>

ፍርድ ቤቱ የታዴዎስ ታንቱን የክስ መቃወሚያ ሳይቀበል ቀረ...!!! (ባልደራስ)

ፍርድ ቤቱ የታዴዎስ ታንቱን የክስ መቃወሚያ ሳይቀበል ቀረ…!!!

ባልደራስ


አዛዎንቱ ጋዜጠኛ እና የታሪክ ጸሐፊ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ ዛሬ ረቡዕ ሀምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀርበዋል። ችሎቱ ለዛሬ ቀጥሮ የነበረው የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ እና ፖሊስ ሁለተኛ ተከሳሽ ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለውን በተገኘበት አስሮ እንዲያቀርብ ነበር።  ሆኖም በከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ የክስ መቃወሚያቸውን ማቅረብ አለመቻላቸውን ጠበቃቸው አቶ አዲሱ ጌታነህ ገልጸዋል። ዓቃቤ ሕግ ሁለተኛ ተከሳሽን ፖሊስ ፈልጎ እስከ አሁን አለማግኘቱን ጠቅሶ ጌጥዬ ያለው ሳይያዝ የክስ መቃወሚያቸውን እንዳያቀርቀቡ በማለት ተቃውሟል።

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ የፊታችን  ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ረፋድ 4  ሰዓት ላይ የክስ መቃዎሚያቸውን አባሪያቸው ሳይያዝም ቢሆን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የፌዴራል ፖሊስ እስከ ነሐሴ 2 ጌጥዬ ያለውን በተገኘበት አስሮ እንዲያቀርብም አዝዟል። በዚህ ዕለት ይዞ ካልቀረበ ግን ሁለተኛ ተከሳሽ እንዲሰናበት ወይም በሌለበት ዶሴው እንዲቀጥል ብይን እንደሚሰጥ ገለጿል።

የታዴዎስ ታንቱ የክስ መቃወሚያ እንዳይቀርብ ሲስተጓጎል ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም የክስ መቃወሚያቸውን በሚያቀርቡበት የቀጠሮ ቀን ችሎቱ ቢሰየምም ፖሊስ ሳያቀርባቸው በመቅረቱ ተስተጓጉሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጋሽ ታዴዎስ ነገ ሀምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይቀርባሉ። በዚህም ችሎቱ የእስር ፍርድ ቤቱ የፈቀደላቸውን የ15 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ያጸናል ወይም ይሽራል።

/

Filed in: Amharic