>

እንደማመጥ... !!!! (በእውቀቱ ስዩም)

እንደማመጥ… !!!!

(በእውቀቱ ስዩም)

.

እድሜየ ላቅመ ምክር ስለደረሰ ልመክር ነው፤

ስልጣንህን ተጠቅመህ የተወዳዳሪህን የመናገር ነፃነት ስታፍን ፤ ራስህንና አገርህን በሁለት መንገድ ትበድላለህ፤ አንደኛ ልክህን እንዳታውቅ ትሆናለህ ! ዜጎች ባስተዳደርህ  ላይየሚያቀርቡትን ቅሬታ ካልሰማህ እንዴት ልክህን ታውቃለህ? ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው፤ብዙ አምባገነኖች የወዳጆቻቸውን ከንቱ ውዳሴ

የህዝብ ድምፅ ነው ብለው በማመን ሲሸወዱ ኖረዋል ፤ አመፅ ደጃቸውን እስኪያንኩዋኩዋ ድረስ ፤ ብዙ ጌቶች ራሳቸውን በህዝባቸው የተወደዱ አድርገው ይቆጥሩ ነበር ፤ ብልጥ መሪ

ከወደረኛው ነቀፋ ይማራል፤ ጵሉታርክ የተባለ የግሪክ ደራሲ ከፃፈው አንድ ገጠመኝ ላስታውስ፤

ሄሮይን የተባለ ጌታ ፤ አንድ ቀን አንዱ ጠላቱ ፤ ” አፍህ ይገማል ” ብሎ ዘለፈው፤ አንገቱን ደፍቶ ወደ ቤቱ ተመልሶ ፤ ሚስቱን “ ለምን አፌ እንደ ሚሸት አልነገርሽኝም ? ” ሲላት ገራሚቱ ሴት “ የሁሉም ወንዶች አፍ እንደዚያ ይመስለኝ ስለነበር ነው ” ብላ መለሰችለት ፤ ጌታ ሄሮይን መፋቂያ እንዲገዛ ያነቃቃው የሚስቱ ፍቅር ሳይሆን የጠላቱ ዘለፋ ነው ፤ ባለስልጣን ስትሆን፤ ከባለንጀራህ ውዳሴ ይልቅ የባላጋራህ ነቆራ አንተንም አገርንም ይጠቅማል ፤

ስልጣንህን ተጠቅመህ የተወዳዳሪህን የመናገር ነፃነት ስታፍን ተወዳዳሪህን አላግባብ ታጀግነዋለህ ፤ ካልተናገርኩ ብሎ የሚቀውጥ

የማይክ ቀበኛ ብዙ ነው ፤ ማይኩን ያውልህ ብለህ ስትሰጠው ፍሬ የለውም፤ በደርግ ጊዜ” ደርግ በሳንሱር ይዞብን ነው እንጂ አለምን የሚነቀንቅ ድርሰት አለን” የሚሉ ሰዎች ነበሩ፤ ደርግ ከነሳንሱሩ ሲወገድ፤ ታፍነን ኖረናል ባዮች ድርሰቱን አላወጡትም፤ (ሲጀምር ድርሰት አልነበራቸውም፤ ) የወጣውም ከጥቂቱ በቀር ገለባ ነው ፤ በመከልከሉ ብቻ ሰማእት አዋቂ ጀግና ሆኖ የሚታይ ችኮ በየማእዘኑ አይጠፋም ፤ እዚህ ላይ የማሞ ታሪክ ትዝ አለኝ፤ ማሞ የእትየ ይመናሹ ጎረቤት ልጅ ነው፤ አንዳንዴ እትየ ይመናሹ ቤት ይመጣና ከልጆቻቸው ጋር ተደባልቆ ይቀመጣል፤ ሌሎች ሲያወሩ፤ማሞ ዝም ይላል፤እትየ ይመናሹ፤የማሞ ጭው ያለ ዝምታ ያስገርማቸዋል፤ እንዴት ያለ ጭምት ልጅ ነው! እያሉ ያደንቁታል፤ አልፎ አልፎ ግን ያሳዝናቸዋል፤

“ልጅየ ለምን አትጫወትም?” “አየ! እናቴ እንዳትጫወትህ አፍህ ባለጌ ነው ፤ሰው ታስቀይማለህ፡” ብላኛለች ይላል ማሞ፤

እትየ ይመናሹ ይሄን የመሰለ ልጅ ታፍኖ መኖሩ አሳዝኑዋቸው “ እናትህን አትስማት፤ አፍህ ማር ነው፤ ተጫወት፤ ‘በለው ጎተጎቱት፤ “እንግዲህ ተጫወት ካላችሁኝ አለና ማሞ የጨዋታ ጭብጥ

ፍለጋ፤ዙርያ ገባውን ተመለከተ፤ ከፊትለፊቱ ትልቅ ራስ ያለው የትየ ይመናሹ ልጅ ቁጭ ብሉዋል፤

“እንግዲህ ተጫወት ካላችሁኝ… የሄ አናታም ልጅ እንዴት ሆኖ ተብልትዎ ወጣ?” “እውነትም አፍህ ባለጌ ነው” አሉ እትየ ይመናሹ እሳት ጎርሰው ፤

“ተናግሬ ነበር!” አለና ማሞ ወደ ዝምታው ተመለሰ፤ ማሞ ንግግር ስለተከለከሉ ብቻ የታፈነ ጥበብ ይዘው የሚኖሩ የሚመስሉ ሰዎች በኩር ነው፤እንዲናገሩ መፍቀድ ልካቸውን ለማወቅ

ይረዳል፤ እንደዜጋ መሪዎቻችንን ብቻ ሳይሆን ወደረኞቻቸውን የማወቅ መብት አለን፤ አፈና፤ቀሊሉን ከከባዱ፤ደደቡን ከሊቁ፤እብዱን ከጭምቱ ፤ የምንለይበትን አጋጣሚ ያሳጣናል፤

Filed in: Amharic