>

የአልሸባብ ወረራ እና የአገዛዙ መግለጫ (ጌጥዬ ያለው)

የአልሸባብ ወረራ እና የአገዛዙ መግለጫ

የአገዛዙ ቀጣይ መግለጫ እንዲህ የሚል ይሆን?፦

ጌጥዬ ያለው


•አልሸባብ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገባ በሚል የሚናፈሰው ወሬ ሀሰት ነው። መንግሥትንና ሕዝብን ለመነጣጠል ያሰቡ፤ ሀገሪቱ የሽብር ቀጣና እንድትሆን የሚፈልጉ ባንዳዎች ወሬ ነው. . .  (እዚህ ላይ ከአልሸባብ ጋር ያለንን ወንድማማችነት ለማጠልሸት ታስቦ ነው) የሚል እንዳይጨምሩበትም ያሰጋል¡

የወራሪው ኦሕዴድ-ብልፅግና ቃል አቀባይ መግለጫውን ውሸት በሚያስተጋቡ ማይክራፎኖች ፊት አንብቦ እንደጨረሰ በደንቡ መሰረት ጋዜጠኞች ለጥያቄ እጆቻቸውን ያወጣሉ። የቃል አቀባዩ ቃል አቀባይ ማለትም የመግለጫው አስተባባሪ የሕዝብ ግንኙነት ሠራተኛ እድል መስጠት ይጀምራል። ከግል ሚዲያ እና ከውጭ ሚዲያ የመጡ ዘጋቢዎች ካሉ በተቻለው መጠን እድል ላለመስጠት ጥረት ያደርጋል። ድንገት ከሰጠ ግን ጋዜጠኞቹን ከርቀት የሚቆጣጠራቸው መሆን አለባቸው። ይህ ሁሉ ፍራቻ የግል ሚዲያዎችም ሆኑ የውጭ ሀገር ሚዲያዎች ከቃል አቀባዩ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠው አልሸባብ 70 ኪሎ ሜትር ድረስ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ መግባቱን፣ የኦሮሞ ወራሪ ሰራዊት አባላት መንገድ መሪ መሆናቸውን፣ የሶማሌ መስተዳድር ልዩ ሃይል ብቻውን እየመከተና የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር እያስከበረ መሆኑን ብሎም የአገዛዙ መግለጫ ሀሰት መሆኑን የሚያጋልጡ ሆነው አይደለም። ይህንን የሚያደርግ ወኔ የላቸውም። ምክንያቱም ይህ ከሥራ ያስባርራል። ድርጅታቸውን ያስዘጋል። ያስደበድባል፤ ያሳስራልም። ጣሂር መሐመድ እንኳን የአማራን ሕዝብ ለካደበት ካሳ በተሰጠችው ትንሽ ሥልጣን ጋዜጠኛ ለመደብደብ ሲጋበዝ በቴሌቪዥን ካሜራዎች ፊት ማየታችንን ልብ ይሏል። በነገራችን ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ርዕዩ የአገዛዙን ሥልጣን ማስጠበቅ ባይሆንና እንደ ስሙ ፍትሕ ለማስፈን ቢሆን ኖሮ ጣሂርን በሕግ ፊት መክሰስ ነበረበት። እንደ አሸን የተፈለፈሉ የጋዜጠኞች ማህበራት ዓላማቸው አገዛዙን ማጀብ ባይሆን ኖሮ ቢያንስ ድርጊቱን ተቃውመው መግለጫ ማውጣት ነበረባቸው።

በአጭሩ፤ የግል ሚዲያዎችም ሆነ የውጭ ሚዲያዎች እውነቱን የማጋለጥ አቅም የላቸውም። የስርጭት ፈቃድ ሲሰጣቸውም ይህ ተጠንቶ ነው። አገዛዙን መደገፍ ባይችሉ እንኳን አጋላጭ ከሆኑ አንድ ሳምንት አይቆዩም፤ የሀገር ውስጦቹ የስርጭት ወይም/እና የንግድ ፈቃዳቸውን ተነጥቀው ይዘጋሉ። የውጮቹም የዘጋቢነት መታወቂያቸውን ተነጥቀው ይባረራሉ።

የቃል አቀባዩ ቃል አቀባይ እንዲጠይቁ እድል የማይሰጣቸው  መግለጫውን በተፃፈበት የፍረጃና የአገላለፅ መልክ ላይዘግቡት ይችላሉ ከሚል ጥርጣሬ ነው። ምሳሌ፦ ‘ጁንታው’ ተብሎ ከሆነ ‘የትግራይ ኃይሎች፣ ሕወሓት’ እንዳይሉት፣ ‘ሸኔ’ ተብሎ ከሆነ ‘ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት’ ብሎ የሚጠራው እንዳይሉት የፍረጃ ፍሰቱን ለመቆጣጠር ነው።

ከላይ በተጠቀሰው መግለጫ ላይ እንዲጠይቁ እድል የተሰጣቸው የአገዛዙ ጋዜጠኞች ታዲያ ምን ሊጠይቁ ይችላሉ?

•ኢቴቪ፦ ኢትዮጵያ ተወረረች እያሉ የሀሰት ወሬ የሚያሰራጩ አካላት ላይ ለመውሰድ የታሰበ ርምጃ አለ ወይ?

  • ፋና፦ በሬ ወለደ እያሉ ይህንን የሀሰት ወሬ የሚናፍሱ ሃይሎች ዛሬ ብቻ አይደለም ደጋጋሚ ናቸው። ከዚህ በፊት ጅቡቲ በአፋር በኩል ወረረች፣ ደቡብ ሱዳን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ሌላም ሌላም እያሉ ሲያስወሩ ቆይተዋል። ከድርጊታቸው ግን አልታቀቡም። እነዚህ ሃይሎች ከጠላት ከፍተኛ ሎጀስቲክ የተሰጣቸው ናቸው። እስከ አሁን እንዴት ርምጃ አይወሰድባቸውም? የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ እያደናቀፉ እንዴት ዝም  ተባሉ? በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ቢሰጡን።

• የቃል አቀባዩ ቃል አቀባይ፦ ካለን ሰዓት አንፃር እነዚህ ጥያቄዎች ብቻ ይመለሱ። ሌሎቻችሁን መቀበል አልችልም!

  • ቃል አቀባዩ፦ በዳሳ ከኢቴቪ ያነሳኸው ጥያቄ  ተገቢ ነው። ከፋናም ቂጢሳ ያነሳሽው የፖለቲካ አመራሩም፣ የሕዝባችንም ጥያቄ ነው። ያው ምሳ ሰዓት እየደረሰ ስለሆነ እንግዲህ ሌሎቻችሁ ዕድሉን አልሰጠናችሁም። በተለይ ፈየራ ከፕሬስ ድርጅት፣ ገመቹ ከዋልታ፣ ገርባ የላከህ ልጅ I mean ልብአርጋቸው ከአማራ ቴሌቪዥን ከቅድም ጀምሮ ነው እጃችሁን አውጥታችሁ የነበረው። ወደ መጨረሻ አካባቢ ጥቂት ደቂቃ ወስደን የእናንተን ጥያቄዎች እቀበላለሁ። ሌሎቻችሁ በግል መገናኘት እንችላለን።

ወደ ጥያቄዎቻችሁ ስመጣ፤ እንደምታውቁት መንግሥታችን በሆደ ሰፊነት ነገሮችን እያለፈ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ከውጭ ሀይሎች ጋር የሚተባበሩ ባንዳዎች እዚም እዚያም አሉ። ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ብቻ ሳይሆን ከአሸባሪ ቡድኖች ጋራ ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች ይዘናል። የብሔራዊ ሰላምና ፀጥታ የጋራ ግብረ ሃይላችን ከ30 በላይ ግለሰቦችን ይዟል። አብዱል መጂድ፣ መሐመድ፣ እንድሪስ የተባሉ ግለሰቦች የአሸባሪው አልሸባብ ወኪል በመሆን በአዲስ አበባ ጥቃት ለመሰንዘር ሲንቀሳቀሱ ይዘናቸዋል። በሕግ ቁጥጥር ስር ሆነው ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል። ርምጃ እንወስዳለን! እንዴት ርምጃ አይወሰድም! እነዚህ ግለሰቦች እኮ አልሸባብን ጅግጅጋ ድረስ እየመሩ ያመጡ ናቸው። (እዚህ ላይ ከጋዜጠኞች ጉምጉምታ ይሰማል)

አዎ! ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ባይኖር ኖሮ ጅግጅጋ ድረስ ለማምጣት ነበር ፍላጎታቸው።

ማስታወሽ

ከዚህ ቀደም  የጅቡቲ ታጣቂዎች በአፋር በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ገቡ። ንፁሃን ኢትዮጵያውያንን ገደሉ። የፋርን ፍየሎች እና ግመሎች ዘረፉ፤ ገደሉም። የአፋር መስተዳድር “ወረራ ተፈፅሞብናል” በማለት መግለጫ ሰጠ። የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ሰመራ ድረስ ሄደው ብሶቱን እንዲሰሙለት ጥሪ ቢያደርግም የደረሰለት አልነበረም። ይባስ ብሎ በለማ መገርሳ ሚንስትርነት ይመራ የነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሌላ መግለጫ አወጣ። የጅቡቲ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር እንዳላለፉ አስተጋባ። የአፋር መስተዳድር የማረካቸውን እና የገደላቸውን የጅቡቲ ታጣቂዎች ከእነ መታወቂያ ካርዳቸው እና መለያ ልብሳቸው ፎቶ እያነሳ ተከራከከረ። ክርክሩ ከመግለጫ አልፎ ወደ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍም ተቀየረ። የአፋር ሕዝብ “ለጅቡቲ ሸቀጥ ተብሎ እኛ መካድ የለብንም” በማለት አደባባይ ወጣ።

በተመሳሳይ ከሳምንታት በፊት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ‘ክልል’ በኩል 70 ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ ኢትዮጵያ መዝለቃቸውን እና የወርቅ ማውጫ ስፍራን መቆጣጠራቸውን የአካባቢውን የአዛዙ ባለሥልጣናት ጠቅሶ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገበ። ወዲያውኑ የአገዛዙ መገናኛ ብዙሃን በሪፖርተር ጋዜጣ የተጠቀሰው ባለሥልጋን እንደተናገረ አስመስለው ነገሩ ሀሰት ነው ሲሉ ሌላ የውሸት ዜና አሰራጩ። ሰውየው ፎቷቸው ቴሌቪዥኑ ላይ ከመለጠፉ ውጭ በድምፅም ሆነ በተንቀሳቃሽ ምስል አልቀረቡም። ከዚህ ሁሉ ምርመራ ውስጥ ሳያስገቡን “ለሪፖለርተር የተናገርኩት እውነት ነው። አንድ ወረዳ ተወሮብናል። የመንግሥት ሚዲያዎች ያሰራጩት ውሸት ነው” በማለት አጋለጡ።

በጎንደር በኩል ሱዳን ለምታደርገው ተደጋጋሚ ወረራም በአገዛዙ በኩል ተመሳሳይ ክህደት ይደመጣል።

Filed in: Amharic