ጠ/ሚ/ሩ በፓርላማ “በቀጣይ የሚያሰጋን አዲስ አበባ ነው” በማለት የወለጋን አጄንዳ ለማስቀየር ሞከሩ!!
ባልደራስ
*… “ሰው እየሞተም የሞተበት ቦታ ችግኝ እንተክላለን ቢያንስ አስከሬኑ ጥላ እንዲኖረው…!!!!”
በከፊል የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚደገፈው ኦነግ-ሸኔ በወለጋ በአማራዎች ላይ እየፈፀመ ያለውን የዘር ማፅዳት በተመለከተ ማብራሪያ ለመስጠት በፓርላማ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት የሌላቸው በርካታ ጉዳዮችን አንስተዋል። በአዲስ አበባ ስድስት የሽብር ጥቃቶች ተሞክረዋል ሲሉም ተደምጠዋል።
ጠ/ሚ/ሩ በከተማዋ የሚኖሩ አንዳንድ የእስልምና እምነት ተከታዮችን በሽብር ድርጊቱ ሞካሪነት ወንጅለዋል።
“ሙስሊም ነኝ ብሎ ጀለብያ ለብሶ ቦምብ ይወረውራል። በዚህ ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ 6 የሽብር ሙከራ አክሽፈናል። ባንዳው ሸኔ ብቻ አይደለም። አዲስ አበባም ባንዳ አለ፤ በየመጅሊሱ የሚሸቅል ማለት ነው” በማለትም ገልፀዋል።
“በቀጣይ የሚያሰጋን አዲስ አበባ ነው። ለገጣፎ ላይ ብቻ 55 አሸባሪ ትናንት ይዘናል። አዲስ አበባ በየቀኑ ቦምብ እየያዝን ነው” ሲሉም በከተማዋ ኗሪዎች ላይ ጭንቀትን የሚያባብስ አባባል ጨምረዋል።
በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የዘር ፍጅት የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ስለመሆን ወይም አለመሆኑ፤ ብሎም መንግሥታቸው ጅምላ ጭፍጨፋውን መቼና እና እንዴት እንደሚያስቆመው ለቀረበላቸው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማፅዳት “የንፁሃን ሞት” በማለት አድበስብሰውታል።
“እናንተ በየሳምንቱ መርዶ ትሰማላችሁ። እኛ ግን በየቀኑ፤ በየሰዓቱ እንሰማለን” በማለትም ለመገናኛ ብዙሃን ያልደረሱ ሌሎች ጅምላ ጭፍጨፋዎች እንዳሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ሽብር በኢትዮጵያ ብቻ ያልተከሰተ፤ ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ ለወለጋው የአማራ ጭፍጨፋ የዘገባ ሽፋን መስጠቱን በአሉታዊ ገፅታ በማቅረብ፣ በተለይ አሜሪካን ከፍተኛ የሽብር ሰለባ አስመስለው አብራርተዋል። በኒውዮርክ፣ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በፊላደልፊያ፣ በቺካጎ ወ.ዘ.ተ. የሽብር ጥቃቶች በተደጋጋሚ እንደሚፈፀሙ ጠቅሰዋል። በመሆኑም በኢትዮጵያም ቢፈፀም አይደንቅም የሚል አንድምታ ያለው መደምደሚያ ሰጥተዋል።