>

በወቅታዊ አሳሳቢ ጉዳይ የተሰጠ የእናት ፓርቲ መግለጫ

በወቅታዊ አሳሳቢ ጉዳይ የተሰጠ የእናት ፓርቲ መግለጫ

 

ከአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገዶች ላይ የሚደርሰው እንግልት ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ መሆኑ አሳስቦናል…!!!

ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ሕገ-መንግስታዊ መብት የተነፈጋቸውና ወደአዲስ አበባ ከተማ እንዳይገቡ በተከለከሉ የአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው እንግልት ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ መሆኑን ከተለያየ አካባቢ ወደአዲስ አበባ ከተማ በመጓዝ ላይ የነበሩ እና የችግሩ ሰለባ የሆኑ መንገደኞች ገለጸዋል። መንገደኞቹ ከአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች ሰሜን ሸዋ ዞንን አልፈው ኦሮሚያ ክልል ከገቡ በኃላ በተደጋጋሚ መታወቂያ ይጠየቃሉ፣ ለረጅም ስዓት ይጉላላሉ፤ በመጨረሻም ወደመጡበት እንዲመለሱ ይገደዳሉ። መንገደኞቹ ከሸኖ ጀምሮ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው ያሉ ሲሆን በተለይም ከአሌልቱ እስከ ገደራ ያለው እንግልት የከፋ እንደሆነ ገልጸዋል። መንገደኞቹ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የሚከለከሉበት ምክንያት የአዲስ አበባ መታወቂያ የላችሁም በሚል ሲሆን አብዛኞቹ ወደመጡበት አካባቢ እየተመለሱ ሲሆን ሕጻናትን የያዙ እናቶች እና ከረጅም ርቀት የመጡት ግን በገንዘብ እጥረት ምክንያት መመለስ ስላልቻሉ ለከፋ እንግልት እየተዳረጉ ነው። ከመንገደኞቹ በተጨማሪ የጭነት መኪኖችም መታወቂያ እየታየ የማለፊያ ገንዘብ ከጸጥታ አካላት እንደሚጠየቁና ያልከፈሉ ማልፍ እንደማይችሉ ተገልጿል።

መንገደኞቹ በወንጀል እስካልተጠረጠሩ ድረስ ከቦታ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስ ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ሆኖ ሳለ የሌላ ሀገር ዜጋ እስኪመስሉ ድረስ የአዲስ አበባ መታወቂያ ስለሌላችሁ ወደ አዲስ አበባ መግባት እትችሉም በሚል ግፍ እየተፈጸመባቸው ነው። ይህ እንቅስቃሴ በወለጋ ላይ ማንነትን መሰረት አድርጎ የሚፈጸመው ጭፍጨፋ መልኩን ቀይሮ የመምጣቱ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል በመሆኑ ከእንቁላሉ ሊታረም ይገባል እንላለለን።

ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ

Filed in: Amharic