>

ወይ ዘንድሮ ! ወይ ዘንድሮ! ማሚቴ ሆነች ዝንጀሮ ።.... (ደረጀ መላኩ)

ወይ ዘንድሮ ! ወይ ዘንድሮ!

ማሚቴ ሆነች ዝንጀሮ ።

ወይ ዘንድሮ ! ወይ ዘንድሮ !

አያልቅም ተነግሮ ።

 

ደረጀ መላኩ 

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ

የሚከተለው ጽሁፍ የተጠናቀረው አንድ ኑሮአቸውን በተባበረችው አሜሪካ ባህር ማዶ ያደረጉ የማህበራዊ ድረገጽ ወዳጄ የኮሌጅ ህይወታቸውን መሰረት አድርገው ካወጉኝ ወግ መሰረት ላይ ሆኖ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ድሮና ዘንድሮ  ኑሮ ምን አይነት ልዩነት እንዳላቸው በወፍ በረር ለማስቃኘት ታስቦ የተሰናዳ መሆኑን አንባቢውን በትህትና አስታውሳለሁ፡፡ በተረፈ ወይ ዘንድሮ ወይ ዘንድሮ የተሰኘውን ዘመን አይሽሬ ዜማ የሆነውን የኤፍሬም ታምሩን ዜማንም እጋብዛለሁ፡፡

ነገርን ነገር ያነሳዋል ። ነገርም ካስተዋሉትና መረመራ (ቂቂቂ) ካደረጉት ለመፃፍም መነሻም ይሆናል ።

በንያ ሩቅ ዓመታት ነው ። ተማሪ ሳለን ልበለው። 

የዕለት እንጀራችንን ስጠን ። 

ወደፈተናም አታግባን ብለን ፀልየን ፀልየን ። 

የተፀለየውም ተምኔት ብቻ ሆኖብን የዘመኑን ፈተናም በግብሩ ተቀብለን የከርሞ ሰው ባለሙያ ለመሆን ከተፈጠርንበት ምሥራቅ ዳርቻ ባልነበረን አማራጭ ወደ 650 ኪሜ ወደ ምዕራብ መሐል ተጉዘን በር አንኳክተን በአንድ የግብርና ትት መስጫ ተቋም ደርሰናል ። 

ተቋሙ ዕድሜው ዘንድሮ ከነሜታሞርፈሰሱ ሠባ አምሥት ደርሷል ። አልማዝ ኢዮቤልዩ ማለትም አይደል ?

የነበረውን ስንስለው ደግሞ ልክ ከተማዋን ለሁለት ሰንጥቆ ከሚያልፈው ትልቁ ሁሉቃ ወንዝን አጠገብ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ አጠገብ እንኳን ደህና መጡ አምቦ /ሐገረ ሕይወት የሚል ቅስትም ተተክሎ ነበር ።

ሁሉቃን ወንዝ ፍሰቱን ብዙ ባላውቀውም ከድልድዩ በታች ጥልቅ ይመስላል ።

ሁሉቃን ማን ባሻገረኝ 01 ጉዳይ ነበረኝ ቂቂቂ

ንግድ ባንክ ውስጥ አንድ ቀላ የሚሉ ቀጭን ሰውዬ ከደንበኛ አገልግሎት መስጫው ሣጥን ጀርባ በሥራ ሰዓት ወደ ባንኩ የዘለቀ አያጣቸውም። 

የሰውዬውን ደቃቅነታቸውን ባያጎላውም በሸሚዛቸው አንገት ላይ አዙረው ከደረታቸው በታች ድረስ ከመኖሪያ ቤታቸው ጓሯቸው ስፋት የማያንስ ሰፋ ያለ ህብረ ቀለም ያለበት ክራቫትም ያስራሉ ። 

ባንከሮች ክራቫት ይወዱም አይደል ?

አንዳንዴም በጠርሙሥ ንባብ ቤት (የሎ ቤት) ከሚያዘወትሩ የተቋሙ ተማሪዎች ጋርም ባልንጀራ ናቸው። ይነፋፈቃሉ ።

ተሜ ሁለተኛ ዓመት ስትገባ በደረጃዋ ብር አራት በየወሩ እየተቆረጠ ሰልፍ ይዛ ፔሮል ላይ ፈርማ ትቀበላለች ። ስታይ ፈንድ ይሷታል ። የኪስ እንጂ የቦርሣም ብር አይደለች ።

ምሽቱ ደስታ ነው ። ትዕይንቱ እንደየሰው ባሕርይ ልዩ ነው ።

አንደኛ ዓመት ብሯ ሦስትም ብትሆን ቀለም መራጩ ወደ መሸታ ቤት አይመርጥም ። 

ደብተርና መፅሐፍ ብቻ ስለሚታይህ ግፋ ቢል ተከስተ ቡና ቤት ቡና እንደወረደ ያወራርዳል ።

ብሯ አመድ እስከምትሆን በየተራ የሎ ቤቷ መድመቋና እንሂኑ ባንከር መገናኛ ወዲያውም የሚታዩና የሚሽኮረመሙ ልጃገረዶች ለማሽኮርኮም (ቂቂቂ ) ተሜ አትጠፋም ።

አንዳንዶቹ ኪሳቸው የብር አኪር የሞላላቸው የሎ ቤቷን ፍቅር የገባቸው የሚናፍቁት ያህል 

ቆጥረው እንደ ወር ደመወዝተኛ መደበኛ ናቸው ።

እስቲ ልወዛወዝ ልወዛወዘው

አገኝሽ እንደሆን ልቤን ቢቀናው ።

የሙሉቀን ዜማና የተሜ ጠጪ የግመል ፈንጪ ቂቂቂ

ባንከሩ ሰውዬ ሞቅ ሲላቸውና ፊታቸው ላይ ያለው ቅላት በማሩ ጠጅ ወዝ የበለጠ ጎልቶ ሲወጣና አንደበታቸው ለጨዋታ ለቀቅ ሲል ባልንጀሮቻቸውን ብ* ነህ …ገና ት* ዳለህ 

ይላሉ ። የሚ*ዳ ቃር ይ*ዳቸውና

ለሰውዬው ወዳጅ የነበሩ የተሜው ቡድኑም ይህችን ቃል ለቀም አድርጎ ለዘመኑ በሚመጥን መልኩ መዝናኛና ጨዋታና ሣቅ ማድመቂያ አድርጓት ነበር ።

ለካስ የወደፊቱ ታይቷቸው ነበር ። 

ትዝብትህን ዐረብ ቤት (መደብር ) ውስጥ ጣለውና በግልፅ ቋንቋ ልንገርህ ገና ት*ዳለህ! 

አበስ ገበርኩ !

 

Filed in: Amharic