>

ስንታየሁ ቸኮል በአማሮች ላይ የተፈፀመን ጅምላ ጭፍጨፋ በማጋለጥ በሽብር ተወነጀለ! (ጌጥዬ ያለው)

ችሎት

• ስንታየሁ ቸኮል በአማሮች ላይ የተፈፀመን ጅምላ ጭፍጨፋ በማጋለጥ በሽብር ተወነጀለ

• ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታ ፍርድ ቤት ቢወስንም ፖሊስ ከለከለ

•ፖሊስ ታዴዎስ ታንቱን ያልፈታበትን ምክንያት ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ አዝዟል

ጌጥዬ ያለው

አቶ ስንታየሁ ቸኮል ዛሬ ሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት ቀርቧል። ፌዴራል ፖሊስ ሐሰት በሽብር ወንጅሎታል። “የአማራ ብሔር ሳይጨፈጨፍ በጅምላ እንደተጨፈጨፈ አድጎ በፌስቡክ መረጃ በማሰራጨት፣ ፋኖን መደገፍ እና የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች እዲደረጉ ማነሳሳት” የሚሉ ውንጀላዎችንም አቅርቧል። በዚህ ጉዳይ ይኸው የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ከፍቶበት በአማራ መስተዳድር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከራክረው በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቱን ጠበቃው ሔኖክ አክሊሉ ጠቅሰው ተከራክረዋል። ፖሊስ ስንታየሁ ባሕር ዳር በነበረበት ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረቡንም ፈፅሞ እንደማያውቅ ተናግሯል። የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠውም ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ያሳለፈበት ዶሴ መዝገቡ ተያይዞ እንዲቀርብ ለሀምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር   ዋስትና ከእስር እንዲፈታና ክሱን በውጭ ሆኖ እንዲከራከር የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ወስኗል። ሆኖም ፖሊስ ውሳኔውን አክብሮ ሊፈታው አልቻለም።

በተመሳሳይ ፖሊስ አዛዎንቱን ጋዜጠኛ እና የታሪክ ጸሐፊ ጋሽ #ታዴዎስ ታንቱን ለምን ከእስር እንደማይፈታ ችሎት ቀርቦ እንዲያስረዳ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ወንጀል ችሎት አዝዟል። ጋሽ ታዴዎስ በ15 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ቤት ወጥተው የተመሰረተባቸውን የሽብር ክስ በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ከተወሰነ ቀናት ቢቆጠሩም ፖሊስ ውሳኔውን ሽሮ እንዳሰራቸው ይገኛል።

በሌላ ዜና ከትናንት በስቲያ ፍርድ በባሕር ዳር የታሰረው ጋዜጠኛ #ወግደረስ ጤናው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ቢኖርበትም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አልቀረበም። የፌዴራል ፖሊስ አባላት እስከሚወስዱት በባሕር ዳር በአደራ እስረኛነት እንደሚቆይም ተነግሮታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አባላት ኩራባቸው ገብሬ እና ናትናኤል የአለም ዘውድ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር ተፈተዋል። ሌላኛው አባል አለም ደመቀ (አሌክስ ሸገር) ደግሞ ታስሯል።

 

Filed in: Amharic