>
5:11 pm - Thursday March 30, 2023

የዲ/ን ዳንኤል ክብረት የሐቅና የአመክንዮ ዝንፋቶች....!!! (ኤርምያስ ክንዴ)

የዲ/ን ዳንኤል ክብረት የሐቅና የአመክንዮ ዝንፋቶች….!!!

ኤርምያስ ክንዴ


*… – “አራት የተለያዩ አካላት ከተቹኝ ጤናማ ነኝ ማለት ነው”

*… በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ንጹሐን በማንነታቸው ምክንያት መጨፍጨፋቸውን በተመለከት ሲጠየቅ -“ከማልቀሱ ይልቅ ስራ ላይ አተኩራለሁ…!”  የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

– ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በEMS ሚድያ ያደረገውን የሁለት ክፍል ቃለ መጠይቅ ተመለከትሁት። እንደእውነቱ ከሆነ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ካነሳቸው አሳቦች ውስጥ የምስማማበት ነጥብ አለ ለማለት እቸገራለሁ። በዚህ መጣጥፍ ውስጥ የማልስማማባቸው አሳቦች ላይ ሁሉ አስተያየት ለመስጠት ጊዜም ትእግስትም በእጅጉ ያጥረኛል። ስለዚህም በተወሰኑ የአመክንዮ ፣ የሐቅና የጽንሰ አሳብ ግድፈቶች ላይ አተኩራለሁ። ውይይቱ በጥቅሉ ከእውነታ ጋር የተፋታና የአድማጭ ተመልካችን ትእግስት የሚፈታተን እንደሆነ ይሰማኛል። ግፋም ሲል ደግሞ ዳንኤል የሰማእያንን Intelligence ዝቅ አድርጎ የሚመለከት ስለመሆኑ የሚያሳብቁ ብዙ የማጭበርበር ክርክሮችን (Deceptive arguments) ተጠቅሟል ስል እደመድማለሁ። ወደ ነጥቦቹ እንዝለቅ።

– “አራት የተለያዩ አካላት ከተቹኝ ጤናማ ነኝ ማለት ነው”

ከላይ የጠቀስሁትን አሳብ ጋዜጠኛ ፋሲል ዳንኤል ክብረትን የተለያዩ አካላት ይተቹሃል በማለት ለጠየቀው ጥያቄ የሰጠው መልስ ነው። ይህ ምላሽ ግልጽ የሆነ የአመክንዮ ሕጸጽ ያዘለ ነው። የአንድ ሰው ትክክለኝነት የሚረጋገጠው የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ስለተቹት ነውን? የተለያየ አመለካከት ያላቸው አካላት የሚተቹት ሰው በሚተቹት አካላት የሃሳብ መለያየት የራሱን ትክክለኝነት ሊያረጋግጥ የሚችልበት አመክንዮአዊ መሠረት የለም። ዳንኤል ክብረት ብሔረተኞችም ፣ አክራሪ ሃይማኖተኞችም ሌሎች በአስተሳሰብ የተለያዩ ጽንፈኛ አካላት የሚተቹት መሆኑ የእርሱን ትክክለኛነት የሚያጸድቅ ነው ሲል ግልብ ሰማእያንን Brainwash ሊያደርግ ቢችልም Common sense አለኝ የሚል ሁሉ ሊቀበለው የማይገባ ክርክር ነው። ክርስትና እውነት የሚሆነው ይሁዲነት ፣ እስልምና ፣ ሂንዱይዝም ፣ ሺንቶይዝም….ወ.ዘ.ተ ስለተቃወሙት ሳይሆን በራሱ እውነት ስለሆነ ነው። ዳንኤል ክብረት የሚተቹት አካላት በአመለካከት የተለያዩ መሆናቸው የእኔን ትክክለኝነት ያስረዳልኛል ሲል ያመጣው ክርክር የሚያስኬድ ክርክር አይደለም። Its of a typical deceptive argument.

– ሌላው ዳንኤል ክብረት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ንጹሐን በማንነታቸው ምክንያት መጨፍጨፋቸውን አለማውገዝህ ቅር የሚያሰኛቸው ሰዎች አሉ። ለዚህ ቅሬታ ምንድር ነው ምላሽህ ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ እኔ ከማልቀሱ ይልቅ ስራ ላይ አተኩራለሁ የሚል ምላሽ ሰጥቷል። ይህ የዳንኤል አነጋገር ማውገዝ Relevance እንደሌለውና ስራ ላይ ማተኮር እንደሚበጅ የሚያትት ነው። በዚሁ ክርክር መሰረት እስቲ ዳንኤልን አንድ ጥያቄ እንጠይቀው። ጭፍጨፋዎቹን ማውገዝ (በዳንኤል አነጋገር ማልቀስ) ጥቅም የሌለው ከሆነ ብጹእ ወቅዱስ ፓትርያርኩን በየሚዲያው ማውገዝና መንቀፍ ምን አይነት ረብሕ ይኖረዋል? ፓትርያርኩ ስሕተት ሊሰሩ ይችላሉ። ቤተክርስቲያናችንም ፓትርያርክ አይሳሳቴ (Infallible) ነው ከሚለው ካቶሊካዊ አስተምሕሮ ጋር ሕብረት የላትም። ነገር ግን የሚታረሙበት የራሱ የሆነ መንገድ አለው እንጂ ማንም መደዴ ተነስቶ ከፍ ዝቅ አድርጎ እንዲናገራቸው የሚፈቅድ ነገረ ሃይማኖታዊም ሆነ ሞራላዊ አግባብ ሊኖር አይችልም። Whatever the mistake is! ዳንኤል ክብረት ጎረምሶች መቆሚያ መቀመጫ ባሳጧቸው ጊዜ የአባትነት ክብራቸው መነካቱ ቆርቁሮት ከጎረምሶች ከበባ እንዲወጡ አደረግኋቸው ያላቸውን ብጹእ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን በተለያዩ ሚዲያዎች ከፍ ዝቅ አድርጎ በመናገር ለፌስቡክና ዩቲዩብ ጎረምሶች አሳልፎ መስጠቱ እጅግ የሚያሳዝን ነገር ነው። ጨፍጫፊዎችን ለማውገዝ የጠፋው የዳንኤል ድምጽ ፓትርያርኩን ለማውገዝ መገኘቱ ዳንኤል ለመርሕ ግድ እንደሌለውና ባለ Double standard መሆኑን የሚመሰክር ነው።

– በውይይቱ ዳንኤል የወያኔ አይነት ድርጅት እንዲጠፋ እፈልጋለሁ ሲል ተደምጧል። የትኛውም የጤናማ አእምሮ ባለቤት የሆነ ሰው የወያኔ አይነት ድርጅት እንዲኖር ይፈልጋል ብዬ አላስብም። ችግሩ ግን ዳንኤል ክብረት ምንም አይነት ሕገመንግስታዊ ፣ መዋቅራዊና አስተሳሰባዊ ለውጥ ያላደረገው የብልጽግና አገዛዝ Subservient የመሆኑ ነገር ነው። ብልጽግናን በጸረ ኦርቶዶክስነት አየከሰሱ ዳንኤልን የሚደግፉ ሰዎች ስመለከት የሚጣላ ሕሊና ባለቤት አለመሆናቸው ያስገርመኛል። ዳንኤል ክብረት የኢትዮጵያ ችግር ከንጉሡ ፣ ከደርግ ፣ ከወያኔ ሲተላለፍ የመጣ እንደሆነ ለመናገር አንድ ሰው በሽታው እስኪጸናበት ከቆየ በኋላ ጥቁር አንበሳ መጥቶ ይሞታል ፣ በዚህም “ጥቁር አንበሳማ መች ሰው ይተርፋል” ተብሎ ይነቀፋል የሚል ተራ ምስስሎሽ በመስራት “ብልጽግና ምን ያድርግ?” ሊለን ይሞክራል። የዚህ ምሳሌ መሠረታዊው ችግር ዳንኤል የሚያገለግለው አገዛዝ መዋቅራዊና ሕገመንግስታዊ ለውጥ ባለማድረግ የሃገሪቱን ሁለንተናዊ ፍርሰት እያፋጠነ በመሆኑ ብልጽግና እርሱ ከጠቀሰው “የጥቁር አንበሳ” ምሳሌ ጋር ስምም አለመሆኑ ነው። ዳንኤል ክብረት በውይይቱ ሙሉ የሚያገለግለው መንግስት መዋቅራዊና ሕገመንግስታዊ ለውጥ ለማድረግ ባለመፈለጉ ያመጣውን ችግር ሁሉ የውጭ ጠላቶች ለሚላቸው ሰጥቶ የሚያገለግለውን አገዛዝ ነጻ ለማውጣት የሄደበት ርቀት አጀብ ነው መቼም።

– የአቋም ወይስ የአቅም ችግር?

ዳንኤል የኢትዮጵያ መንግሥት ያለበት የአቋም ሳይሆን የአቅም ችግር እንደሆነ በውይይቱ ተናግሯል። መዋቅራዊና ሕገመንግስታዊ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኝነት የሌለውና በየጊዜው ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ እንዲካሄድ ምክንያት የሆነን መንግስት የአቋም ችግር የለበትም የሚል ክርክር ማንሳቱ ሊያስኬድ የሚችልበት አመክንዮ የለም። መንግስት የአቋም ችግር እንደሌለበት የአቅም ችግር እንዳለበት ደጋግሞ ሲናገር የነበረው ዳንኤል ቆየት ይልና “የኢትዮጵያን አቅም ከወዳጆቿ ይልቅ ጠላቶቿ ያውቁታል ፣ የመከለከያና የደኅንነት ተቋማቱ የተለወጡበትን መንገድ አይቼ ይህን ያዩ አይኖቼ የተባረኩ ናቸው ብያለሁ” ሲል ቀድሞ ያነሳውን የአቅም አልባነት መከራከሪያ በአፍጢሙ የሚገለብጥና የሚቃረን አሳብ ይሰነዝራል። የመንግስት የጸጥታ መዋቅር እንዲህ የዘመነና አቅም ያለው ከሆነ ይህን ሁሉ ጭፍጨፋ ከመሆን ለምን ማዳን አልቻለም? ዳንኤል በደረቁ እየላጨን አይደለምን? ዳንኤል ለሚሰማው ሰው Intelligence ንቀት ከሌለው እንዲህ እርሱ በርሱ የሚቀዋወም የሚላተምና የሚጣፋ አሳብ ያቀርባል ብዬ አላስብም።

– በወለጋም ሆነ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የሚደረጉ ማንነት ተኮር ጭፍጨፋዎችን በተመለከተ ዳንኤል “መንግስት ያከሸፈው ብዙ የሽብር ተግባር ስላለ መንግስትን Blame አናድርግ” የሚል አሳብ ሰንዝሯል። አንባቢ ሆን ይህን መከራከሪያ አሰላስለው እስቲ! በሃገራችን ውስጥ የትኛውም ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ በተደረገ ቁጥር  “ከኅቡእ መሥገርት የሚሰውረን መንግስታችን” ብለን ከማመስገን ውጭ ቅሬታ ባይኖረን ይመረጣል ብለን Articulate ብናደርገው የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን አሳብ አልሳትነውም።

– እንደ መሰናበቻ የዳንኤል ምሳሌዎች እርሱ ይወክሉልኛል ከሚላቸው ሃሳቦች ጋራ ያላቸውን ርቀት በተመለከት ጥቂት ልበል። ዳንኤል ሃሳቦቼን ይወክሉልኛል ብሎ የሚጠቅሳቸው ምሳሌዎች ለሎጂክና ለመርሕ ግድ እንደሌለው የሚያመላክቱ ይመስለኛል። ለምሳሌ በዚህ ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ከችግር ወደ ልእልና እየወጣች ነው ለማለት “ልጆች ሆነን መኪና ውስጥ ስንጓዝ ዛፉ እየሄደ ይመስለን ነበር የሚሄደው ግን ዛፉ ሳይሆን መኪናው ነው። ኢትዮጵያ መከራዎቿን ወደ ኋላ እየተወች እየሄደች ነው” የሚል እጅግ ግራ የሚያጋባ ምሳሌ ይመስላል። ኢትዮጵያ ከችግር እየወጣች ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን አሳብ ወደ ጎን ትተን ዳንኤል ነጥቤን ያስረዳልኛል ለማለት የጠቀሰውን ምሳሌ ብንመለከት እንኳን የጠራ ምስል ማየት የምንችል አይመስለኝም። እንዲህ ያለ ተራ ምስስሎሽ በመመሰል አገራችን ወደ ከፍታ መውጣቷን ይነግረናል ዳንኤል። ይህ ምሳሌ ዳንኤል ሊናገረው ከፈለገው ጉዳይ ጋር ያለውን ጽንሰ አሳባዊ ተዛምዶ የሚያውቀው ዳንኤል ብቻ ነው። ይሕን እንደ ምሳሌ ጠቀስሁ እንጂ ዳንኤል ክብረት አሳቤን ይደግፉልኛል በማለት የጠቀሳቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦችም ሆኑ ምሳሌዎች ከጉዳዮቹ ጋር የሚገጥሙ ሆነው አላገኘኋቸውም። በተለይ ዳንኤል አሳቡን ለማሻሻጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮችን ያለ አውዳቸው እየቆነጻጸለና ሊሉት ከፈለጉት መሰረታዊ አሳብ ውጭ እርሱ እንዲሉለት የሚፈልገውን በግድ ቆንጥጦ የማናገሩ ነገር የሰነባበተና አደገኛ ውጤት ያለው ነው። ለምሳሌ “ጌታ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ” የሚለውን ቆየት ያለ ወጉን ማንሳት ይቻላል። ይሕ ራሱን የቻለ ጉዳይ ነውና በሌላ ጊዜ መወያየቱ ሳይጠቅም ይቀራል ብለን አንጠረጥርም። ለዛሬ በዚሁ ላብቃ።

Filed in: Amharic