>

የዘር ፍጅት የታወጀባቸው አማራዎች የጭፍጨፋ ዶሴ ሲገለጥ....! (አሳዬ ደርቤ)

የዘር ፍጅት የታወጀባቸው አማራዎች የጭፍጨፋ ዶሴ ሲገለጥ….!!!

አሳዬ ደርቤ


*….ትውልድና ታሪክ ሊረሱት የማይገባ ግፍ (መንግስታዊ የዘር ማጽዳት ) በታሪክ ሰነድ ተሰንዴ ሊቀመጥ የሚገባው!!

➔ጃዋር መሐመድ ተከብቤያለሁ ያለ ቀን 86 አማራዎች ተገደሉ፡፡

➔አርቲስት ሐጫሉ የተገደለ ቀን 350 አማራዎች ተጨፈጨፉ፡፡

➔በቤኒሻንጉል ክልል በመተከል ዞን በ2013 ዓ.ም ብቻ በኦነግና በጉምዝ ታጣቂዎች 2,980 አማራዎች ሲገደሉ 411 ዜጎችን አካል ጉዳተኛ ሆኑ፡፡ 408 ሕጻናትም ወላጅ አልባ ለመሆን ሲገደዱ፣ 216,980 ዜጎች ደግሞ ተፈናቀሉ፡፡

➔በ2012 ዓም ወደ ደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ያመሩ 17 ሴት ተማሪዎች ወደ ትውልድ ቀያቸው በመመለስ ላይ ሳሉ ተሰወሩ፡፡

➔በወርሐ ጥቅምት መጀመሪያ 2013 ዓ.ም መከላከያ ሠራዊቱ እንዲወጣ በተደረገ ቅጽበት ለስብሰባ የተጠሩ ከ287 በላይ የጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አማራዎች አንድ እንኳን ለመሀላ ሳይተርፍ ሁሉም ተጨፈጨፉ፡፡ የክልሉ መንግሥትም የተወሰነውን አስከሬን ማንነት ቀይሮ ኦሮሞዎች ቢያደርጋቸውም ጭፍጨፋውን ግን መካድ አልተቻለውም፡፡

➔ሚያዚያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም ያለማንም ከልካይ ወደ ኤፍራታና ግድም ወረዳ ያመራው የኦነግ ታጣቂ አጣዬን አውድሞ ከ265 በላይ አማራዎችን ገደለ፡፡

➔በወርሐ ሕዳር 2013 ዓ.ም ከባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ 7 ሹፌሮች “አሊ ዶሮ” ላይ በኦነግ ታግተው ተገደሉ፡፡ ተሸከርካሪዎቻቸውም ተቃጠሉ፡፡

➔ከሕዳር 20-21 2013 ዓ.ም፡- በምስራቅ ወለጋ ሊሙ ወረዳ አርቁምቢ መንደር በምሽት ቃጠሎ መነሳቱን የሚገልጽ እሪታ  ሰምተው እሳቱን ለማጥፋት ከወጡ አማራዎች መሃከል 38 ንጹሐን ሲገደሉ በርካቶች ቆሰሉ፡፡

➔ሕዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም በዚሁ ዞን እና ወረዳ ውስጥ በሪሶ ቀበሌ ከ27 በላይ አማራዎች ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ደብዛቸው ጠፋ፡፡

➔ጥቅምት 1 እና 2 ቀን 2013 ዓ.ም፡-  በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሀሮ ከተማ 15 አማራዎች ሲገደሉ፣ ከአንድ ሺህ በላይ ደግሞ ተፈናቀሉ፡፡ በቀጣዩ ወር ታሕሳስ 1 ቀን 2013 ዓም በዚሁ ዞን ውስጥ በጊዳ አያና ወረዳ ድሬ ጎዳ ቀበሌ ከ20 በላይ አማራዎች የሞት ፍርድ ሲፈረድባቸው ከ40 በላይ ንጹሐን ደግሞ ታፍነው ተወሰዱ፡፡

➔ታሕሳስ 2 ቀን 2013 ዓ.ም፡- በሆሮ ጉድሩ ዞን አባይ ጮመን ወረዳ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካን የሸንኮራ እርሻ በእሳት ያጋየው የኦነግ ታጣቂ በአካባቢው ያገኛቸውን የአማራ ተወላጅ የሆኑ 7 አዛውንቶችን በጥይት ደብድቦ ገደለ፡፡ ታሕሳስ 7 ቀን ደግሞ በሆሮ ጉድሩ ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ በከካ በሚባል አካባቢ የአቶ ባይሌና የአቶ እንደሻው ስድስት ቤተሰቦች በጅምላ ሲያልቁ ሌሎች አማራዎችም ተጎዱ፡፡

➔ከየካቲት 27-28/ 2013 ዓ.ም፡- በሆሮ ጉድሩ ዞን አቤ ደንጎሮ ወረዳ ደቢስ ቀበሌ ሕጻናትን ሳይቀር በቀጠፈ ጭፍጨፋ ከ50 በላይ አማራዎች ተገደሉ፡፡ ይሄውም መረጃ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በሥም ዝርዝር ጭምር ተደግፎ ሶሻል ሚዲያ ላይ የወጣ ቢሆንም በመንግሥት በኩል ግን የተባለ ነገር አልነበረም፡፡

➔በወርሐ መጋቢት 2013 ዓ.ም፡- የኒጀርና የማዳጋስካር ብሔራዊ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ 0 ለ 0 በመውጣታቸው የተነሳ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጠሪያ ማለፏን የሰሙ ኢትዮጵያውያን በደስታ ሲንሳፈፉ፣ በዚያው ምሽት የኦነግ ታጣቂ በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ሰዴቃ እና ሎንቺሳ ቀበሌዎች ውስጥ በሰነዘረው ጥቃት ከ170 በላይ አማራዎች ተጨፈጨፉ፡፡ የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግሥታትም የኀዘን መግለጫ አስተላለፉ፡፡

➔ነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም፡- በኦነግ ሸኔ ጥቃት ከ350 በላይ አማራዎች መገደላቸው በተለያዩ ሚዲያዎች ቢገለጽም ኢሰመኮ ባቀረበው ሪፖርት ግን ከ150 በላይ ንጹሐን መገደላቸውን አረጋግጦ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የዜጎችን ሕይወት እንዲጠብቁ አሳሰበ፡፡ ይሄውም ሪፖርት ከኢሰመኮ የፌስቡክ ገጽ ላይ ይገኛል፡፡

➔ነሃሴ 9/2013 ዓ.ም፡- በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ የኦነግ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 24 አማራዎች ሲገደሉ 10 አማራዎች ደግሞ ታግተው መወሰዳቸው የወረዳው አስተዳደሪ በሆኑት በአቶ ቡላ ደመረ አማካኝነት ተገለጸ፡፡

➔በሌላ መልኩ ደግሞ አሸባሪው ትሕነግ ተመትቶ ከተባረረ በኋላ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደስታ መንፈስ ሲሞላ ኦነግ ሸኔ ግን በወለጋና በሸዋ የአማራ ንጹሐንን ነፍስ ሲበላ ነበር፡፡ በወቅቱም የሚከተሉት የጥቃት ሪፖርቶች ኢሰመጎ ገጽ ላይ ወጥተው ነበር፡፡

➔መስከረም 27 ቀን 2014 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ጅባት ወረዳ፣ ዳርጌ ቀበሌ በስድስት መንደሮች በርካታ ቤቶችና ክምሮች ተቃጥለው በሺህዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን… በ23/4/2014 ዓ.ም በሆሮ ጉድሩ ዞን ጃርቲ ወረዳ ለገበያ የወጡ ሰባት አማራዎች ተገድለው አስከሬናቸው ተሰጥቶ መዋሉን…. በ11/4/2014 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ወረዳ መንቃት ቀበሌ ሌሊት ላይ በተፈጸመ ጥቃት 10 አማራዎች ተገድለው በማግሥቱ በአምቦ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መቀበራቸውን…..ታሕሳስ 14/2014 ዓ.ም ደራ ከተማ እና አካባቢው ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አማራዎች ሲገደሉ በከተማው የሚገኙ የአማራ ባለሃብቶች ደግሞ ሲዘረፉ ማደራቸውን….. ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ በእርሻ ማሳቸው ላይ በነበሩ ገበሬዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የስድስት ቤተሰብ አባላት የሆኑ 14 አማራዎች መገደላቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች በኢሰመጎ የቴሌግራም ገጽ ላይ ይፋ ሆነው ነበር፡፡

➔በመጋቢት ወር 2014 ዓም አባይ በረሐ ድረስ የመጣው የኦነግ ታጣቂ አራት ሹፌሮችን ገደለ፡፡ በዚያም ዘመቻው ጎሃ ጽዮን ድረስ ዘልቆ በመግባት ከ20 በላይ አማራዎችን ጨፍጭፎና በርካታ ንብረት ዘርፎ ተሰወረ፡፡

➔በወርሐ ጥር መጨረሻ 2014 ዓ.ም አሸባሪው ኦነግ በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳማ ወረዳ 168 አማራዎችን ጨፈጨፈ፡፡ ከእነዚህም አማራዎች አስከሬን መሃከል የ87 ንጹሐን አስከሬን ባንድ ቦታ ተከምሮ መገኘቱ በመንግሥት ሚዲያዎች ሳይቀር ተላለፈ፡፡ ፊደል የቆጠሩት የአማራ ልጆችም በሁለት ቀናት ውስጥ በተጨፈጨፈው ወገናቸው ፈንታ በሁለት እግሩ የቆመ የአገው ፈረስና የአንዲት ቆንጆ ልጅ ፎቶ ይዘው “አይገርምም ወይ” ሲባባሉ ነበር፡፡

➔በእለተ ስቅለት 2013 ዓ.ም በአንድ በአውቶብስ ወደ ጎጃም በማምራት ላይ የነበሩ ከ30 በላይ አማራዎች መንገድ ላይ ታግተው ተረሸኑ፡፡

➔ታሕሣስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም (የገና እለት) ደግሞ በሆሮጉድሩ ዞን የኦነግ ታጣቂ በከፈተው ጥቃት አጎቴን ጨምሮ 26 አማራዎች ባንድ ጎጆ ውስጥ ከተዘጋባቸው በኋላ በእሳት ተቃጥለው አለቁ፡፡

➔ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም የአማራ ባንክ ሥራ በጀመረበት እለት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በብልጽግና ከፍተኛና ዝቅተኛ አመራሮች ድጋፍ ከ1500 አማራዎች በኦነግ ታጣቂዎች ተጨፈጨፉ፡፡

➔ከሁለት ቀን በፊት ደግሞ በቄለም ወለጋ ሃዋ ገላን ወረዳ ለበተፈጸመ የጅምላ ፍጅት በ8 ሰዓታት ውስጥ ከ350 በላይ አማራዎች ተጨፈጨፉ፡፡

➔በሌሎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች

▬ኦነግ ወደ አገር ቤት የገባ ቀን 400 ጋሞዎች፣ ጉራጌዎችና አማራዎች ተጨፈጨፉ።

▬በ2013 ዓ.ም በኦነግ የተከበቡ ንጹሐን የመታደግ ዓላማ አንግበው በፖሊስ መኪና ሲጓዙ የነበሩ 20 የፌደራል ፖሊስ አባላት በቦንብ ጋይተው መንገድ ላይ ቀሩ፡፡

▬በ2013 ዓ.ም ኮንሶ ወረዳን የወረረው የኦነግ ታጣቂ “ሥማችሁ ከአማራ ጋር ይመሳሰላል››በሚል ምክንያት ከ66 በላይ የአማሮ ተወላጆችን ጨፈጨፈ፡፡

ማሳሰቢያ ፡-

▬▬▬▬

ይህ የዘር ፍጅት መረጃ በመንግሥታዊ መዋቅር ታግዘው በድብቅ ከተፈጸሙ እልፍ አእላፍ ጭፍጨፋዎች መሀከል ሾልከው የወጡትንና በኔ ማስታወሻ ላይ የተመዘገቡትን ያካተተ እንጂ በብልጽግና ዘመን የተፈጸመውን ድምጽ የለሽ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሊገልጽ የሚችል አይደለም፡፡

Filed in: Amharic