>

በአሳፋሪ የፈጠራ ክስ ለእስር የተዳረገው የዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ነገር...!!! (መስከረም አበራ)

በአሳፋሪ የፈጠራ ክስ ለእስር የተዳረገው የዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ነገር…!!!

መስከረም አበራ

እውቀት ያጓጓኛል፣የአዋቂ ብክነት ያሳስበኛል፡፡ ሃገሬ ደግሞ እውቀት አያገጓጓትም፣አዋቂ አይስባትም፤ እውቀት ታጣጥላለች፣አዋቂ ታሳድዳለች፡፡ ምስሉን የምትመለከቱት ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ይባላል፡፡ በሙያው የህክምና ዶክተር ነው፡፡ በበርካታ የውጭ ሃገራት ተዘዋውሮ ትምህርት የቀሰመ ፣ የተመሰከረለት የስትራቴጅ ባለሙያ ነው፡፡  ወያኔ እንኳን ይህን አውቆ አሉ የተባሉ የማህባራዊ ጉዳይ ስትራቴጅዎችን እንዲሰራለት ጠይቆ ሊያሰራው ሞክሮ ነበር፡፡

እሱም በዚህ ሃገሩን የሚረዳ መስሎት ሞክሮ ነበር፡፡ የወያኔ ነገር አልጥም ሲለው ነገሩን ተወው እንጅ፡፡

የወያኔ ነገር አልጥም ሲለው የዜግነት ፖለቲካን እናመጣለን የሚሉ ፓርቲዎችን ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ሁሉም አልሆን ሲል የአማራ ህዝብን ከሞት የማዳኑ ስራ ይዋል ይደር የማይባል ሆኖ አገኘውና በዚሁ አንፃር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ብዙ ሰርቷል፡፡ እንደ ታላቅነቱም ተተኪዎችን ለማፍራት ይተጋል፡፡ እውቀት ፈልጎ ለተጠጋው ወጣት ሁሉ እንደ አስተማሪ ከማስተማር አልፎ የሚነበብ በማጋራት ጭምር ሃገሪቱ በእውቀት መጥፋት እንዳትጠፋ ይጥር ነበር፡፡ ዶ/ር ወንድ ወሰን የአማራ ህዝብ የወረደበትን በህይወት የመኖር መብት የመነፈግን ያህል መከራ በልኩ የሚረዳ ሰው ነው፡፡ ተረድቶም አልቀረም ይህ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ሰብዓዊ ክብሩ ተጠብቆ እንዲኖር የሚያስፈልገውን ትግል ለመታገል ቆርጦ የተነሳ ሰው ነው፡፡ ሁሉም እንቅስቃሴው በእውቀት እና ሃላፊነት የተሞላ ነው፡፡ ሰርቶ አይደክመውም ፤ ላመነበት ብርቱ ሰው ነው፡፡ አማራ የተባለ ህዝብ ሁሉ ጥብቅና ሊቆምለት የሚገባ ሁነኛ ታጋይ ነው ፡፡ የማታውቁት ተዋወቁት፣ ይፈታዘንድ ድምፅ ሁኑት…..

የዶ/ር ወንድወሰን እስር ተዓምር እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ ጥፋት አለበት ተብሎ ከተጠረጠረ ይታሰር ግድ የለም፡፡ የሚገርመው ነገር የቀረበበት ክስ ጉዳይ ነው፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን እና ጓዶቹ መጀመሪያ የተከሰሱት የሃይማኖት ግጭት በማስነሳት ነው ተባለ፣ይህ አላስኬድ ሲል ደግሞ ፋኖን በአንድ እዝ ስር ለማስገባት ተባለ ይህም አላስኬድ ሲል ደግሞ ባህርዳር የፈነዳው ቦምብ በእናንተ አቀናባሪነት ነው ተባለ! ህሊና ያለው ይፍረድ ……

Filed in: Amharic