>

የእነታዴዎስ ታንቱ ክስ ሙሉ ይዘት

የእነታዴዎስ ታንቱ ክስ ሙሉ ይዘት

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለልደታ ምድብ 3ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት

ተከሳሾች

1ኛ. ታዴዎስ ታንቱ ብላቴ እድሜ፦ 70 ዓመት አድራሻ፦ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የቤት ቁጥር 2356

2ኛ. ጌጥዬ ያለው ጀመረ

እድሜ፦ 29 ዓመት አድራሻ፦ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 የቤት ቁጥር፦ አዲስ

1ኛ ክስ በሁለቱም ተከሳሾች ላይ

ወንጀሉ

በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32/1/ሀ/ እና 257/ሀ/ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ

የወንጀሉ ዝርዝር

ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥት ስርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀል እንዲሁም የጦር መሳሪያ ይዞ በማመፅ ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት በማነሳሳት በመንግሥት ላይ የሚደረግ ወንጀል እንዲፈጸም ለማድረግ ወይም ለመደገፍ በማሰብ በማናቸውም መንገድ በፌዴራሉ ወይም በክልል ሕገ መንግሥት የተቋቋመው ሥርዓት እንዲፈርስ ወይም እንዲለወጥ ለማድረግ እንዲሁም አንዱ ወገን በሌላው ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሳ ለማነሳሳት በማሰብ

1ኛ ተከሳሽ ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ራስ ሚዲያ በተባለ የዩቱዩብ ቻናል አማካኝነት “የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላ አማራጭ የለውም፤ ጭቆናው በዝቷል፤ ሕዝባዊ አመፅ ለመምራት መነሳሳት አሁን ነው፤ ዛሬ ነው። እስከ መቼ ተኝተን እንሞታለን፣ የአገዛዙን ጠንካራ ጎኖች በደንብ አጥንተን ማን ከማን ጋር ተሰልፏል፤ እንዴት ብንሄድ የመንግሥትን ስስ ብልት አግኝተን ቦርቡረን እናስወግዳለን፤ የአገዛዙን ደካማ ጎን እና ጠንካራ ጎን አጥንተን ደካማ ጎኑን በመጠቀም በዚያ በአገዛዙ ስስ ብልት በመግባት አገዛዙን በማዳከም ሕዝባዊ ሥልጣን እውን እንዲሆን መነሳሳት፣ ለሕዝባዊ አመፅ መነሳሳት ዛሬ ነው፣ አሁን ነው፤ ተኝተን አንሙት፤ እየተንቀሳቀስን እንሙት፤ መስዋዕትነት እንክፈል። ሀገራችንን እናድን፣ ነፃ እናውጣ፣ ባርነት ይብቃን” እያለ ሲያነሳሳ የነበረ በመሆኑ

2ኛ ተከሳሽ አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በተመሳሳይ የዩቱዩብ ቻናል አማካኝነት “ይህንን ጨፍጫፊ፣ ይህንን አፈናቃይ፣ ይህንን ገዳይ መንግሥት እንደ መንግሥት ተቀብለን መቀጠል አለብን ወይ? ፋኖ እንደ ውጭ ወራሪ መታገል የለበትም ወይ? ጣሊያን በመጣ ጊዜ እንደ መንግሥት ተቀብለው አይደለም አርበኞች አምስት ዓመት ሙሉ ሲታገሉ የነበረው፤ የውጭ ወራሪነቱን አውቀው ነው፤ እንደ መንግሥት አልተቀበሉትም፤ እንደ ውጭ ወራሪ እንጂ። ስለዚህ ይህ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ ተነስቷል ብለን ደምድመናል። ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሠራ ከሆነ፤ ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ  እንደ ውጭ ወራሪ ልንታገላቸው አይገባም ወይ? ፋኖ እነርሱን እንደ መንግሥት መቀበል አለበት ወይ?” እያለ ሲቀሰቅስ

1ኛ ተከሳሽም “መቀበል የለበትም። ይሄ መንግሥት ኢትዮጵያዊ አይደለም። ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣ ነው። መቅሰፍት ነው። ከወያኔ የከፋ ነውና አምርረን ይህንን አገዛዝ መቃዎምና ከሕዝብ ጫንቃ ላይ ማውረድ አለብን። ይህንን እንደ ፋሽት ኢጣሊያ እንደ ባዕድ ወራሪ በማየት ከሕዝብ ጫንቃ ላይ ማስወገድ አለብን” በማለት ተከሳሹ መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በተመሳሳይ የዩቲዩብ ቻናል “ሥራ እንዲቆም አድርገን፤ ታክሲ ሥራውን ሲያቆም፣ አውቶብሶች ሥራቸውን ሲያቆሙ ሰላም መንሳት ነው። በአደባባይ በግልፅ ወጥተን አንበሳ ሆነን መንግሥት መቀየር ባንችል ቁንጫ ሆነን ውስጥ ውስጡን ሰርስረን ገብተን ሰላም ነስተን፣ ምቾት አሳጥተን ይሄን ሰው በላ ሥርዓት ማመንመን እና ማስወገድ አለብን። የአማራ ልጅ የተባለ ሁሉም መታጠቅ አለበት። ምክንያቱም እርሱን የሚያድነው የለም። ትጥቅ ፍታ ማለት ትግሬ መጥቶ ይፍጅህና መሬትህን ይውሰድ በሕይዎት የተረፍከውንም የራሱ አሽከር አድርጎ እንደ ከብት ይንዳህ ማለት ነው። ፋኖ ትጥቅህን ፍታ ማለት ኦሮሞ በዚያ በኩል መጥቶ መሬትህን ወስዶ አንተንም አርዶ ምናልባት በአቅመ ቢስነትህ ንቆ በሕይዎት የሚተውህ ከሆነ ለእርሱ እግር አጣቢ እንድትሆን ተዘጋጅ ማለት ነው። ጠመንጃ በነፍስ ወከፍ በአማራ ቤት መኖር አለበት። ትጥቅ መፍታት የለበትም፤  አማራ አገዛዙ የሚለውን መስማት የለበትም፤ አገዛዙ እራሱ ጠላቱ ነው” እያለ ቅስቀሳ በማድረጉ

እንዲሁም ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ሀሌታ ቴቪ በተባለ የዩቱዩብ ቻናል ላይ “አማራ የሰማይን ከዋክብትና የምድርን አሽዋ የሚያህል ጠላት አለው፤ ስለዚህ ሁሉም አማራ መታጠቅ አለበት እንደ ጠላቱ ብዛት። እንደ አማራ ጠላት የበዛበት ከኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ዘሮች መካከል አለ ይሆን? በአሁን ጊዜ ሁሉም እየተነሳ አማራን ላጥፋ ይላል። አማራ ላይ እተኩሳለሁ ይላል፤ ይተኩሳልም” እያለ የአማራ ብሔር ተወላጆችን በሌሎች ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሱ እንዲሁም የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ኢትዮ 251 ሚዲያ በተባለ የዩቱዩብ ቻናል “ብሔር ብሔረሰብ ተብየው፣ ብሔር ብሔረሰብ ነኝ እያለ ራሱን የሚያቆለጳጵሰው የትም አይደርስም። ለሺህ ዓመት በአማራ ባሕልና ማህበራዊ ሕይዎት፤ ወግ ሥር ይኖራል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አመለካከት፤ የአማራ ሃይማኖት የበላይነትን ይዞ ይቀጥላል” እያለ የአማራ ብሔር በሌላው ላይ ባህሉን፣ ወጉን፣ ሃይማኖቱን ለመጫን የመጣ መስሎ እንዲታይና በሌላው ብሔር አማራ በጥርጣሬ እንዲታይና ተነጥሎ እንዲጠቃ ሲያነሳሳ የነበረ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር ወንጀል ተከሰዋል።

2ኛ ክስ በሁለቱም ተከሳሾች ላይ

ወንጀሉ

በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32/1/ሀ/  እና የጥላቻ ንግግር እና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀፅ 4 እና 7/4/ ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ

የወንጀሉ ዝርዝር

ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በአንድ በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ ብሔርን ከብሔር እና ሕዝብን መሰረት በማድረግ፦

1ኛ ተከሳሽ ታህሳስ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ሰላም ቲዩብ በተባለ የዩቱዩብ ቻናል አማካኝነት በተሰራጨው “የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ከሀዲ ነው። ሕዝቡ ራሱ የዓለም ውሸታም ነው። የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው። የሞኝነት መጀመሪያ ትግሬን ኢትዮጵያዊ ነው፣ ወገን ነው ብሎ ማሰብ ነው፤ ሸክም እንጂ እነርሱ ወገን ሆነው አያውቁም” በማለት

2ኛ ተከሳሽ አዘጋጅና አቅራቢ ሆኖ ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ራስ ሚዲያ በተባለ የዩቱዩብ ቻናል ላይ በተሰራጨው ንግግር

1ኛ ተከሳሽ “ኦሮሞ ሚስት ለማግኘት የሰውን ብልት ቆርጠው ነው የሚያመጡት፣ ከራሳቸው ጎሳ ውጭ ማንንም መግደል በገዳ ስርዓት መብት ነው፤ ገሎ ቅቤ መቀባት፣ ሰው ቢጠፋ መጨረሻ ላይ አውሬ ገድለው ጥያቄ ያቀርባሉ። በአብዛኛው ግን ሰው ያልገደለ ሰው አይደለም፤ መግደል በኦሮሞ ባሕል የተፈቀደ ነው። ለዚህም ነው የአረመኔነትን ትርጉም የሰጡት፤ ጫካ የሚገቡት ሰው ካልገደሉ ጸጉራቸውን አይላጩም። ጸጉራቸውን ለመላጨት ሰው ይገድላሉ። እንግዲህ የገዳ ስርዓት ከተባለ ይሄ ነው፤ በጣም ኋላ ቀር የሆነ ነው” ሲል  2ኛ ተከሳሽም “አሁን እንደ አንድ የዴሞክራሲ መገለጫ አድርገው የሚገልፁት ከግሪኮች ጋርም ከሌሎች ጋርም እያዛመዱ ገዳ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው እያሉ የተደጋጋሚ የሚለፍፉት ነገር ግን አንድ የገዳ መሪ ወይም ሉባ ከመሆኑ በፊት የሚያልፍባቸው መንገዶች አሉ። የመጀመሪያው ጉዳይ 40 ዓመት ሳይሞላው መገረዝ አይችልም። 40 ዓመት ሳይሞላው ከተገረዘ የሚወልደው ልጅ ሜዳ ላይ ተጥሎ እንዲገደል ያበረታታል። የገዳ ማህበር ያስገድዳል ጭምር” ሲል

1ኛ ተከሳሽም መልሶ “ይህ ከዴሞክራሲ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ግንኙነቱ ከድንቁርና ጋር፣ ልክ ከሌላው በቃላት ሊገለፅ ከማይችል ድንቁርና ጋር ነው ዝምድናው። የወላይታ ባህል ድንቁርናም ገደብ የለውም። በወላይታ ባህል የበኩር ልጅ ሴት ከሆነች ትቀበር ነበር። በቃ እንደተወለደች ወስዶ እንሰት ውስጥ ወይም ቦቆሎ ውስጥ ወደ ጓሮ ወስዶ ይቀብራል። ብዙ ሴቶች በተከታታይ ከተወለዱ አንዷ ትገደላለች። ትልቅም ትሁን ትንሽ ቤተዘመድ ተሰብስቦ፤ ተመክሮ እከሊትን እንግደል ተብላ ወደ ጓሮ ተወስዳ እንሰት ውስጥ ትታረዳለች። እንዲሁም አባቷ ነው የሚያርዳት። ከፋ አሁን አባቱ ሲሞት የአባቱን ሚስቶች የሚወርሰው የበኩር ልጁ ነው” ሲል

2ኛ ተከሳሽም “ይህንን ስናስብ አሁን ኅሊናችንን አይቀፍፍም፤ እናቱን መልሶ ያገባል ማለት ነው?” ሲል

1ኛ ተከሳሽም “እናቱም እንደሚስት ነው የምትታየው። የአባቱ አምስት 6 ሚስቶች ይኖራሉ። ባልየው ከሞተ የበኩር ልጁ ከሁሉም ጋር ይገናኛል። እንዳውም ገና አባቱ መታመም ሲጀምር ሚስቶቹን መገናኘት ሳይጀምር ይቀራል፤ ይሄ ሰውየ አይተርፍም ብሎ፤ ባህሉ ነው።

እናቱም በቃ እንደሚስት ነው የምትታየው፤ ደግሞም ርግጠኛ ነኝ ከእናቱም ጋር ግንኙነት ይፈፅማል። ምን የሚረባ ባህል አለው የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ። የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የምዕራብ ኢትዮጵያ እና የኦሮሞ ባህሎች በጠቅላላው የፓጋን ሕዝብ ባህሎች ስለሆኑ ከእነዚያ ምንም የሚወሰድ ነገር የለም” በማለት እያንቋሸሹ ሁለቱም ተከሳሾች እየተቀባበሉ ብሔርን ከብሔር እና ሕዝብን መሰረት በማድረግ ሆን ብለው ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ ንግግር በድምፅ እና በቪዲዮ ያሰራጩ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የጥላቻ ንግግርን በማሰራጨት ወንጀል ተከሰዋል።

3ኛ ክስ በሁለቱም ተከሳሾች ላይ

ወንጀሉ

በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32/1/ሀ/ እና 337 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ

የወንጀሉ ዝርዝር

ተከሳሾች የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴዎችን ለማሰናከል ወይም የሚያሰናክል አደጋ እንዲደርስባቸው ለማድረግ ወይም ወታደሮችን ከስነ ስርዓት ውጭ እንዲሆኑ ወይም እንዳይታዘዙ ለማነሳሳት በማሰብ ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ራስ ሚዲያ በተባለ የዩቱዩብ ቻናል አማካኝነት

2ኛ ተከሳሽ “በማዕረግ ደረጃ ያሉት፣ ከማዕረግ በታች ያሉት ወታደሮች በስፋት ከመከላከያ እየወጡ ወደ አማራ ልዩ ሃይል እየተቀላቀሉ ነው። በመሰረታዊነት እነርሱ በአንድ ብሔር የበላይነት ማለትም በኦሮሞ የበላይነት መያዝ ስለሚፈልጉ ሆን ብለውም ይገፋሉ። ሥራዬ ብለውም እያባረሩ ያስወጣሉ። ከዚያም በላይ ደግሞ የሰራዊቱ ፍላጎት ፋኖን መቀላቀል ነውና መከላከያ ውስጥ አንድም አማራ እንዳይኖር እየተደረገ ነው” ሲል

1ኛ ተከሳሽም ተቀብሎ “አመራር የሚሰጠው ሃይል ወይም ግለሰብ ወይም አዛዥ ፈፅም ያለውን ብቻ እየፈፀመ ለመኖር ከሆነ የአማራ ልጅ እዚያ መኖር ትርጉም የለውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት እምነት የጣለበት ፋኖ ላይ ነው። ፋኖን ነው ማጠንከር፣ መከላከያን እንደገና ማደራጀት ይቻላል ወገን የበላይነትን ከያዘ በኋላ፤ የኢትዮጵያ የጦር መኮንኖች ሁሉም የአንድ ዘር አባላት ሆነዋል” በማለት መረጃዎቹ ትክክል አለመሆናቸውን እያወቁ የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ ማሰራጨት ወንጀል ተከሰዋል።

4ኛ ክስ በሁለቱም ተከሳሾች ላይ

ወንጀሉ

በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32/1/ሀ/ የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀፅ 14 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ

የወንጀሉ ዝርዝር

ተከሳሽ በሕብረተሰቡ መካከል አመፅ፣ ሁከት ወይም ግጭት እንዲፈጠር በማሰብ 1ኛ ተከሳሽ ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ራስ ሚዲያ በተባለ የዩቱዩብ ቻናል አማካኝነት “የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላ አማራጭ የለውም፤ ጭቆናው በዝቷል። ሕዝባዊ አመፅ ለመምራት መነሳት ጊዜው አሁን ነው፤ ዛሬ ነው። እስከ መቼ ተኝተን እንሞታለን፣ ማን ከማን ጋር፣ እንዴት ብንሄድ የመንግሥትን ስስ ብልት ቦርቡረን እናስወግደዋለን፤ የአገዛዙን ደካማ ጎን እና ጠንካራ ጎን አጥንተን ደካማ ጎኑን በመጠቀም ከዚያ በአገዛዙ ስስ ብልት ገብተን አገዛዙን በማዳከም ሕዝባዊ ሥልጣን እውን ለማድረግ መነሳሳት፣ ለሕዝባዊ አመፅ መነሳሳት አሁን ነው፣ ዛሬ ነው። ተኝተን አንሙት፣ እየተንቀሳቀስን እንሙት። መስዋዕትነት እንክፈል፣ ሀገራችንን እናድን፣ ነፃ እናውጣ፣ ባርነት ይብቃን” እያለ ሲያነሳሳ የነበረ በመሆኑ

2ኛ ተከሳሽም አዘጋጅና አቅራቢ በመሆን ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በተመሳሳይ የዩቱዩብ ቻናል አማካኝነት “ይህንን ጨፍጫፊ፣ ይህንን ገዳይ መንግሥት፣ ይህንን አፈናቃይ እንደ መንግሥት ተቀብሎ መቀጠል አለበት ወይ? ፋኖ እንደ ውጭ ወራራ መታገል የለበትም ወይ? ጣሊያን በመጣ  ጊዜ እንደ መንግሥት ተቀብለው አልነበረም አርበኞች አምስት አመት ሙሉ ሲታገሉት የነበረው። የውጭ ወራሪነቱን አውቀውት ነው። እንደ መንግሥት አልተቀበሉትም፤ እንደ ውጭ ወራሪ እንጂ። ስለዚህ ይህንን መንግሥትም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ ተነስቷል ብለን ደምድመናል። ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሠሩ ከሆኑ፤ ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ እንደ ውጭ ወራሪ ልንታገላቸው አይገባም ወይ? ፋኖ እነርሱን እንደ መንግሥት መቀበል አለበት ወይ” እያለ ሲቀሰቅስ

1ኛ ተከሳሽም “መቀበል የለበትም። ይሄ መንግሥት ኢትዮጵያዊ አይደለም፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይበጅም፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣ ነው፣ መቅሰፍት ነው። ከወያኔ የከፋ ነውና አምርረን ይህንን አገዛዝ መቃወም እና ከሕዝብ ጫንቃ ላይ ማውረድ አለብን። ይህን እንደ ፋሽስት ኢጣሊያ እንደ ባዕድ ወራሪ በማየት ከሕዝብ ጫንቃ ላይ ማውረድ አለብን” እያለ ተከሳሹ መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በተመሳሳይ የዩቲዩብ ቻናል “ሥራ እንዲቆም አድርገን፣ ታክሲ ሥራውን ሲያቆም፣  አውቶብሶች ሥራቸውን ሲያቆሙ ሰላም መንሳት ነው። አደባባይ እንኳን በግልፅ ወጥተን አንበሳ ሆነን መንግሥት መቀየር ባንችል ቁንጫ ሆነን ውስጥ ውስጡን ሰርስረን ገብተን ሰላም ነስተን ምቾት አሳጥተን ይሄን ሰው በላ ስርዓት ማመንመንና ማስወገድ አለብን፣ ሁሉም የአማራ ልጅ መታጠቅ አለበት። አማራ አገዛዙ የሚለውን መስማት የለበትም። አገዛዙ ራሱ ጠላቱ ነው” እያለ ቅስቀሳ በማድረግ

እንዲሁም ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ሀሌታ ቴቪ በተባለ የዩቱዩብ ቻናል ላይ አማራ የሰማይን ክዋክብትና የምድርን አሽዋ የሚያክል ጠላት አለው። ስለዚህ ሁሉም አማራ መታጠቅ አለበት። እንደ ጠላቱ ብዛት በአሁኑ ጊዜ ሁሉም እየተነሳ አማራን ላጥፋ ይላል። ያም እየተነሳ አማራ ላይ እተኩሳለሁ ይላል፤ ይተኩሳልም። ይገድላልም” እያለ የአማራ ብሔር ተወላጆችን በሌሎች ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሱ እንዲሁም የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ኢትዮ 251 ሚዲያ በተባለ የዩቱዩብ ቻናል “ብሔር ብሔረሰብ ተብየው፣ ብሔር ብሔረሰብ ነኝ እያለ ራሱን የሚያቆለጳጵሰው የትም አይደርስም። ለሺህዎች አመታት በአማራ ባሕልና ማህበራዊ ህይዎት፣ ወግ ስር ይኖራል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወደደም ተጠላ ይኖራል፣ የአማራ ባህል፣ የአማራ ወግ፣ የአማራ ልምድ፣ የአማራ አመለካከት፣ የአማራ ሃይማኖት የበላይነትን ይዞ ይቀጥላል” እያለ የአማራ ብሔር በሌላው ላይ ባህሉን፣ ወጉን እና ሃይማኖቱን ለመጫን የመጣ መስሎ እንዲታይና በሌላው ብሔር አማራ በጥርጣሬ እንዲታይና ተነጥሎ እንዲጠቃ በኮምፒዩተር ስርዓት አማካኝነት በድምፅና በቪዲዮ ያሰራጨ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በሕዝብ ደህንነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተከሰዋል።

5ኛ ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ

ወንጀሉ

በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀፅ 244/1/ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ

የወንጀሉ ዝርዝር

ተከሳሽ የሀገሪቱን መንግሥት በስድብ ለማዋረድ በማሰብ  መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ራስ ሚዲያ በተባለ የዩቲዩብ ቻናል አማካኝነት “አሁን በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ጸረ ሉዓላዊ ነው። ጸረ ሕዝብ ነው። ጸረ ኢትዮጵያ ነው። ጸረ ታሪክ ነው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ጸረ ሰንደቅ አላማ ነው። ክፉ ነገሮችን ሁሉ አሟልቶ የሚገኝ አገዛዝ ነው” በማለት የተሳደበ ወይም በሀሰት የወነጀለ በመሆኑ የሀገሪቱን መንግሥት ስም በማጥፋትና ማዋረድ ወንጀል ተከሷል።

የማስረጃ ዝርዝር

ሀ. የሰነድ

1. የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን በቁጥር ኢመብባ/4009/1369 ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፅፎ በተሰጠ ተከሳሾች የማነሳሳትና የጥላቻ ንግግሮቹን ያደረጉበት ቪዲዮዎች የተላለፉበትን ቀን እንዲሁም የቻናሎቹን ስም ጠቅሰው የሰጡት 03 ገፅ

2. በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን በቁጥር ኢመብባ/4009/1070 ሰኔ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፅፎ የተሰጠ ተከሳሾች የማነሳሳትና የጥላቻ ንግግሮችን ያሰራጩበት በባለሥልጣኑ ያልተመዘገበ መሆኑን የሚገልፅ 04 ገፅ

3. ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የመከላከያ ሚንስቴር የመከላከያ ወታደራዊ ዓ/ሕግ ዋና ዳይሬክተር ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ተይዞ ተከሳሽ ያረጋቸው ንግግሮችን አስመልክቶ በቀን 11/10/2014 ዓ.ም. የሰጠው ማስረጃ 02 ገፅ

ለ. ገላጭ (ሲዲዎች)

ተከሳሾች በክሶቹ ዝርዝር ላይ የተጠቀሱትን ንግግሮች ያደረጉባቸው ቪዲዮዎች 04 ሲዲ

መግለጫ፦ 1ኛ ተከሳሽ ከ10/09/2014 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።

Filed in: Amharic