታ የፈጠረባቸው አንዳንድ የሶማሌ ጎሳ አባላትን ጭምር ይዞ ነው።

በመስከረም ወር 1957 ዓ.ም. የዋቆን መሸፈት የሰማው የሶማሊያ መንግሥት፣ ዋቆ ጉቱ ሸፍቶ ከተቀመጠበት ገናሌ ወንዝ ድረስ መሐመድ ሳላ የተባለውን የመሪኻን ጎሳ የሆነ ሰው ልኮ ወደ ሶማሊያ መጥቶ የሃይማኖት ወንድሙ ከሆነው የሶማሊያ መንግሥት የፈለገውን ያህል የጦር መሳሪያ ወስዶ በጦር የወጉትንና የሃይማኖት ጠላቶቹም ጭምር የሆኑትን የቦረና ጎሳዎች እንዲወጋና መሀል ባሌ ድረስ ገብቶ ያሻውን እንዲዘርፍ ማደፋፈሪያ ሰጠው። ዋቆም የሃይማኖት ወንድሞቼ ከሚላቸው የሶማሊያ መንግሥት ባለሟሎች የመጣለትን ልመና ተቀብሎ ወደ ሱማሊያ ገብቶ ከሱማሊያ መንግሥት መጀመሪያ አርባ ሁለት፣ ለሁለተኛ ጊዜ አምስት መቶ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ ከስድስት መቶ በላይ ጠመንጃ፣ አምስት ሞርታርና ሁለት ባዙቃ ከነ ሙሉ ጥይቱና አሰልጣኝ መኮንኖች ጋር ላከለት።

በመቀጠል የሱ ግብረአበሮች የሆኑትን አደም ጂሎና አልዬ ጭሪ ወደ ሶማሊያ ሄደው ሦስት መቶ ጠመንጃ ተቀብለው እንዲመጡ አደረገ። ከዚህ በኋላ አደም ጂሎ ብቻውን ሄዶ አራት መቶ ጠመንጃና ልኩ ያልታወቀ ፈንጂ ተቀብሎ ወደ ዋቆ ዕዝ ተመለሰ። ለሦስተኛ ጊዜ ዋቆ ሎጉ የሚባል ግብረአበሩ ሁለት መቶ ሰባ ጠመንጃና አምስት ሌጀራ መትረየስ ከሶማሊያ መንግሥት ተቀብሎ ተመለሰ። የሶማሊያ መንግሥት ይህንን ሁሉ ትጥቅና ስንቅ ለዋቆ ጉቱና ግብረአበሮቹ ያስታጥቅ የነበረው ዋቆን የሃይማኖት ወንድሙ አድርጎ የዋቆ የሃማኖት ጠላቶች ባላቸው ዜጎች ላይ በጋራ በባሌ ጠቅላይ ግዛት ለሚያካሂዱት የወረራ ዘመቻ ነበር። እነ ዋቆ የሶማሊያ መንግሥት የሚሰጣቸውን መሳሪያ የሚረከቡት ሶማሊያ ግዛት ውስጥ ሊክ ከሚባለው ቦታ እየሄዱ ከጄኔራል አፊያ እጅ ነው። ከሶማሊያ ግዛት እየተነሣ በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ እየገባ እነዚህና ሌሎች ትጥቆችን የሶማሊያ መንግሥት እንደሚሰጣቸው በማባበል እነዋቆን ወደ ጄኔራል አፊያ ይልካቸው የነበረው ከፍሲል ስሙ የተጠቀሰው መሐመድ ሳላ ነው። እንግዲህ! ለአርነትና ለነጻነት እንደተካሄደ ትግል ተቆጥሮ ላለፉት አርባ አራት ዓመታት ሲነገርለት የነበረው የነዋቆ አመፅ የቦረና ጎሳዎችን በመውጋት የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን የግዛት ጥያቄ ለማሳካት በዚህ መልክ በቅንጅት ይሠራ በነበረበት ወቅት በመሳሪያነት ያገለገሉበትን ዘመን ነው።

ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የጀመረችው በ1956 ዓ.ም. መሆኑና በዚህም ጦርነት ድል ሁና መመለሷ ቢታወቅም ዋቆ ጉቱ ኢትዮጵያና ሱማሊያ በግልጽ መጣላታቸውን አይቶ የቀረበለትን ጥያቄ ሳያመነታ በመቀበል የሶማሊያ መንግሥት መሳሪያ ለመሆን ግብረ አበሮቹን ይዞ የገባው በ1957 ዓ.ም. ነው። በሌላ አነጋገር በ1956 ዓ.ም.

የተካሄደው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጦርነት ባይፈጠር ኖሮ ዋቆ የሚባል በታሪክ የሚወሳ ሰው አይኖርም ነበር። ዋቆ የሚባል ስም በታሪክ ሊነሣ የቻለው ሶማሊያ የኢትዮጵያን ግዛት ወርራ ከያዘች በኋላ ከኢትዮጵያ ግዛት በኃይል ተሸንፋ እንድትወጣ ስትገደድ የኢትዮጵያ ጠላትነቷ ጥያቄ ውስጥ ባለመውደቁ እሷን ተገን አድርጎ ጦርነት በመክፈቱ ነው። በፊት ለፊት ጦርነት የተሸነፈው የሶማሊያ መንግሥት እነ ዋቆን በደስታ ተቀብሎ ዋቆ በግጦሽ ምክንያት የተጣላቸውን ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ወንድሞቼ አይደሉም ያላቸውን የቦረና የኦሮሞ ጎሳዎችን ለመውጋት የሸመቁትን ግብረ አበሮቹን ሁሉ ስለጦር መሳሪያ አፈታትና አገጣጠም እንዲሁም ስለፈንጂ አጠማመድ ካሰለጠነ በኋላ «የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር» የሚል ድርጅት መስርቶላቸው ዋቆ ጉቱን «የምዕራብ ሶማሊያ ጄኔራል» ብሎ የግንባሩ መሪ አድርጎ ማዕረግ ያደለው ሲሆን በሥሩ ያሉት አመፀኞች ደግሞ ሻለቃ የሚል ማዕረግ ተሰጣቸው።

ልብ በሉ! ዋቆ ጉቱ «ጄኔራል ዋቆ» እየተባለ የሚጠራውና አዲስ አበባ ውስጥ የጄኔራል ዋቆ ጉቱ ትምህርት ቤት ተብሎ የተሰየመለት የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ያለውን የግዛት ባለቤትነት ጥያቄ ለማስፈጸም «የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር» የሚል ድርጅት ፈጥሮለት የዚህ ድርጅት መሪ አድርጎ ሲሾመውና ለወራት የተሰጠውን ሥልጠና አጠናቆ «የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር»ን እየመራ ወደ ኢትዮጵያ ለግዴታ ሲሰማራ በተሰጠው ማዕረግ ነው።

ለወትሮው ጄኔራልነት ከተራ ወታደርነት እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት፣ ከልጅነት እስከ አዛውንትነት ከሀገር ጠላት ጋር ሲዋጋና ሲተናነቅ ለኖረ፣ እግሩን ለጠጠር፣ ግንባሩን ለጦር ለሰጠ የሀገር ባለውለታ ሀገር የምትሰጠው ማዕረግና የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ለተከፈለ መስዕዋትነት መታሰቢያ ተደርጎ የሚቀርብ ነበር። እነ ዋቆ ግን ጄኔራል እየተባሉ የሚጠሩት ኢትዮጵያ በሰጠቻቸው ማዕረግ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጠላት ሀገር ያላትን የግዛት ጥያቄ በእጃዙር ለማግኘት ስትል «የምዕራብ ሶማሊያ ነጻነት ግንባር»ን መሥርታ ላሰማራቻቸው ቅጥረኞች በሰጠቻቸው ማዕረግ ነው። ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ዋቆ ጉቱን በማረኩት ወቅት ዋቆ ይዞት የተገኘው የሶማሊያ መንግሥት የሰጠው ባለ ማኅተም መታወቂያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ «General of Western Somalia» ይላል። ለዚህ የምዕራብ ሶማሊያ ጄኔራልነቱ ነው እንግዲህ አዲስ አበባ ውስጥ «ጄኔራል» ተብሎ ትምህርት ቤት በስሙ የተከፈተለት።

እንደ ዋቆ ሁሉ ሞቃዲሾ ቤተ መንግሥት የሰለጠኑት ወያኔዎችም የትግራይ ሪፑብሊክን ለመመሥረት ጫካ ከገቡ በኋላ ሻዕብያን ተከትለው አዲስ አበባ ሲገቡ ኢትዮጵያን ሲያደሙ ለኖሩ የትግራይ የገበሬ ሽፍቶች «ጄኔራል» የሚል ወታደራዊ ማዕረግን ያደሏቸው በተመሳሳይ እሳቤ ነው። እነ ዋቆ ጄኔራል የተባሉበትና እነ ሳሞራ ጄኔራል የተባሉት አገልግሎት አንድ ዓይነት ነው። እነ ዋቆ ኢትዮጵያን ይወጉ የነበረው በምሥራቅ ነው። እነ ሳሞራ ደግሞ ኢትዮጵያን የወጉት በሰሜን ነው። ሁለቱም ጄኔራል የተባሉት ከተራ ወታደርነት እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት፣ ከልጅነት እስከ አዛውንትነት ከሀገር ጠላት ጋር ሲዋጉና ሲተናነቁ ስለኖሩ አይደለም። ጄኔራል የተባለው ዋቆ ጉቱም ሆነ ጄኔራል የተባሉት የፋሽስት ወያኔ የገበሬ ሽፍቶች ጄኔራል የተባሉት ለኢትዮጵያ ስለተዋጉ ሳይሆን ኢትዮጵያን ስለወጉ ነው። ኢትዮጵያን ሲወጉ ኖረው ለኢትዮጵያ የተዋጉላትን ማዕረግ የተላበሱት ሀገርና መንግሥት ስለሌለን ነው። ይህ ተግባር የየካቲት 12 መታሰቢያ ሐውልትን አፍርሶ በቦታው ለፋሽስቱ መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒና ለሩዶልፎ ግራዚያኒ ሐውልት ከማቆም አይተናነስም።

ወደነዋቆ ታሪክ ስንመመለስ ዋቆ ራሱ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1965 ዓ.ም. በተናገረው ቃል መሠረት ወደ ጫካ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በ1962 ምሕረት ጠይቆ በሌተናት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ አማካኝነት ምሕረት ተደርጎለት እስከገባበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ላይ ከፍ ያለ በደል ሲፈጽም የኖረ ሰው መሆኑን ስላመነ ጄኔራልነት ሊያሰጥ የሚያስችል ተግባር እንደሌለው ራሱ ምስክር ነው። እንግዲህ ዋቆ ጉቱ ሸፍቶ በባሌ ጫካ ገብቶ የሃይማኖት ወንድሞቼ አይደሉም ያላቸውን ቦረናዎችን የወጋውና የሶማሊያን መንግሥት የተስፋፊነት ፍላጎት ለማስፈጸም የረጋውን የኢትዮጵያ ፀጥታ ሲያደፈርስ የነበረው፣ ከዚህ በላይ በተገለጠው ምክንያት እንጂ የኦሮሞ ብሔርተኞቹ እነ ዐቢይ አሕመድ እንደሚሉት የባሌ ሕዝብ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ተበድሎ ለሕዝቡ በደል ተቆርቋሪ ሆኖ አይደለም።

ባጭሩ ዋቆ ጉቱ የሶማሊያ መንግሥት ቅጥረኛ ሆኖ በሀገሩ ላይ ለመዝመት የበቃው «የቦረናዎችን ርስት ይዘህ ለመኖር አይገባህም፤ ወደርስትህ ገብተህ ተቀመጥ» ተብሎ ሲበየንበት የቦረናዎችን ርስት ቀምቼ ካልተቀመጥኩ ብሎ በመቃወም ከቦረናዎች ጋር ጦር ገጥሞ ሲሸነፍ እነሱን ለመውጋት ሲል ነው ጫካ የገባው። ግብረአበሮቹ እነ አደም ጂሎ፣ አልዩ ጭሪና ዋቆ ሌጉ ደግሞ የሸፈቱት በዋቆ ጉቱና ከሶማሊያ መንግሥት ተወክሎ በመጣው በመሐመድ ሳላ ስብከት ተስበው ወዲያውም የጦር መሳሪያ ለማግኘት ሲሉ ነው። ከዚህ ውጭ በባሌ ምድር የወቅቱ ኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝባዊ በደል አድርሶ እነ ዋቆ ያንን ለመቃወም የመሩት አመፅ የለም። ይሁን እንጂ የምንኖርበት ዘመን የሚያኮሩን የነበሩ ነገሮች ሁሉ ተዋርደው፣ ልናፍርባቸው በሚገቡ ወራዳ ተግባሮች የምንኮራበት ዘመን ስለሆነ እንጂ ከፍ ሲል እንዳየነው የዋቆ ተግባር እንኳን ሐውልት ሊቆምለት ቀርቶ በሀገር ክህደትና በፈጃቸው ቦረናዎች ነፍስ ሊወገዝ የሚገባው ሰው ነበር። ከዚህ ውጭ የዋቆ ጉቱ ታሪክ የነጻነቱ አንዱ አካል የሆነውን የቦረናን የመሬት ባለቤትነት መብት ለመግፈፍ እንጂ ለሕዝብ መብት ለመታገል ጫካ እንደወረደ የሚያሳይ አንዳች ታሪክ የለውም።

እንግዲህ! እነ ራስ ጎበና ዳጬና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ በተፈጠሩበት ሀገር በኦነጋውያንና በኦሮሞ ብሔርተኞች ሁሉ ‹የኦሮሞ ጀግና› እየተባሉ ሲሞካሹ የሚውሉት እነ ዋቆ ጉቱ ከጎሳቸዉ እና ከሃይማኖታቸዉ ውጭ ያለውን ሌላውን ኦሮሞ ጭምር በኢትዮጵያ ጠላቶች እየታገዙ ሲወጉና ሲፈጁ የነበሩ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገር በቀል ወኪሎች ናቸው። የዋቆ ጉቱ ልጆች ነን ያሉት የባሌና የአርሲ ቄሮዎችም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የዘር ማጥፋትና ፍጅት ሲያካሂዱ የሰነበቱት ልክ እንደ ዋቆ ጉቱ ሁሉ በነገድና በሃይማኖት እኛን አይመስሉም ባሏቸው ክርስቲያኖችና አማሮች ላይ ነው። ዋቆ ጉቱ የሶማሊያ ቅዠት መሳሪያ ሆኖ በነገድና የሃይማኖት ወንድሙ ባደረገው በሶማሊያ መንግሥት እየታገዘ በሃይማኖት አይመስሉኝም ባላቸው ላይ ያካሄደው ዘመቻና ፍጅት ቢወገዝ ኖሮ ዛሬ በስሙ የሚምሉ ወጣቶች በነገድና በሃይማኖት አይመስለንም ባሉት ላይ የዘር ጅፍት ለማካሄድ ባልተነሱ ነበር።

ከላይ የቀረበው ታሪክ ምንጮች፡- የሲ.ኤይ.ኤው ሰላይ ፖል ሄንዚ እ.ኤ.አ. በ1985 ዓ.ም. «Rebels and Separatists in Ethiopia: Regional Resistance to a Marxist Regime» በሚል ያሳተመው የራንድ ኮርፖሬሽን ሪፖርት፣ በሪሁን ከበደ በ1993 ዓ.ም. ያሳተሙት «የዐፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ» መጽሐፍ፣ ጆን ማርካኪስ እ.ኤ.አ. በ1987 ዓ.ም. «National and Class Conflict in the Horn of Africa» በሚል ያሳተመው መጽሐፍ፤ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ በ2006 ዓ.ም.

ያሳተመው «እኛና አብዮቱ» የሚለው መጽሐፍ፣ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ «ጃገማ ኬሎ የበጋው መብረቅ (የሕይዎት ታሪክ) በሚል ጄኔራል ጃገማ ኬሎን ቃለ መጠይቅ አድርጎ በ2001 ያሳተመው የታሪክ ማስታወሻ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረው አበራ ቀጸላ፣ ዋቆ ጉቱን አዲስ አበባ ውስጥ ቃለ መጠይቅ አድርጎ «The Rebellion in Bale (1963–1970)» በሚል በ1963 ዓ.ም. ያዘጋጀው የዲግሪ ማሟያ ወረቀት፣ ማሪናና ዴቪድ ኦቶዋይ የተባሉ ተመራማሪዎች «Ethiopian Empire in Revolution» በሚል እ.ኤ.አ. በ1978 ዓ.ም. ያሳተሙት መጻሕፍና ፕሮፌሰር ተሬ ኦስቴቦ በቅርቡ Islam, Ethnicity, and Conflict in Ethiopia The Bale Insurgency, 1963-1970 በሚል እ.ኤ.አ. በ2020 ዓ.ም. የሳተሙት መጽሐፍ ናቸው።

ከላይ የታተሙት ምስሎች ዋቆ ጉቱ “የምዕራብ ሶማሊያ ጀኔራል” በሚል ይጠራ እንደነበርና በጀኔራል ጃገማ ኬሎ ሲማረክ የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ናቸው።

Filed in: Amharic